1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ መጋቢት 28 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ሰኞ፣ መጋቢት 28 2007

በስፔን ላሊጋ ክሪያስቲያኖ ሮናልዶ በ8 ደቂቃ ሐትሪክ በመሥራት ለቡድኑ 5 ግቦችን አስቆጥሯል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ሊሰናበቱ እንደሆነ ተገለጠ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዳጉ ማራቶን የሩጫ ውድድር በወንድም በሴትም አሸናፊ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/1F3J6
Deutschland Fußball Champions League Achtelfinale Real Madrid - Schalke 04
ምስል Reuters/J. Medina

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ፖርቺጊዙ ማሪያኖ ባሬቶ ሊሰናበቱ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ለዶይቸ ቬለ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ይፋ አደረገ። ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ አሠልጣኙ ቃል ከገቧቸው አራት ነጥቦች ያሳኩት አንዱን ብቻ ነው ብሏል። አሠልጣኙ ካለፈው ዓመት አንስቶ በቆዩበት የአሠልጣኝነት ዘመን ለደሞዝ ብቻ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ተከፍሏቸዋል። በወር የ18 ሺህ ዶላር ተከፋይ ነበሩ። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ ግራናዳን ትናንት 9 ለ1 በሆነ እጅግ ሰፊ ልዩነት ግራ አጋብቶ ልኮታል። በዕለቱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ8 ደቂቃዎች ውስጥ በተከታታይ ሦስት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ሐትሪክ ሠርቷል። በ90ኛው ደቂቃ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ ያሳረፋትን ኳስ ጨምሮ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ አምስት ግቦችን አስቆጥሯል።

Schalke vs. Madrid
ክሪስቲያኖ ሮናልዶምስል Getty Images

በእርግጥ ለ25 ደቂቃዎች ያኽል መረባቸውን ሳያስደፍሩ ለመቆየት ችለው ነበር፤ ግራናዳዎች። 25ኛዋ ደቂቃ ላይ ግን በግብ ናዳ እንዲፍረከረኩ ቀዳሚ የሆነችዋን ግብ ጋሬት ቤል ለሪያል ማድሪድ በድንቅ ኹናቴ ግብ ጠባቂውን እና ተከላካዮችን አልፎ ያስቆጥራል። ከዚያ በኋላ ግራናዳዎች የቀራቸው ነገር ቢኖር በሪያል ማድሪድ ኃያል የቁጣ በትር ደቂቃ በደቂቃ መሠቃየት ነበር።

በደቡብ ኮሪያ ዴጉ ትናንት በተከናወነ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ዓለም አቀፍ ማኅበር የማራቶን ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም በአንደኛነት ድል ተቀዳጅተዋል። በወንዶች ፉክክር ግርማይ ብርሐኑ አሸናፊ ሲሆን፤ በሴቶች ደግሞ መሠለች መልካሙ ከተፎካካሪዎቿ ልቃ የበላይ ሆናለች። በዴጉው የሩጫ ውድድር በ6 ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያውያን በኹለቱም ፉክክሮች ሲያሸንፉ ትናንት ለሦስተኛ ጊዜ ነው። ለኹለቱም አትሌቶች የትናንትናው ድል በማራቶን የሩጫ ዘርፍ ኹለተኛ ድላቸው ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል።

Marathonläufer
ምስል Fotolia/ruigsantos

ግርማይ ብርሐኑ በአንደኛነት ያጠናቀቀው በ2:07:26በመግባት ሲሆን፤ ይኽ ሠዓት በዚህ የውድድር ዘርፍ ኹለተኛው ፈጣኑ ሠዓት እንደሆነ ተጠቅሷል። ነፋሻማ በነበረው የትናንት ማለዳ የአየር ንብረት 14,452 ሯጮች በዴጉ ጎዳናዎች ላይ መትመማቸው ታውቋል። ግርማይ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ኬንያውያኑ ስቴፋን ቼምላኒ እና ቤንጃሚን ሙታይን ጨምሮ ስድስት ሯጮች በነበሩበት ቡድን ውስጥ ከፊት ከፊት ይሮጥ ነበር።

ከውድድሩ ማጠናቀቂያ ቦታ በርካታ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከተፎካካሪዎቹ ኬንያውያን አፈትልኮ በመውጣት ነው አንደኛ የሆነው። ኬንያዊው አትሌት ስቴፋን ቼምላኒ ከግርማይ አንድ ደቂቃ ግድም ዘግይቶ በ2:08:21በመግባት ኹለተኛ ሆኗል። ሌላኛው የሀገሩ ልጅ ቤንጃሚን ሙታይ ደግሞ 33 ሠከንዶች ዘግይቶ በሦስተኛነት አጠናቋል።

ዴጉ በተከናወነው በዚሁ የሴቶች የማራቶን ሩጫ ውድድር መሠለች መልካሙ ተፎካካሪዎቿን ወደ ኋላ አስቀርታ አንደኛ የሆነችው በ2:27:24በመግባት ነበር። ሆኖም ትናንት በአሸናፊነት ያስመዘገበችው ሠዓት ከእዚህ ቀደም ካስቆጠረችው ዝቅተኛው መሆኑ ተዘግቧል። መሠለች መልካሙን በመከተል ኹለተኛ የሆነችውም ኢትዮጵያዊቷ ድንቅነሽ መካሻ ናት። የገባችበት ሠዓት 2:29:44ነው። ጃፓናዊቷ አዩሚ ሳካይዳ በ2:30:39ሦስተኛ ሆናለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ደጋፊዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ደጋፊዎችምስል DW/H. Turuneh

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካለፈው ዓመት አንስቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ፖርቺጊዙ ማሪያኖ ባሬቶን ሊያሰናብት እንደሚችል ይፋ አደርገ።

የ57 ዓመቱ አሠልጣኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለማሠልጠን የፈረሙት ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት በ2006 ዓም የካቲት ወር ውስጥ ነበር። ፌዴሬሽኑ አሠልጣኙን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሲያስመጣ ዋነኛ ግቡ አድርጎ ያሠፈረው፤ በውጭ ሀገር አሠልጣኝ አመራር ብሔራዊ ቡድኑን እጎአ በ2015 ጊኒ ባዘጋጀችው የአፍሪቃ ዋንጫ ላይ ተፎካካሪ ማድረግ ነበር። ሆኖም ብሔራዊ ቡድኑ ስኬት ርቆት በተደጋጋሚ ሽንፈት ቀምሶ ከምድብ ማጣሪያው የመጨረሻ ሆኖ ማጠናቀቁ ይታወሳል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩን ዛሬ በስልክ አነጋግረናቸዋል፤ አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ይፋዊ በሆነ መልኩ ገና ባይሰናበቱም ከአሁን በኋላ ፌዴሬሽኑ ሊታገሳቸው እንደማይችል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውምስል DW/H. Turuneh

አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የቀድሞው ኢትዮጵያዊ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ተክተው ከተቀጠሩ አንድ ዓመት ሊቆጠር ጥቂት ቀናት ነው የሚቀሩት። አሠልጣኙ የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ሲሰጡ ኢትዮጵያ የነበረ የስፖርት ጋዜጠኛ አነጋግረናል። በአዲስ ጉዳይ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በተለያዩ የሬዲዮ ዝግጅቶች በዋና አዘጋጅነት እና አዘጋጅነት ያገለግል የነበረው ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ አሠልጣኙ በተመለከተ በመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው «በዋነኛነት ሦስተ ነገሮችን አስቀምጠው ነበር» ብሏል። «ከነኚህ ሦስቱ ማሪያኖ ባሬቶ ያሳኩት አንዱን ብቻ ነው» ብሏል።

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ሳንወጣ ትናንት ደደቢት ቡድን ከናይጄሪያው ዎሪ ዎልፍስ ቡድን ጋር ባሕር ዳር ስታዲየም ባደረገው የመልስ ጨዋታ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በአጠቃላይ ድምር 2 ለዜሮ የተሸነፈው ደደቢት ቡድን ከማጣሪያው ወጥቷል።

ትናንት በስፔን ላሊጋ ግጥሚያ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ8 ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሐትሪክ የሠራ ሲሆን፤ ለቡድኑ ሪያል ማድሪድ በአጠቃላይ 5 ግቦችን አስቆጥሯል። ካሪም ቤንዜማ ኹለት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፤ የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ጋሬት ቤል ነበር። ዲዬጎ ማይንትስ በራሱ በግራናድ ላይ በስህተት አንድ ግብ አስቆጥሯል። ዘጠኝ ግቦች በተከታታይ የተቆጠሩበት ግራናዳ ቡድን ግራ ተጋብቶም ቢሆን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነችውን አንዲት ብቸኛ ግብ በሮቤርት ኢባኔትስ አስቆጥሯል። ሮናልዶ ሐትሪክ የሠራው ከ30 እስከ 38 ባሉት 8 ደቂቃዎች ውስጥ ነው።

ካሪም ቤንዜማ
ካሪም ቤንዜማምስል Senna/AFP/Getty Images

ትናንት ጌታፌ ዴፖርቲቮ ላኮሩኛን 2 ለ1 ረትቷል። ቫሌንሺያ ከቪላሪያል ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። መሪው ባርሴሎና ሴልታቪጎን 1 ለምን በመርታት ሦስት ተጨማሪ ነጥቦችን አግኝቷል። በዚህም መሠረት ባርሴሎና የደረጃ ሠንጠረዡን በ71 ነጥብ እየመራ ይገናል። ሪያል ማድሪድ በ67 ነጥብ ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ62 ይሠልሳል። ቫሌንሺያ 61 ነጥብ ይዞ ደረጃው አራተኛ ነው። ኮርዶባ በ18 ነጥብ የመጨረሻ 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በላሊጋው ትናንት ያስቆጠራቸው 5 ግቦቹ ተደምረውለት ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በ36 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል። የመሪው ባርሴሎና ሊዮኔል ሜሲ በ32 ግቦቹ ይከተለዋል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት ሔርታ ቤርሊን ፓዴርቦርንን 2 ለምን የረታ ሲሆን፤ አውስቡርግ ከሻልከ ያለምንም ግብ በመለያየት ነጥብ ተጋርተዋል። የደረጃ ሠንጠረዡን ከትናንት በስትያ ዶርትሙንድን 1 ለባዶ ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን በ67 ነጥብ በመምራት ላይ ይገኛል። ቮልፍስቡርግ በ57 ነጥብ ይከተላል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 50 ነጥብ አለው፤ ደረጃው ሦስተኛ ነው። 23 ነጥብ ያለው ሽቱትጋርት በ18ኛ ደረጃ መጨረሻ ላይ ይገኛል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ አኹንም 10ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፤ 33 ነጥብ አለው።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ
ቦሩስያ ዶርትሙንድምስል Lars Baron/Bongarts/Getty Images

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች ትናንት ሠንደርላንድ ኒውካስልን 1 ለ0 ሲያሸንፍ፤ በርንሌይ ከቶትንሐም ዜሮ ለዜሮ ተለያይቷል። ከትናንት በስትያ በርከት ያሉ ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ አርሰናል ሊቨርፑልን 4 ለ1 ኩም አድርጎታል። ማንቸስተር ዩናይትድ አስቶን ቪላን 3 ለ1 ሸኝቷል። መሪው ቸልሲ ስቶክ ሲቲን 2 ለ1 በሆነ ጠባብ ልዩነት አሸንፏል።

የደረጃ ሠንጠረዡን ቸልሲ በ70 ነጥብ ይመራል። አርሰናል 63 ነጥብ ይዞ ይከተላል። ማንቸስተር ዩናይትድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ 62 ነጥብ አለው። እንደ ቸልሲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ሲቲ በ61 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይስተር ሲቲ 22 ነጥብ ይዞ በ20ኛ ደረጃ መጨረሻ ላይ ይገኛል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ