1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባባሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአውሮጳ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 14 2014

ጀርመንን ጨምሮ በአብዛኛው የአውሮጳ ሃገራት የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት ዳግም መጠናከሩን በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወቅት ከገባበት ካለፉት አራት ሳምንታት ወዲህ በተለይ በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ እያለ መሆዱም እየታየ ነው።

https://p.dw.com/p/43Nfy
Deutschland Leipzig | Coronakrise: n Intensivstation vom Universitätsklinikum Leipzig
ምስል Waltraud Grubitzsch/dpa/picture alliance

ኮቪድ 19 በጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ቤልጂግ

የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወራት ቅዝቃዜን ተከትሎ በጀርመን እና በሌሎች የአውሮጳ ሃገራት በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መበርከቱ እየተነገረ ነው። የጀርመኑ የተላላፊ በሽታዎች ምርምር ተቋም ሮበርት ኮኽ ዛሬ ይፋ ባደረገው መሠረት ባለፉት 24 ሰዓታት 45,326 አዲስ በተሐዋሲው ተይዘዋል።  ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መሆኑ በዓለም የጤና ድርጅት ከታወጀ አንስቶ እስከ ትናንት ድረስ በመላው ዓለም ከ256 ሚሊየን 966 ሺህ በላይ ሰዎች በተሐዋሲው መያዛቸውን ድርጅቱ መዝግቧል። ከ5,1 ሚሊየን በላይ ሰዎችም አልቀዋል። አሁንም በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በተለያዩ ሃገራት በየቀኑ እየጨመረ መሆኑ ይነገራል። 

የጀርመን ጎረቤት በሆነችው ኦስትሪያ ለ20 ቀናት የሚዘልቅ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል ግድ ብሏል የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት። ኦስትሪያ ከትናንት ጀምራ ተግባራዊ ባደረገችው ጥብቅ ገደብ መሠረት ዜጎች ከመኖሪያ ቤታቸው ለመውጣት የሚችሉት አንድም ለሥራ የግድ መውጣት ያለባቸው ከሆነ፣ ለሕክምና፣ ወይም ምግብ ለመግዛት እና አስቸኳይ ችግር ካጋጠመ ብቻ ይሆናል። በእነዚህ 20 ቀናትም ከምግብ ሸቀጣሸቀጥ መሸጫዎች እና ከመድኃኒት ቤቶች እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ መሸጫዎች ውጪ የንግድ ቦታዎች፣ ሆቴሎች እና ቡና ቤቶች እንዲሁም ቴያትር እና ፊል ቤቶች፤ የዋና እና ስፖርት ማዘውተሪያዎች ሁሉ ይዘጋሉ። ኦስትሪያ ጠንካራውን ርምጃ በመውሰድ ትለይ እንጂ ተሐዋሲው እንደአዲስ ስርጭቱ የተስፋፋባቸው ሌሎች የአውሮጳ ሃገራትም የጥንቃቄ ርምጃዎችን በማጠናከር ላይ ናቸው።

Deutscher Zukunftspreis 2021
ምስል Ansgar Pudenz/Deutscher Zukunftspreis

ኮሮና ተሐዋሲ በከፍተኛ ፍጥነት ዓለም ባዳረሰበት ወቅት ጀርመን ቀድማ በወሰደችው የጥንቃቄ ርምጃ ምክንያት ብዙ ዜጎቿ ባለመያዛቸው እና ለሞትም ባለመዳረጋቸው እንደምሳሌ ስትጠቀስ ነበር። ዛሬ ያ የተቀየረ መስሏል። ከዚህ ቀደም ባልታየ ፍጥነት ግዙፍ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ለኮቪድ 19 ክትባት ሲያዘጋጁም ባዮንቴክ እና ፋይዘር የተባሉት የጀርመን የመድኃኒት አምራቾች በቀዳሚነት እውቅና የተሰጣቸውን ክትባቶች አዘጋጁ። በአሁኑ ጊዜም ጀርመን ባጠቃላይ 70,6 በመቶ የሚሆኑ ኗሪዎቿ ቢያንስ የመጀመሪያውን ክትባት ሲወስዱ፣ 68 በመቶው ደግሞ ሁለቱንም ክትባት ወስደው አጠናቀዋል። አሁንም ግን ከክረምቱ ቅዝቃዜ ጋር በተገናኘ በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ያልተከተቡ እንዲከተቡ ግፊት ለማድረግ የተለያዩ መንገዶችን መጠቀም ተጀምሯል። ለምሳሌ በምግብ እና መጠጥ ቤቶች ገብቶ ለመስተናገድ፤ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ለመገኘት፣ በተለያዩ በርካታ ሰዎች በሚገኙባቸው ዝግጅቶች ለመሳተፍ መከተብ፤ ወይም በተሐዋሲው ተይዞ ማገገምን የሚያመላክት ወይም ተመርምሮ ከተሐዋሲው ነጻ መሆኑንን የሚያሳይ ማረጋገጫ ማቅረብ ያስፈልጋል።

Deutschland | Karnevalsauftakt in Köln
የክትባት መታወቂያምስል Henning Kaiser/dpa/picture alliance

በተለይ ባለፉት ሳምንታት ጀርመን ውስጥ በተሐዋሲው የሚያዙ ሰዎች ቁጥራቸው በመበራከቱ የጀርመን 16 ፌደራል ግዛቶች አስተዳዳሪዎች የጥንቃቄውን ርምጃ ለማጠናከር ሲመክሩ ሰንብተው ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል። ባለፉት ሰባት ቀናት በተሐዋሲው የተያዙት እና በዚህ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈው ወገኖች ቁጥር ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ መጨመሩም አነጋጋሪ ሆኗል። በአንዳንድ ፌደራል ግዛቶችም የጽኑ ሕሙማን መታከሚያ ክፍሎች ከአቅም በላይ ታማሚዎችን እያስተናገዱ እንደሆነም ነው የሚሰማው። 

በነገራችን ላይ የዓለም የጤና ድርጅት አውሮጳ ውስጥ አሁን የሚታየው የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭት በዚህ አያያዙ ከቀጠለ እስከ መጪው መጋቢት ወር መጀመሪያ ድረስ በዚህ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሚሊየን ሊበልጥ ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል። ከ53 የአውሮጳ ሃገራት በ49ኙ ሃኪም ቤቶች የጽኑ ሕሙማን ክፍሎች ከፍተኛ ጫና ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ከወዲሁ ጠቁሟል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ