የተፈናቃዮች ብዛትና የመረጃ እጥረት
ረቡዕ፣ ጥር 17 2015ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሰኔ 2013 እስከ ሰኔ 2014 በነበረዉ አንድ ዓመት የተደረጉ ግጭቶችና ድርቅ 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ከየቀየዉ መፈናቀሉን የሐገሪቱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።መንግስት የሚቆጣጠረዉ ኮሚሽን አክሎ እንዳለዉ ከተፈናቃዮቹ ግምሽ ያሕሉ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችና ሕፃናት ናቸዉ።ይሁንና ኢሰመኮ አክሎ እንዳስታወቀዉ በየአካባቢዉ ስለሚፈናቀለዉ ሕዝብ በቂ መረጃ ባለመጠናቀሩ ለችግር ለተጋለጠዉ ተፈናቃይ የሰብዓዊ ድጋፎችን ለማቅረብ እንቅፋት ሆኗል።
መንግሥት ተፈናቃዮችን ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት የተፈናቃዮችን ፍላጎት ፣ ከመፈናቀላቸው በፊት የነበራቸውን የአኗኗር ዘይቤ ፣ የአካባቢዎቹን የፀጥታ ሁኔታ በማረጋገጥ አለመሥራቱ ተፈናቃዮች በዘላቂነት እንዳይቋቃሙ ማድረጉ ተገልጿል።በኢትዮጵያ ውስጥ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመብቶቻቸው ሁኔታ አሳሳቢ ፈረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ከሰኔ 2013 እስከ 2014 ዓ. ም በስድስት ክልሎች እና በአንድ ከተማ መስተዳድር ውስጥ የሚኖሩ 1.5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች የነበሩባቸው 52 መጠለያ ጣቢያዎች እና ተቀባይ ማህበረሰቦች በምን ሁኔታ እንደሚገኙ መመልከቱን ገልጿል።
በዚህም በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአፋር ፣ በአማራ፣ እና በትግራይ ክልሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች መፈናቀላቸውን ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ ባዘጋጀውና ዛሬ በተከናወነ ውይይት ላይ ተገልጿል።
የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኝ አደመ በክልሉ ያለውን የመፈናቀል አደጋ በዚሁ ወቅት በዝርዝር አብራርተዋል።
የኦሮሚያ ክልል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን አቶ ማልቻ ሎጂ በክልሉ የትጥቅ ግጭት እና ድርቅ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሕዝብ ማፈናቀላቸውን ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ የክልሉ አንድ ሦስተኛ ሕዝብ ተፈናቃይ ከመሆኑ ባሻገር ከሁለቱ ሱዳኖች ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች መገኛ መሆናቸው የድጋፍ ሥራቸውን የበለጠ ፈታኝ እንዳደረገው ገልፀዋል።የተፈናቃዮች መብት እዲከበር ኢሰመኮ ጠየቀ
ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገሮች ውስጥ በ2021 400 ሚሊዮን ዜጎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ናቸው ያሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ
አብዛኛዎቹ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ናቸው ብለዋል።
"ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ በ2021 አምስት ሚሊዮን ይደርሳሉ ተብሎ ከተገመቱት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ውስጥ 3.6 ሚሊዮን ዜጎች በግጭት እና ብጥብጥ ምክንያት የተፈናቀሉ ናቸው። ይህ በአንድ ሀገር ላይ በአንድ ዓመት ተመዝግቦ የማያውቅ ነው።
ኢትዮጵያ ለተፈናቃዮች በቂ እቅድ ለመያዝ እና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የተጠናቀረ እና የተሰባጠረ የተፈናቃዮች መረጃ የላትም"የኢሰመኮ ዓመታዊ መግለጫ
ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ ለመብት ጥሰቶች መስፋፋት ምክንያት እየሆነ ነው የተባለውን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ቁጥር እና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ሰላምና ፀጥታን ያስከብር የሚለው ጉዳይ በስፋት ተነስቷል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ