1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽግግር ሂደት በትግራይ፤ ተስፋና ስጋቶቹ

እሑድ፣ መጋቢት 24 2015

በሰላም ስምምነቱ መሰረት በትግራይ ጊዚያዊ የሽግግር መንግስት ተቋቁሙ ሁሉም የመንግስት መዋቅሮችን ሥራ ለማስጀመር የሚደረገው ጥረት ``ህወሐት አካታች ባልሆነ መልኩ ሽግግሩን የበላይ ሆኖ በሚመራበት መልኩ እያዋቀረው ነው`` የሚሉ ወቀሳና ትችቶች በተቃዋሚዎች ዘንድ አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/4PYX0
Kenia I Friedensabkommen von Pretoria
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የሽግግር ሂደት በትግራይ፤ ተስፋና ስጋቶቹ

በትግራይ ሃይሎችና በፌደራል መንግስት መካከል በተካሄደ ደም አፋሳሽ ውግያ በሚልዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ለሞት፣ መቁሰና መፈናቀል፤ የንብረት ውድመት ተዳርጓል።

የፌረራሉ መንግስትና ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት ) በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ ቡኋላ ውግያው ይደረግበት በነበረው አካባቢ አንጻራዊ ሰላም ቢሰፍንም ሕዝቡ አሁንም ከረሐብና ከችግር አልተላቀቀም። በሚልዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች  ገና ወደ መኖሪያ ቤታቸው አልተመለሱም፤ በትግራይ ትምህርት ቤቶች ስራ ባለመጀመራቸው ከ2.3 ሚልዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።

በሰላም ስምምነቱ መሰረት በትግራይ ጊዚያዊ የሽግግር መንግስት ተቋቁሙ ሁሉም የመንግስት መዋቅሮችን ሥራ ለማስጀመር የሚደረገው ጥረትም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች  ``ህወሐት አካታች ባልሆነ መልኩ ሽግግሩን የበላይ ሆኖ በሚመራበት መልኩ እያዋቀረው ነው`` የሚሉ ወቀሳና ትችቶች አስከትሏል።

የትግራይ ነጻነት ድርጅት (ውናት)፣ ሳልሳይ ወያነ (ሳወት) እና ታላቋ ትግራይ (ባይቶና ) የሽግግር መንግስቱን ለማቋቋም ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር ምንም አይነት ግኑኝነት እንደማይኖራቸው ገልጸው ነበር። ሰሞኑ ሳወትና ውናት ሁለቱም ድርጅቶች በጋራ ባወጡት የአቋም መግለጫ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕረዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ``የሚንጠባጠብ ሃይል አይኖርም።አካታች መንግስት እንመሰርታለን`` ማለታቸው ከኛ አቋም ጋር የሚስማማ በመሆኑ ተግባራዊ እንዲሆንና ሁሉንም አካታች መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ እናደርጋለን ብለዋል።

ገና ከጅምሩ ህወሐት በሩን ቀርቅሮ ካለምንም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ብቻውን የበላይ ሆኖ የሚመራው የሽግግር መንግስት እያቋቋመ ነው ከሚል ትችት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሽግግሩን ይመራሉ ተብለው በህወሐት የተሰየሙትን እስከ ማስቀየር ተደርሶ አሁን አቶ ጌታቸው ረዳ የሽግግር መንግስቱን እንዲመሩ ተሰይሟል።

ከጅምሩ ተቃውሞና የአካታችነት ጥያቄ ያልተለየው የትግራይ የሽግግር መንግስት ምስረታ ስጋትና የወደፊት ተስፋ የዛሬ የውይይታችን ርእስ ነው።

ተሳታፊዎቻችን

1.አቶ ወልደአብርሃ ንጉሰ ከትግራይ ነጻነት ፓርቲ በትግርኛ ምህጻሩ ውናት

2. አቶ ክንፈ ሐዱሽ ከሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሳወት

3. አቶ ተወልደ ተስፋይ ከትግራይ ዳያስፖራ ማሕበረሰብ ናቸው። 

 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር