1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

  የተመድ የኤርትራን የመሣሪያ ማዕቀብ አራዘመ

ዓርብ፣ ኅዳር 2 2009

የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት በኤርትራ እና በሶማሊያ ላይ ጥሎት የቆየዉን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ዳግም አራዘመ። ምክር ቤቱ ይህን ዉሳኔ ያሳለፈዉ ኤርትራ በየመን ጦርነት ያላት ሚናም ሆነ፣ የጅቡቲን የጦር ምርኮኞች በተመለከተ ያሳየችዉ ለዉጥ ስለሌለ እንደሆነ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/2SZmn
USA UN-Sicherheitsrat tagt in New York zu Syrien
ምስል Getty Images/AFP/D. Reuter

UN extends arms embargo on Eritrea - MP3-Stereo

       
 የፀጥታዉ ምክር ቤት በሶማሊያም ላይ በተመሳሳይ የጣለዉ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲራዘም ወስኗል። የሁለቱን ሃገራት ጉዳይ እንዲከታተል የተሰየመዉን ኮሚቴ ስልጣንም አራዝሟል። 
በተመድ ስምምነት ምዕራፍ 7 ሥር የተላለፈዉ ዉሳኔ 2317 በአስር የምክር ቤቱ አባል ሃገራት የድጋፍ ድምጽ ነዉ የፀናዉ። ቀሪዎቹ አምስቱ ማለትም አንጎላ፣ ቻይና፣ ግብፅ፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን እና ቬንዝዌላ ደግሞ ድምፀ ተአቅቦን መርጠዋል።በሶማሊያ  ጣልቃ ገብታለች  በሚል በሚል የዛሬ ሰባት ዓመት በኤርትራ ላይ የተጣለዉ የጦር መሣሪያ ማዕቀብን ለማራዘም በቂ መረጃ የለም የምትለዉ ቻይና ማዕቀቡ እንዲነሳ ግፊት ብታደርግም፤ ማዕቀቡ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ወስኗል። በአስመራ ላይ የመሣሪያ ማዕቀቡ የመቀጠሉ አስፈላጊነት ሲገለፅም፤ በተለይ በየመን ጦርነት ዉስጥ ባላት ሚና እና የጅቡቲን የጦር ምርኮኝ በተመለከተ መሆኑን አፅንኦት ሰጥቷል።  የፀጥታዉ ምክር ቤት በሶማሊያ ላይም ጥሎት የቆየዉን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ለአንድ ዓመት አራዝሟል። የተራዘመዉ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በአፍሪቃ ቀንድ አሁን በሚታየዉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምን ለዉጥ ሊያስከትል ይችላል? ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ኃላፊ ያኪ ሲሊየ የምክር ቤቱ ርምጃ  ከኤርትራ በኩል ለዉጥ ካልታየ ያን ያህል የሚያስከትለዉ ነገር እንደማይኖር ይናገራሉ።
«የጦር መሣሪያ እገዳዉ የተራዘመዉ በኤርትራና በሶማሊያ ላይ ነዉ። የፀጥታዉ ምክር ቤት አሸባብ ላስከተለዉ ስጋት ቁርጠኝነቱን ነዉ ያሳየዉ። ይህ በመሠረቱ የነበረዉን ማዕቀብ ነዉ ያራዘመ ነዉ። ይህ ደግሞ ከአልቃይዳ ጋር የተሳሰረዉ አሸባብ በሁለቱም ሃገራት እንደሚንቀሳቀስና ስጋትነቱም እንዳለ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል። ኤርትራ ከአካባቢዉ ራሷን ነጥላለች። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሶማሊያ ዉስጥ ያለዉን እየደገፈ ነዉ። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከኤርትራ መንግሥት በኩል የዝንባሌ ለዉጥ ይመጣል የሚል ተስፋ የያዘ ይመስለኛል። ያ ካልሆነና፤ ያ መኖሩንም የሚያሳይ ግልፅ መረጃ ካልኖረ የአሁኑ የተመድ የተለየ አቋም ይኖረዋል ብዬም አላስብም።»
በተመድ የኤርትራ ጉዳይ አስፈፃሚ አማኑዌል ጆርጂዮ የምክር ቤቱ ዉሳኔ በኤርትራ ላይ ዳግም የተፈፀመ ኢፍትሃዊነት ነዉ ሲሉ ተቃዉመዋል። እሳቸዉ እንደሚሉት ሀገራቸዉ ከአልቃይዳ ጋር ትስስር እንዳለዉ የሚነገርለት አሸባብን አትደግፍም የጅቡቲን የጦር ምርኮኞች በመልቀቅም ከሀገሪቱ ጋር ግንኙነቷን አድሳለች። ያም ሆኖ የመንግሥታቱ ድርጅት ትናንት ያፀናዉን ዉሳኔዉን በመጪዉ ሚያዝያ ወር የኤርትራና ሶማሊያን ጉዳይ የሚከታተለዉ ኮሚሽን የሚያቀርበዉን ዘገባ ተመልክቶ ዳግም ለመመርመር ቀጥሯል። ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸዉ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ኤርትራ ከአሸባብ ጋር መተባበሩን የሚያሳይ መረጃ ባልቀረበበት መድረክ ምክር ቤቱ ማዕቀቡን ማንሳት ነበረበት ነዉ የሚሉት።
«በትናንትናዉ ዕለት 15 ሃገራት ያቀረቡትን ዘገባ የተመለከትን እንደሆነ ኤርትራ ከአሸባብ ጋር ትተባበራለች የሚለዉ ሃሳብ ምንም ተጨባጭነት እንደሌለዉ አምነዉበታል። እንደዛ ከሆነ በኤርትራ ላይ የተጫነዉ እገዳ መነሳት ነዉ የነበረበት። ሆኖም ይህ ጉዳይ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሃገራት አሜሪካ እና ፈረንሳይን ጨምሮ ስለገፉበት እገዳዉ እንዲቀጥል ተወስኗል። እንደገና ከሶስት ወራት በኋላ ስለሚታይ አብረን የምንመለከተዉ ይሆናል።»
ምንም እንኳን የኤርትራ መንግሥት የሚቀርብበትን ክስ ቢያጣጥልም የመን ዉስጥ እጁን ያስገባ ብቸኛ ሀገር እንዳልሆነ ከእሱ የሚበልጡ ኃያል እና ትላልቅ ሃገራት በሰፊዉ እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ያኪ ሲልየ፤ እንዲህ ያለዉን እገዳ የመንግሥታቱ ድርጅት ሲያፀናም ያለምንም ምክንያት እንዳልሆነም አስረድተዋል። የመንግስታቱ ድርጅት ኤርትራ ላይ የጦር መሣሪያ እገዳዉን ከጣለ ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ጊዜ ዉስጥ ማዕቀቡ ለአካባቢዉ መረጋጋት ምን ያህል አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻል ይሆን? እንደገና ያኪ ሲሊየ።
«ማዕቀቦች እንደሚመስለኝ መልዕክት ያስተላልፋሉ እንጂ በራሳቸዉ የሚኖራቸዉ ርዳታ እጅግ ዉሱን ነዉ። በራሳቸዉ የሚለዉጡት ነገር የለም። የፀጥታዉ ምክር ቤት ከሚመለከተዉ ሀገር ጋር ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በጉዳዩ ላይ ክፉኛ እንዳሳሰበዉ መልዕክት የሚለዋወጥበት መንገድ ነዉ። ከማዕቀቡ በስተጀርባ መንቀሳቀሻ መንገዶች ምንጊዜም አሉ፤ የሚፈለገዉን መሣሪያ የሚቀርቡም ይኖራሉ። ያም ሆኖ ግን ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እንዲህ ያለዉ ሀገር በዓለም ደረጃ መነጠሉን የሚያመላክትበት ስልት ነዉ። የኤርትራ መንግሥት ይህን ቁብ ትሰጠዉ እንደሆነ እንጃ። በአካባቢዉ ላሉት እንደ ኢትዮጵያ ሱዳን፣ ዩጋንዳ እና ለመሳሰሉት ሃገራት ይህ ጠቃሚ ተምሳሌታዊ መልዕክት ነዉ። ኤርትራንም እንደ ኢጋድ እና የአፍሪቃ ኅብረት ካሉ የአካባቢዉ ተቋማት አግልሏታል።»
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ግን ኤርትራ የተነጠለች ሀገር አይደለችም ነዉ የሚሉት።
«በቅድሚያ ኤርትራ የተነጠለች ሀገር አይደለችም። ኤርትራ ከአሜሪካ እና ከአንዳንድ ሃገራት ጋር አለመግባባት ሊኖራት ይችላል። ይሄ ደግሞ ኤርትራ ፈልጋዉ ሳይሆን ጥቅማቸዉን ለማስከበር ሲሉ የሚገፉበት ጉዳይ ስለሆነ ነዉ። በተረፈ ኤርትራ ከአብዛኞቹ ሃገራት ጋር ጤናማ የሆነ የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት አላት።»
የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ኤርትራ ላይ ያራዘመዉ የጦር መሣሪያ እገዳ እንጂ ሌላ አጠቃል ማዕቀብ እንደልሆነ ተገልጿል። በትናንቱ ዉሳኔ ምክር ቤቱ አክሎም ኤርትራ እና ሶማሊያ ላይ የተጣለዉን የመሳሪያ እገዳ ተግባራዊነት እንዲከታተል የሰየመዉን ኮሚሽን ኃላፊነትም በተመሳሳይ አራዝሟል።  

Eritrea Architektur in Asmara
ምስል Reuters/T. Mukoya
Jakkie Cilliers Leiter Institut für Sicherheitsstudien in Pretoria
ያኪ ሲሊየምስል DW/T. Waldyes

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ