የአሜሪካ እና የሰሜን ኮሪያ ስምምነት
ማክሰኞ፣ ሰኔ 5 2010የዓለም መንግሥታት እና መሪዎች የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ዛሬ የደረሱበትን ስምምነት አደነቁ። በተለይ የሰሜን ኮሪያ የቀድሞ ባላንጦች ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ስምምነቱን ለአካባቢው ሰላም ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ሲሉት፤ የሰሜን ኮሪያ ወዳጅ የምትባለዉ ቻይና ደግሞ «አዲስ ታሪክ» ስትል አወድሳዋለች። ሁለቱ መሪዎች ዛሬ ሲንጋፖር ውስጥ ባካሄዱት ጉባኤ የኮርያን ልሳነ ምድር ሙሉ በሙሉ ከኒዩክልየር መሣሪያ ነጻ ለማድረግ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል። ኂሩት መለሰ ዘገባ አላት
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሰሜን ኮሪያው መሪ የኪም ጆንግ ኡን ታሪካዊ የተባለው ጉባኤ ውጤት ከዓለም መንግሥታት እና መሪዎች የሚቸረው ሙገሳ እና አድናቆት ቀጥሏል። ሁለቱ መሪዎች ሰላም i,ማስፈን ዓላማ ያለው አዲስ ግንኙነት ለመመሥረት ዛሬ ሲንጋፖር ውስጥ የደረሱበት ስምምነት በተለይ ለሰሜን ኮሪያ ጎረቤቶች ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ልዩ ትርጉም አለው። ጃፓን የትራምፕ እና የኪምን ስምምነት ለኮሪያ ልሳነ ምድር ብሩህ ተስፋ የሚሰጥ ብላዋለች። ደቡብ ኮሪያም በደስታ ነው የተቀበለችው። የሰሜን ኮሪያ የቅርብ ወዳጅ ቻይናም ሁለቱ መሪዎች በአንድ ጠረጴዛ ተቀምጠው ፊት ለፊት መወያያተቻው በራሱ አዲስ ታሪክ ነው ብላለች ። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይኢ
«ዩናይትድ ስቴትስ እና ሰሜን ኮሪያ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ተቃራኒ እና በጠላትነት የሚተያዩ ነበሩ። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ዛሬ በአንድ ላይ መቀመጥ መቻላቸው እና በእኩል ደረጃ መወያየታቸው በራሱ ትልቅ እና በጎ ውጤት ነው።ይህም አዲስ ታሪክ ፈጥሯል። በርግጥ ቻይና የምትደግፈው ነገር ነው። ምክንያቱም እኛ በትክክል እንዲሆን የምንፈልገው እና ከግብ
እንዲደርስም ከባድ ጥረት ስናደርግበት የቆየነው ጉዳይ ነው።»
የአውሮጳ ህብረት የኪምን እና የትራምፕን ስምምነት ወሳኝ እና አስፈላጊ እርምጃ ብሎታል። የህብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ፌደሪካ ሞጎሮኒ ዛሬ ባወጡት መግለጫ ስምምነቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የተመ የፀጥታ ምክር ቤት እንደሚሉት የኮሪያን ልሳነ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኒዩክልየር ጦር መሣሪያ ነጻ የማድረጉ ግብ ላይ መድረስ እንደሚቻል ግልጽ ምልክት ነው ብለውታል።
የትራምፕ እና የኪም ታሪካዊ ጉባኤ 40 ደቂቃ ነበር የወሰደው። በጉባኤው ማጠቃለያም የኮሪያን ልሳነ ምድር ከኒዩክልየር ጦር መሳሪያ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማድረግ የተስማሙበትን ሰነድ ፈርመዋል። ባለ አራት ነጥቡ ሰነድ ሰሜን ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስ አዲስ ግንኙነት ለመመስረት ፣ የተረጋጋ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቆርጠው መነሳታቸውን እንዲሁም ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ ፓንሙጆብ ውስጥ ያወጡትን የጋራ መግለጫ ዳግም ማረጋገጣቸውን ያካትታል። ሁለቱ ወገኖች ተጨማሪ ድርድሮችን ለማድረግ መስማማታቸው በሰነዱ ማጠቃለያ ላይ ተጠቅሷል። ሁለቱ መሪዎች የጋራውን የስምምነት ሰነድ ከፈረሙ በኋላ ኪም ተጨማሪ ቃል እንደገቡላቸው ትራምፕ እዚያው ሲንጋፖር ውስጥ ለብቻቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
" ሊቀመንበር ኪም ሰሜን ኮሪያ ዋና የሚሳይል ሞተሮች መፈተሻ ስፍራን እያወደመች መሆኑን ነግረውኛል። ይህ በተፈራረምነው ሰነድ ውስጥ የለም። በዚህ ላይ የተስማማነው ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ ነው። ይህ ትልቅ ነገር ነው። ሚሳይሎችን የሚፈትሹበት ስፍራ በጣም በቅርቡ እንዲወድም ይደረጋል።»
ኪም እና ትራምፕ አንድ ላይ ተመግበዋል። አብረው ሲንሸራሸሩም ታይተዋል። ኪም ባቀረቡት ጥያቄ የትራምፕ ልዩ መኪና ተከፍቶላቸው ውስጡን ተመልክተዋል። ቻይና በሰጠችው ቦይንግ 747 አውሮፕላን ከፒዮንግዮንግ ሲንጋፖር የሄዱት ኪም እንዳሉት የስምምነቱን ሰነድ ከመፈረማቸው በፊት መንግሥታቸው ያለፈውን በነበር ትቶ ለማለፍ ወስኗል።
«ዛሬ ታሪካዊ ውይይት አካሂደናል። ያለፈውንም ወደ ኋላ ለመተው ወስነናል። እናም ታሪካዊ ሰነድ ልንፈርም ነው። ዓለም ከፍ ያለ ለውጥ ያያል።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህ ውይይት እንዲካሄድ በማድረጋቸው ምስጋናየን ልገልጽላቸው እወዳለሁ። አመሰግናለሁ።»
ታሪካዊው ጉባኤ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሰሜን ኮሪያን ከኒክልየር ባላንጣነት እና የቃላት ጦርነት ወደ ወዳጅነት የሚያሸጋግራቸው ድልድይ ይመስላል። ይሁን እና ሰሜን ኮሪያ በገባችው ቃል መሠረት የኒዩክልየር ትጥቋን መፍታት ሳትጀምር ዩናይትድ ስቴትስ እስከዛሬ የጣለችባትን ማዕቀብ እንደማታነሳ አስታውቃለች።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ