1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሐምሌ 3 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ሐምሌ 3 2009

ዋይኔ ሩኒ ወደ ልጅነት ቡድኑ ተመልሷል። ከእንግዲህ በማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን አይታይም። በዋይኔ ሩኒ እግር የቤልጂየሙ አጥቂ ተተክቷል። ወደ 85 ሚሊዮን ዩሮ ግድም ክፍያ ቀርቦለታል። ሌሎች የዝውውር ዜናዎችንም አካተናል። በፎርሙላ 1የመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል በነጥብ እየመራ ነው። ሌዊስ ሀሚልተን በ20 ነጥብ ተበልጧል። 

https://p.dw.com/p/2gIGh
Symbolbild Fußball, Ball im Tor
ምስል picture-alliance/blickwinkel/McPhoto

ስፖርት፣ ሐምሌ ሶስት፣ 2009 ዓም

ዋይኔ ሩኒ ወደ ልጅነት ቡድኑ ተመልሷል። ከእንግዲህ በማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን ውስጥ አይታይም። በዋይኔ ሩኒ እግር የቤልጂየሙ አጥቂ ተተክቷል። ወደ 85 ሚሊዮን ዩሮ ግድም ክፍያ ቀርቦለታል። ሌሎች የዝውውር ዜናዎችንም አካተናል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል በነጥብ እየመራ ነው። በአራተኛነት ያጠናቀቀው ብሪታንያዊው ሌዊስ ሀሚልተን በጀርመናዊ ተፎካካሪው በ20 ነጥብ ተበልጧል። 

እግር ኳስ
ሊጀመር አንድ ወር ግድም በቀረው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ቡድኖች ወሳኝ ተጨዋቾችን እያስፈረሙ ነው። ቸልሲ የጀርመኑን የመሀል ተከላካይ አንቶኒዮ ሩይዲገርን ከኤ ኤስ ሮማ አስፈርሟል። የ24 ዓመቱ የቀድሞ የሽቱትጋርት ተጨዋች ከፕሬሚየር ሊጉ ባለድል ቸልሲ ጋር ለመቆየት የ5 ዓመት ውል ፈርሟል።  እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2015 አንቶኒዮ ሩዲይገር ወደ ጣሊያኑ ሴሪኣ ቡድን ያቀናው በውሰት ነበር፤ ኾኖም ያኔ ሮማ ወዲያው ነበር በ9 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ የገዛው።

በሌላ የዝውውር ዜና ዋይኔ ሩኒ በ18 ዓመቱ ለማንቸስተር ዩናይትድ ተሰልፎ ለ13 ዓመታት አብሮት ከዘለቀው ቡድኑ ጋር ፍቺ ፈጽሟል። ዋይኔ ሩኒ ከማንቸስተር ዩናይትድ የወጣው በአሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ቡድን ውስጥ ብዙም ትኩረት ባለማግኘቱ ነው። «ታላቅ ተጨዋች ከሚጠብቀው በታች ትንሽ ሲጫወት መመልከት መቼም ቢሆን ቀላል አይደለም» ያሉት የማንቸስተሩ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኝሆ አክለው ሲናገሩ፦ «ወደ ኤቨርተን ለመመለስ ሲጠይቅ ላከላክለው አልፈለግኹም» ብለዋል። 

Fußball Nationalspieler Antonio Rüdiger
ምስል Getty Images/AFP/P. Stollarz

በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ ገጹ «ወደ ኤቨርተን ለመመለስ ጓጉቻለሁ» ያለው ዋይኔ ሩኒ የኤቨርተኑ አሰልጣኝን ስም በመጥቀስ «ከሮናልድ ኮማን እና ከወጣቶቹ ጋር እስክገናኝ ቸኩያለሁ» ሲል ጽፏል።  

ዋይኔ ሩኒ በ13 ዓመት የማንቸስተር ዩናይትድ ቆይታው  በ253 ግቦቹ የቡድኑ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ መሆን ችሏል፤ ከአዲሱ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኝሆ ጋር ግን ሊጣጣም እንደማይችል ግልጽ ነበር። 

ዋይኔ ሩኒ የዛሬ 13 ዓመት በ25.6 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ማንቸስተር  ዩናይትድ ሲመጣ ብዙዎች የክፍያው ከፍተኛነትን እና የተጨዋቹን ልጅነት በመጥቀስ አጉረምርመው ነበር። ለሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ  ከቱርኩ ፌኔርባህ ቡድን ጋር ለነበረው ወሳኝ ጨዋታ ወደ ኦልድትራፎርድ ሜዳ ሲገባም ዋይኔ ሩኒ የመጀመሪያው ነበር። በዕለቱ በተደረገው ግጥሚያ ግን ዋይኔ ሩኒ የተጠራጣሪዎቹን አንደበት ለማዘጋት ፋታም አልወሰደበት።

የዛሬ 13 ዓመት ዋይኔ ሩኒ የማንቸስተር ዩናይትድን መለያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሶ በታየበት እና በሜዳው 6 ለ2 ባሸነፈበት ጨዋታ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሄት ትሪክ ሠርቶ ብዙዎችን አስደምሟል። ዛሬ ማንቸስተር ዩናይትድን ተሰናብቶ ገና በ9 ዓመት ለጋ ዕድሜው የእግር ኳስ «ሀሁ»ን ወዳስቆጠረው የልጅነት ቡድኑ ኤቨርተን አቅንቷል። 

ዋይኔ ሩኒ ከማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ኤቨርተን ሲመለስ፤ የኤቨርተኑ ሮሜሉ ሉካኩ ደግሞ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ለማቅናት ፈርሟል፤ የዋይኔ ሩኒ ቦታን ለመሸፈን። የ24 ዓመቱ  ሮሜሉ ከማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ጥሪ ሲቀርብለት ዐይኑን እንዳላሸ ነው የተናገረው። የቤልጂየም ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አጥቂው ሮሜሉ ሉካኩን ለመውሰድ በሆዜ ሞሪኝሆ የሚመራው ማንቸስተር ዩናይትድ እንደመነሻ 85 ሚሊዮን ዩሮ ክፍያ ውል ማዘጋጀት ነበረበት።                                     

ቸልሲ የሪያል ማድሪዱ የ24 ዓመት ወጣት አጥቂ አልቫሮ ሞራታን ለማስመጣት 70 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል። የኢንተር ሚላን  አማካይ ኢቫን ፔሪሲች የተጨዋቾች የዝውውር ጊዜ ከማብቃቱ አስቀድሞ ወደ ኦልትራፎርድ ሊያቀና እንደሚችል ተገልጧል። የ28 ዓመቱ አጥቂ ገና ከወዲሁ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ለማቅናት ሻንጣዎቹን መሸካከፍ መጀመሩም ተዘግቧል። አርሰናል  የሞናኮው የክንፍ ተጨዋች ቶማስ ሌማርን ለማስመጣት ለሦስተኛ ጊዜ ያሻሻለውን የ30 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። አርሰናል ቀደም ሲል ፈረንሳይ ውስጥ የሚጫተው የክንፍ ተጨዋችን በ30 እና በ40 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ለማስመጣት ለሁለት ጊዜ ጥያቄ አቅርቦለት ነበር። ቶማስ ሌማር በ45 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ መድፈኞቹ አርሰናሎች ይመጣ ይሆናል። 

Frankreich Fußball-EM Slowakei vs. England Wayne Rooney
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

የእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስበርግ የእግር ኳስ ቡድንን የፌስቡክ ባለቤት ቢሊየነሩ ማርክ ሱከርበርግ የሚደግፈው አንድ የአሜሪካ ተቋም  በ1 ቢሊዮን ፓውንድ ሊገዛው ነው የሚባለውን ዜና ቶትንሀም አጣጣለው። ቶትንሀምን ሊገዛ ነው የተባለው አይኮኒክ ካፒታል የተሰኘ አንድ የአሜሪካ ኢንቨርስትመንት ኩባንያ ሲሆን የሚደገፈውም በፌስቡክ ባለቤቱ ቢሊየነር እንደሆነ ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ በድረ-ገጹ ዘግቦታል።  

ለአፍሪቃ የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ቀድሞ ማለፉን ያረጋገጠው የቱኒዝያው ኤስፔራንስ ቅዱስ ጊዮርጊስን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት በመርታት ከምድቡ በ12 ነጥብ አንደኛ ሆኗል። ጨዋታው ከቱኒዝያ መዲና ቱኒስ አቅራቢያ በሚገኝ ስታዲየም ነበር የተከናወነው። በትናንትናው ውጤት መሠረት ከምድቡ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ የሚገኘው የደቡብ አፍሪቃው ማሜሎዲ ሰንዳውን ነው። በሰበሰበው 9 ነጥብ ኤስፔራንስን ተከትሎ ወደ ሩብ ፍጻሜው አልፏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (AS V.) ተመሳሳይ አምስት ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ 3ኛ ደረጃ ሆኖ አጠናቋል። 

አትሌቲክስ
ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በሚሳተፉበት እና ኬንያ ውስጥ ከሐምሌ 5 እስከ 10ቀን 2009 ዓ. ም. ድረስ በሚከናወነው 10ኛው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚወዳደሩ አትሌቶች ማንነት ይፋ ተደረገ። በውድድሩ 12 ወንዶች፣ 11 ሴቶች በአጠቃላይ  ድምር 23 አትሌቶች በ6 አይነነት ውድድሮች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጧል።

Österreich, Start der Formel 1 in Spielberg
ምስል picture-alliance/H.Neubauer

የመኪና ሽቅድምድም
ሽፒልበርግ ውስጥ በተከናወነው የፎርሙላ አንድ የአውስትሪያ ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድም የነጥብ ተፎካካሪዎቹ ሰባስቲያን ፌትል እና ሌዊስ ሐሚልተን ድል አልቀናቸውም። በውድድሩ የመርሴዲስ አሽከርካሪው ቫልተሪ ቦታስ አስደናቂ በሆነ ፍጥነት በማሽከርከር አሸናፊ ኾኗል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን በፌራሪው አሸክርካሪ የነጥብ ተቀናቃኙ ሰባስቲያን ፌትል እና በዳኒኤል ሪካርዶ ተቀድሞ በአራተኛነት አጠናቋል። በ2ኛነት ያጠናቀቀው ሰባስቲያን ፌትል እስካሁን 171 ነጥቦች ሰብስቧል። ሌዊስ ሐሚልተን በ20 ነጥብ እየተመራ 151 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሰባስቲያን ፌትል ለፌራሪ ቡድኑ ዳግም አዲስ ውል ሊፈርም እንደሆነም እየተነገረ ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ