ስፖርት
ሰኞ፣ መስከረም 30 2009ከአፍሪቃ ናይጀሪያ ትናንት ዛምቢያን 2 ለ 1 በመርታት የቡድን የማጣሪያ ጨዋታዋን በድል ጀመራለች። ግብጽ ኮንጎን በሜዳው ብራዛቪል ውስጥ 2 ለ1 አሸንፏል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ኒኮ ሮዝበርግ በቀዳሚነት እየገሰገሰ ነው።
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአውሮጳ
እንግሊዝ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ነገ ከስሎቫኪያ ጋር ለምታደርገው ጨዋታ አምበሉ ዋይኔ ሩኒ አይሰለፍም። የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ በእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰላፊዎች መካከል እጅግ ከተሳካላቸው ተጨዋቾች ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደብ ነው። ሩኒ ለእንግሊዝ 117 ጊዜ በተሰለፈበት የቅዳሜው ጨዋታ ቡድኑ ማልታን 2 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ይኹንና የ30 ዓመቱ እንግሊዛዊ ከቅርብ ጊዜ አንስቶ አቋሙ እየወረደ በመምጣቱ ከፍተኛ ነቀፌታ እየቀረበበት ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያው የዌምብሌይ ታዳሚዎች በተቃውሞ ሲጮሁበት ተደምጠዋል። እንግሊዝ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከምትገንበት ምድብ በ6 ነጥብ እየመራች ትገኛለች።
በምድብ «ሐ »ም ጀርመን እስካሁን ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ እንደ እንግሊዝ 6 ነጥቦችን ሰብስባለች። ጀርመን ቀደም ሲል ኖርዌይን 3 ለ0 ከረታች በኋላ ቅዳሜ ዕለት ቼክ ሪፐብሊክን 3 ለባዶ በሆነ ልዩነት በጨዋታ በልጣ ማሸነፍ ችላለች። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከተጋጣሚው በጨዋታ ልቆ ተገኝቷል። ጀርመን ነገ ከሰሜን አየርላንድ ጋር ሦስተኛ ግጥሚያውን ያከናውናል።
በዚህ ግጥሚያ ላይ ብዙም የተጨዋች ለውጥ እንደማይኖር የጀርመን አሰልጣኝ ዮኣሒም ሎይቭ አስታውቀዋል። ዮኣሒም ሎይቭ ቼክ ሪፐብሊክን 3 ለ0 ከማሸነፋቸው አስቀድሞ እንዳስታወቁት በነገው ጨዋታ ከመጀመሪያው አንስቶ ኢካይ ጉይንዶዋንን አማካይ ቦታ ላይ እንደሚያሰልፉ በድጋሚ አስታውቀዋል። በነገው ጨዋታ ለኢካይ ጉይንዶዋን ቦታውን ሳሚ ኪዲራ ማስረከብ ግድ ይኾንበታል። ምናልባትም በነገው ጨዋታ የጀርመን ቡድን የአሰላለፍ ለውጥ የሚኖረው ይኽ ብቻ ይኾናል ማለት ነው።
ዛሬ ምሽቱን ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል በምድብ «ሀ» ፈረንሳይ ከኔዘርላንድ የምታደርገው በጉጉት ይጠበቃል። ሁለቱም የመጀመሪያ ጨዋታቸው ላይ ነጥብ ጥለዋል። ፈረንሳይ ከቤላሩስ ጋር ባደረገችው የመጀመሪያ ጨዋታ ያለምንም ግብ ነበር የተለያየችው። ኔዘርላንድ ከስዊድን ጋር አንድ እኩል ተለያይታ እንደ ፈረንሳይ ነጥብ ተጋርታለች። በሁለተኛ ጨዋታቸው ደግሞ ሁለቱም በተመሳሳይ የግብ ልዩነት ተጋጣሚዎቻቸውን 4 ለ1 መርታት ችለዋል። ፈረንሳይ ቡልጋርያን፤ ኔዘርላንድ ቤላሩስን 4 ለ1 የረቱት ዐርብ ዕለት ነበር። ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድ ተመሳሳይ አራት ነጥብ እና የግብ ልዩነት ሲኖራቸው ኔዘርላንድ ብዙ በማግባት አንደኛ ደረጃ ላይ ትገናለች። ስዊድን ከቡልጋሪያ እንዲሁም ሉክዘንቡርግ ከቤላሩስ ጋር ዛሬ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ከምድብ «ለ» ፖርቹጋል ፋራኦ ደሴቶችን፣ ላቲቪያ ሐንጋሪን፤ እንዲሁም የምድቡ መሪ ስዊትዘርላንድ አንዶራን ይገጥማሉ። ፖርቹጋልን በመጀመሪያ ጨዋታው 2 ለ0 እንዲሁም ሐንጋሪን 3 ለ2 የረታው የስዊትዘርላንድ ቡድን ከምድቡ ዝቅተኛ ግምት የተሰጣት አንዶራን በሰፊ የግብ ልዩነት እንደሚያሸንፍ ይጠበቃል። አንዶራ የመጀመሪያ ጨዋታዋን በላቲቪያ 1 ለ0 የተሸነፈች ሲሆን፤ ሁለተኛ ጨዋታዋን ግን ቅዳሜ ዕለት በፖርቹጋል በሰፋ ልዩነት ተሸንፋለች። ፖርቹጋል አንዶራን 6 ለባዶ በመሸኘት የጎል ጎተራ አድርጋታለች።
የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአፍሪቃ
ለዚሁ ከሁለት ዓመት በኋላ ሩስያ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ለመሳተፍ የአፍሪቃ ሃገራትም የማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን አከናውነዋል። ትናንት በተከናወኑ ጨዋታዎች ናይጀሪያ፣ ግብጽ እና ቱኒዚያ ማሸነፍ ችለዋል። አልጄሪያ ከካሜሩን ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርታለች። ከሜዳው ውጪ ጨዋታውን ያከናወነው የናይጀሪያ ቡድን ዛምቢያን ንዶላ ከተማ ውስጥ የረታው 2 ለ1 በሆነ ውጤት ነው።
አልጀሪያ ነጥብ በመጣሏም ናይጀሪያ ምድቡን እየመራ ይገኛል። በመጀመሪያው አጋማሽ ለናይጀሪያ ቡድን ሁለቱን ግቦች ያስቆጠሩት በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዝናቸው እየጨመረ የመጣ ሁለት ተጨዋቾች ናቸው። የአርሰናሉ አጥቂ አሌክስ ኢዎቢ የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው በ32ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኬሌቺ ኢሔናቾ ከ10 ደቂቃ በኋላ ሁለተኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ሁለቱም ቡድኖች ባደረጉት የንዶላው ፈጣን ጨዋታ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አምበል ጆን ሚኬል ኦቢ ሦስተኛ ግብ ልትሆን ትችል የነበረች ሙከራ አድርጓል። ኾኖም በዛምቢያው ግብ ጠባቂ ኬኔዲ ምዊኒ ግብ ከመሆን ድናለች። ዛምቢያ በሜዳው በባዶ ከመውጣት ያዳነችውን ግብ ያስቆጠረው በ71ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ዛምቢያዎች በዕለቱ ዕድል ቢጠምባቸውም ጫና ማድረግ ግን ችለዋል።
አልጀሪያ ከካሜሩን አንድ እኩል በተለያየችበት ጨዋታ የላይሰተር ሲቲው ሪያድ ማህሬዝ እና ኢስላም ስሊማኒን አሰልፋለች። ኾኖም የካሜሩኑ ቤንጃሚን ሙካንጆ የመጀሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ቡድኑን አቻ የምታደርገውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። ትናንት ግብጽ ኮንጎን በሜዳው ብራዛቪል ውስጥ ያሸነፈችው 2 ለ0 ነው። ቀደም ሲል ዐርብ እለት ጋና በሜዳው ከኡጋንዳ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ቱኒዚያ በሜዳዋ ሞናስቲር ውስጥ ትናንት ምሽት ጊኒን 2 ለ0 አሸንፋ ልካለች።
የመኪና ሽቅድምድም
በጃፓን ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ በመርሴዲስ ተሽከርካሪው አሸናፊ ኾኗል። በአጠቃላይ ነጥብም ቀዳሚ ነው። ኔዘርላንዳዊው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክ ፈርሽታፐን ሁለተኛ ሲወጣ፤ የሦስተኛ ደረጃ ያገኘው ደግሞ የብሪታንያው ሌዊስ ሐሚልተን ነው። የመርሴዲስ አሽከርካሪው ሌዊስ ሐሚልተን በአጠቃላይ ነጥብ ቀዳሚው ከኾነው ኒኮ ሮዝበርግ በ33 ነጥብ ይበለጣል። ኒኮ እስካሁን 313 ነጥቦችን ሰብስቧል።
የሜዳ ቴኒስ
የዓለማችን የቀድሞ ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች ራፋኤል ናዳል እና ሮጀር ፌዴሬር ከ13 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ምርጥ አራት ውጪ ኾኑ። የ30 ዓመቱ ስፔናዊው ራፋኤል ናዳል በዓለም የሜዳ ቴኒስ ደረጃ አምስተኛ ኾኗል። ስዊትዘርላንዳዊው ሮጀር ፌዴሬር ከስፔናዊው ሁለት ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ነው የሚገኘው። ሰርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች በአንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የብሪታንያው አንዲ ሙራይ ይከተለዋል። አራተኛ ደረጃን የተቆናጠጠው ጃፓናዊው ካይ ኒሺኮሪ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ