የስፖርት ዘገባ፤ መጋቢት 7 ቀን፣ 2007 ዓ.ም
ሰኞ፣ መጋቢት 7 2007የጀርመኑን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ውጤት ቀዳሚ አድርገናል። ትናንት ፍራይቡርግን ሦስት ለባዶ የረታው ቮልፍስቡርግ በ53 ነጥቡ አሁንም የኹለተኛ ደረጃውን እንዳስጠበቀ ነው። ከትናንት በስትያ ቬርደር ብሬመንን በቀላሉ ለማሸነፍ የቻለው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ላይ ለመድረስ ግን ቮልፍስቡርግ 11 ነጥቦች ይቀሩታል።
ምንም እንኳን የቀድሞው ባላንጣው ቬርደር ብሬመን ራሱን አጠናክሮ ብቅ ቢልም ባየር ሙይንሽን ግን 25ኛውን የቡንደስ ሊጋ ፍልሚያ እንደለመደው በቀላሉ ነበር ያሸነፈው። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው ባየርን ሙይንሽን ያገኘውን ቅጣት ምት ዴቪድ አላባ በግሩም ሁናቴ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ባየርን ሙይንሽን ቬርደር ብሬመንን 4 ለዜሮ ያሸነፈው አሬየን ሮበንን እና ፍራንክ ሪቤሪን በጉዳት፣ እንዲሁም ዣቪ አሎንሶን በኹለት ቢጫ ቅጣት ማሰለፍ ባልቻለበት ሁኔታ ነው። ስፔናዊው የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ወሳኝ ተጨዋቾቻቸው ሳይኖሩም ብቃታቸውን አስመስክረዋል።
«በኹለተኛው አጋማሽ ለማጥቃት ሙከራ አድርገናል። ባየርኖች ጨዋታውን ለመቆጣጠር መቸገራቸው ታይቷል። እንደሚመስለኝ የባየርን ማሸነፍ ምንም ውይይት አያስፈልገውም። መተቸት ያለብን ራሳችንን ነው። እንዲያም ሆኖ የተጫወትነው በደረጃ ሠንጠረዡ አንደኛ ከሆነው፣ ከመሪው እና አሁንም የዋንጫ ባለቤት ከሚሆነው፣ የሻምፒዮንስ ሊግ ተስፈኛ ከሆነው ከባየር ሙይንሽን ጋር ነው። መሸነፋችንን ብዙም ማጋነን አያስፈልግም፤ ምክንያቱም የተቻለንን ሁሉ አድርገናል።»
ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ትናንት ሐኖቨርን 2 ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። በደረጃ ሠንጠረዡ ከቮልፍስቡርግ ዝቅ ብሎ በያዘው 44 ነጥብ ሦስተኛ ነው። ሆፈንሀይም ሐምቡርግን 3 ለዜሮ፣ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ፓዴርቦርንን በሰፊ ልዩነት 4 ለምንም እንዲሁም ማይንትስ አውስቡርግን 2 ለባዶ አሸንፈዋል። ሻልከ ከቤርሊን ጋር 2 እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ኮሎኝ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ዬይርገን ክሎፕ ብዙም ባይደሰቱም ውጤቱን ግን ተቀብለዋል።
«በሜዳህ ዜሮ ለዜሮ መውጣት፤ እውነቱን ለመናገር በጣም የሚያስደስት አይደለም። ሆኖም ካለንበት ሁኔታ አንፃር ውጤቱ ምንም አይደለም። በየሣምንቱ ከደረጃ ሠንጠረዡ ላለመውረድ ስለምናደርገው ፍልሚያ ለማውራት አሁን አንገደድም። ላለመውረድ ዛሬ ሌሎቹም ተጫውተዋል። ዛሬ ያገኘነው አንድ ነጥብ ድል ነው። ስለዚህ ያን እንቀበላለን»
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከወራጅ ቃጣናው ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ በማሸነፉ እና ትናንት ነጥብ በመጋራቱ አሁን የሚገኘው 10ኛ ደረጃ ላይ ነው።
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ቶትንሐም ሆትስፐርን 3 ለባዶ በሆነ ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ ደጋፊዎቹ በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ በአርሰናል ከደረሰባቸው ሽንፈት እንዲጽናኑ አድርጓል። ኤቨርተን ኒውካስልን 3 ለምንም ሸኝቷል። መሪው ቸልሲ በ6ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሳውዝሐምፕተን ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል።
ከትናንት በስትያ አርሰናል ዌስት ሐም ዩናይትድን 3 ለባዶ አሸንፏል። ማንቸስተር ሲቲ ባልተጠበቀ መልኩ በደረጃ ሠንጠረዡ 18ኛ ላይ በሚገኘው በበርንሌይ አንድ ለምንም ተረትቷል። ክሪስታል ፓላስ ክዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን 3 ለ1 ሲረታ፣ አስቶን ቪላ ሰንደርላንድን 4 ለባዶ አንኮታኩቶ በግብ ተንበሽብሿል። ዌስት ብሮሚች አልቢኖ ስቶክ ሲቲን 1 ለዜሮ በማሸነፍ ሦስት ነጥብ ሰብስቧል። ያለምንም ግብ የተለያዩት ሌስተር ሲቲ እና ሁል ሲቲ ነጥብ ተጋርተዋል።
በዚህም መሠረት ቸልሲ የደረጃ ሠንጠረዡን በ64 ነጥብ ይመራል። ማንቸስተር ሲቲ 58 ነጥብ ይዞ ይከተላል። አርሰናል በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በያዘው 57 ነጥቡ ሦስተኛ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ 56 ነጥብ አለው አራተኛ ነው። ሊቨርፑል 51 ነጥብ ይዞ በ5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እንደ ቸልሲ ሁሉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል።
የመኪና ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አሸናፊ ሆነ። ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ በመርሴዲስ ኹለተኛ ሆኗል። ሌላው የሀገሩ ልጅ ሰባስቲያን ፌትል በፌራሪ ተሽከርካሪው ሦስተኛ ወጥቷል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ዳኒኤል ሪካርዶ በስምነተኛነት ነው ያጠናቀቀው።
ውድድሩን «አሰልቺ» ሲሉ የገለጡት የሬድ ቡል ቡድን አማካሪ ሔልሙት ማርኮ አንዳንድ ሕግጋት ካልተቀየሩ በስተቀር ቡድናቸው ከፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድሙ ራሱን ሊያገል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ከመርሴዲስ ጋር መፎካከር ካልቻሉት ሌሎች ቡድኖች ጋር መከፋታቸውን የገለጡት ሬድ ቡሎች የሁሉም ቡድኖች ተሽከርካሪዎች የሞተር አቅም ተመጣጣኝ መሆን አለበት ሲሉ አማረዋል። መርሴዲስ በዘንድሮው የአውስትራሊያ ሽቅድምድም መክፈቻ እንደ ዓምናው ሁሉ አሸናፊ ለመሆን እምብዛም አልተቸገረም።
የብሪታንያው ተወላጅ ሊዎስ ሐሚልተን ትናንት አሸናፊ ከሆነ በኋላ ዋንጫውን ከፊልም ተዋንናዩ አርኖልድ ሸዋዚንገር እጅ ሲቀበል በቁመታቸው ቀልድ ብጤ ጣል ለማድረግ ሞክሯል። «ረዥም ትመስለኝ ነበር» አለ 1.74ሜትር ርዝመት ያለው የመኪና አሽከርካሪ ሌዊስ። 1.88ሜትር ርዝመት እንዳለው የሚነገርለት እውቁ ተዋናይ አርኖልድ ሸዋዚንገርም ለመልሱ አላመነታም። «አያይ፤ ታኮ ጫማዬን ስላላደረግኹ ነው» ፈጠን ሲል መልስ ሰጠ። ሌዊስ ሐሚልተን በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም አሸንፎ ዋንጫውን ከእውቁ የፊልም ተዋናይ እጅ በመቀበሉ ደስታ ከፊቱ ይነበብበት ነበር።
አጫጭር የስፖርት ዜናዎች
አውስትራሊያዊው የ23 ዓመቱ ወጣት ቡጢኛ ብራይደን ስሚዝ ከ10 ዙር ፍልሚያ በኋላ ለኹለት ቀናት ራሱን በመሳት ዛሬ ሐኪም ቤት ውስጥ መሞቱ ተዘግቧል። የሟቹ ቤተሰብ ቃል አቀባይ ጄምስ ኦሼ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ቅዳሜ ዕለት ከፊሊፒንሱ ጆን ሞራልድ ጋር ለእስያ ቡጢ ምክር ቤት የአህጉሩ ቀበቶ ሲፋለም አቅሉን ስቶ የሞተው ብራይደን በዩነቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ዲግሪውን ለማግኘት የሚማር የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ነበር።
ብራይደን አስሩን ዙር ከተፋለመና በዳኞች ውስሳኔ መሸነፉ ከተነገረው በኋላ ተጋጣሚው ሞራልዴን አቅፎ ሲጨብጥ በፈገግታ ነበር። ኹለቱም ተፋላሚዎች ፈገግ ቢሉም ገፃቸው በቡጢ በልዞ አባብጦ ታይቷል። ብራይደን ያገኘውን ሰው እየጨበጠ ወደ መልበሻው ክፍል ሲያቀና በግራ እጁ የያዘውን የፕላስቲክ ውኃ እየተጎነጨ በፈገግታ እንደተዋጠ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ታዲያ ራሱን ይስታል። ከዚያ በፊት ግን ንቁ እና ከተለመደ ባሕሪው ውጪ ያለማቋረጥ ያወራ ነበር ብሏል የቤተሰቡ ቃል አቀባይ።
በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ግጥሚያ ወደ ናይጀሪያ ያቀናው ደደቢት ቡድን በዎሪ ዎልቭስ የእግር ኳስ ቡድን ቅዳሜ ዕለት 2 ለ ዜሮ ተሸንፏል። ዎሪዎች የመጀመሪያውን ግብ በኦጌኔካሮ ኤቴቦ አማካኝነት ያስቆጠሩት ጨዋታው በተጀመረ በ5 ደቂቃ ውስጥ ነበር። ኹተኛውን ግብ ከመረብ ለማሳረፍ ግን እስከኹለተኛው አጋማሽ መጠበቅ ነበረባቸው። በኹለተኛው አጋማሽ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት በአግባቡ በመጠቀም ሣላሚ ባስቆጠራት ግብ ዎሪ ዎልቭስ አሸናፊ ለመሆን ችሏል።
የመልስ ጨዋታው በባህር ዳር ስታዲየም እሁድ መጋቢት 27 ቀን እንደሚከናወን ተጠቅሷል። የባህር ዳር ስታዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ውድድር ባስተናገደበት ወቅት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የስፖርት አፍቃሪያን ታድመው እንደነበር ይታወሳል።
የ18 ዓመቱ የአርሰናል ተሰላፊ ጌዲዮን ዘላለምን ከእግር ኳስ ማኅበር ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን (FIFA)ፍቃድ ከተሰጠው በቀጥታ የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እንደሚካተት ተገለጠ። ጀርመናዊው የዩናይትድ ስቴትስ አሠልጣኝ የርገን ክሊስንስማ ጌዲዮንን በዋናው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በቀጥታ ለማካተት ፍላጎታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ ፊፋ ሕግ ከሆነ አንድ ተጨዋች ለአንድ ሀገር ተሰልፎ መጫወት የሚችለው እድሜው 18 ዓመት ከሞላበት ጊዜ አንስቶ ለአምስት ዓመታት ለኖረበት ሀገር ነው ይላል። ይኽ ሕግ፦ ሃገራት ተጨዋቾችን ሙሉ ለሙሉ ከእግር ኳስ ጋር በተገናኘ ምክንያት ብቻ ዜግነት እንዳይሰጡ ለማከላከል የወጣ እንደሆነ ይጠቀሳል። የአርሰናሉ አማካይ ጌዲዮን ዘላለም ወደ ለንደን ከማቅናቱ በፊት እጎአ ከ2006 እስከ 2013 ድረስ ኑሮው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር። ገና ልጅ ሳለ ከወላጆቹ ጋር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀናው ጌዲዮን አመጣጡ ለትምህርት እንጂ ከእግር ኳስ ጋር በምንም አይነት ግንኙነት የለውም የሚል መከራከሪያም ቀርቧል።
የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የርገን ክሊንስማን ዓይናቸውን ጥምር ዜግነት ባላቸው ሌሎች ተጨዋቾችም ላይ አሳርፈዋል። ከእዚህም ባሻገር አሠልጣኙ ሜክሲኮ ውስጥ ለሚገኝ ቡድን የሚጫወተው ተከላካዩ ቬንቱራ አልቫርዶን እና የሊዮን ግብ ጠባቂው ዊሊያም ያርብሩንም በማካተት ቡድናቸውን ማጠናከር ይሻሉ።
ጀርመን በርሊን ከተማ ተወልዶ የጀርመን የወጣቶች ቡድውን ወስጥ በመሰለፍ የተጫወተው ጌዲዮን በወላጆቹ በኩል ለኢትዮጵያ ለመጫወትም ይፈቀድለት ነበር። ሆኖም የ18 ዓመቱ ጌዲዮን መጫወት የሚፈልገው ለዩናይትድ ስቴትስ መሆኑን ከገለጠ በኋላ ባለፈው ታኅሣሥ ወር የአሜሪካ ዜግነት ማግኘቱ ይታወቃል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተክሌ የኋላ