1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና-አሜሪካ የንግድ ግብግብ

ረቡዕ፣ ጥር 1 2011

የከረረ እንካ ሰላንቲያቸውን ያቆሙት ቻይናና አሜሪካ በንግድ ግንኙነታቸው ኹኔታ ላይ እየተደራደሩ ነው። የምጣኔ-ሐብት ተንታኞች የንግድ ጦርነት እንዳያስነሳ ያሰጋቸው መካረር ከድርድሩ በኋላ መፍትሔ ይበጅለታል የሚል ተስፋ አላቸው። የሁለቱ ኃያላን እሰጥ አገባ በዓለም ንግድ ላይ ጭምር ጫና አሳድሯል። 

https://p.dw.com/p/3BG3T
Symbolbild USA-China-Handelskrieg
ምስል Colourbox

የቻይና-አሜሪካ የንግድ ግብግብ

ቻይና እና አሜሪካ የንግድ ግንኙነታቸውን መልክ ለማስያዝ ድርድር ተቀምጠዋል። እስካሁን ቻይና የአሜሪካን ሸቀጦች በምትሸምትበት ኹኔታ እና ገበያዋን ለአሜሪካ በምትከፍትበት መንገድ መግባባት ላይ ቢደርሱም ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ብዙ እንደሚቀራቸው ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ላለፉት ሁለት ቀናት በቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ የተደረገው ድርድር ዛሬም ይቀጥላል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደተለመደው በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ከቻይና ጋር የሚደረገው ድርድር በጥሩ ኹኔታ እየሔደ ነው" ሲሉ ፅፈዋል። ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው የቻይና ባለሥልጣን ሁለቱ አገሮች የደረሱበትን "ገንቢ" ብለውታል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ሁለቱን ኃያላን ባፋጠጠው የንግድ ውዝግብ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ አጥቂ የቻይናው አቻቸው ዢ ዢፒንግ በአንፃሩ ተከላካይ ሆነው ያታያሉ። 

ከመጋረጃ ጀርባ ያለው ድርድር ትክክለኛ ኹኔታ በይፋ ባይታወቅም ባለሥልጣኖቻቸው ግን ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቃል-አቀባይ ሉ ካንግ "ቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ አዎንታዊ እና ገንቢ ውይይት በማድረግ የሁለቱ አገሮች ፕሬዝደንቶች በተስማሙት መሠረት የገቡበትን የንግድ ቅራኔ ለመፍታት ተስማምተዋል" ብለው ነበር። 

China USA Donald Trump & Xi Jinping | Große Halle des Volkes
ምስል Reuters/D. Sagolj

የአሜሪካው የንግድ ምኒስትር ዊልበር ሮስ አሜሪካ ከቻይና አኳያ ያለባት የንግድ ሚዛን መጓደል እንዲስተካከል አጥብቀው ይሻሉ። ምኒስትሩ አሁን በቤጂንግ የተጀመረው ድርድር ውጤት ያመጣል የሚል ዕምነት አላቸው። ዊልበር ሮስ "ከድርድሩ አንዳች ውሳኔ እንጠብቃለን። ከዚህ በኋላ የሚኖረን የንግድ ግንኙነት በድርድር በሚወሰነው ይከወናል ወይስ እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዳችን በሌላችን ላይ ከፍተኛ ታሪፍ እየጣልን እንቀጥላለን የሚለው ይወሰናል። ስለዚህ የድርድሩ ውጤት መንታ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል። 

የቻይና እና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ንግድ ውጥረት ቀድሞም በዓለም ፖለቲካ የሚፎካከሩትን አገሮች ግንኙነት አክርሮታል። ሁለቱም ታዲያ በቤጂንግ የተጀመረው ውይይታቸው በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ በሚቀጥለው ወር በዋሽንግተን ለሚደረገው ድርድር በቂ እርምጃ አሳይቷል የሚል ተስፋ አላቸው። የቻይና ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል-አቀባይ ሉ ካንግ ቀድሞም ቢሆን አገራቸው በንግድ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር ወደ አተካሮ የመግባት ፍላጎት እንዳልነበራት ተናግረዋል። ሉ ካንግ "ቀድሞም የንግድ ውዝግብ ለቻይናም ሆነ ለአሜሪካ እንዲሁም ለዓለም ምጣኔ ሐብት ጠቀሜታ አይኖረውም የሚል አቋም ነበረን። ቻይና በመከባበር፣ በእኩልነት እና የጋራ ጥቅም ላይ በመመስረት የተፈጠረውን የንግድ ውጥረት ለመፍታት ዝግጁ ነች" ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ድርድሩ በጎ እርምጃ አሳይቷል ይባል እንጂ መፍትሔ ያልተበጀላቸው ልዩነቶች አሁንም በመካከላቸው ይታያሉ። ከእነዚህ መካከል የቻይና ኩባንያዎች እና የመንግሥቱ ባለሥልጣናት የአሜሪካ የሥራ አጋሮቻቸው ያለ ፍላጎታቸው ቴክኖሎጂዎቻቸውን ከማሻገር እንዴት መግታት ይቻላል የሚለው ይገኝበታል። ዊልበር ሮስ እንዳሉት አኩሪ አተር እና የተበጠበጠ የተፈጥሮ ጋዝ ግብይትን የመሳሰሉት ውስብስብ አይደሉም። ቻይና አብዝታ የምትታማበት የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነትን ማስከበር ግን አንገብጋቢው ጉዳይ ነው።  

ቻይና የአሜሪካን ቴክኖሎጂዎች ትሰርቃለች ወይም በገበያዋ የሚሰሩ የውጭ ኩባንያዎች አሳልፈው እንዲሰጡ ታስገድዳለች በማለት የሚወቅሱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሐምሌ ወር በቻይና ሸቀጦች ላይ የነበረውን የታሪፍ ክፍያ አሳድገው ነበር። ትረምፕ እንደ አውሮጳ፣ ጃፓን እና ሌሎች የንግድ አጋሮች ሁሉ ቻይና ገበያዋን ዝግ አድርጋለች የሚል ትችትም ያቀርባሉ። 

China Qingdao - Containerhafen
ምስል picture-alliance/dpa/Imaginechina/H. Jiajun

የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ ከቻይና በምትሸምታቸው 50 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል። ሌሎች 200 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦች 10 በመቶ ታሪፍ ተጭኖባቸዋል። ቤጂንግ በበኩሏ በተመሳሳይ እርምጃ ከአሜሪካ በ50 ቢሊዮን ዶላር በምትሸምታቸው ሸቀጦች ላይ 25 በመቶ ታሪፍ ጥላለች። ሌሎች 60 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሸቀጦችም በተመሳሳይ 10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ ተጭኖባቸዋል። 

ቻይና ወደ አገሯ የሚገቡ የቻይና ሸቀጦች የጉሙሩክ ሒደት አዘግይታለች ፋይናንስን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለአሜሪካ ኩባንያዎች ፈቃድ መስጠት አቁማለች እየተባለችም ትወቀሳለች። በአሜሪካ የሸማቾች ቴክኖሎጂ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጋሪ ሻፒሮ "ከአንድ ወር በፊት ከነበርንበት ኹኔታ ጋር ስናነፃፅረው አሁን በተሻለ ቦታ እንገኛለን። እስከ አዲሱ አመት መጀመሪያ 25 በመቶ ታሪፍ ተጭኖብን ነበር። አሁን ግን እስከ መጪው መጋቢት 1 ቀን ታሪፉ 10 በመቶ ብቻ ሆኖ ይቆያል። ኩባንያዎች የስራ ሁኔታቸውን ለማስተካከል ጊዜ ይሰጣል። በርካቶች እንዲያውም አጠናቀናል ብለዋል። ከቻይና በመውጣት ወደ ጎረቤት አገራት ሥራቸውን አዘዋውረዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

የሁለቱ አገሮች ኩባንያዎች ፋታ ያገኙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና የቻይናው አቻቸው ዢ ዢፒንግ በቡድን ሰባት አባል አገራት ስብሰባ ላይ በአርጀንቲናዋ የቦነስ አይረስ ከተማ ተገናኝተው ፋታ ለመውሰድ ከተስማሙ በኋላ ነበር። ሁለቱ መሪዎች ከአንድ ወር ገደማ በፊት ባደረጉት ውይይት አንዳቸው በሌላቸው ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ለ90 ቀናት ለማቆም ተስማምተው ነበር። እነዚህ ዘጠና ቀናት ግን ልዩነቶቻቸውን ጨርሶ ለመፍታት በቂ አለመሆናቸውን የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ያምናሉ። ትራምፕ በድንገት በቻይና ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታሪፍ ወደ መጣል እርምጃቸው እንዳይመለሱም ያሰጋቸዋል። ለዚህም ቻይና ፕሬዝዳንቱን ማባበል ይኖርባታል። ለምሳሌ አኩሪ አተር፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና ሌሎች የአሜሪካ ሸቀጦችን መሸመት መጀመር እንደ አማራጭ ሲቀርብ ይደመጣል። 

USA China - Handel - Kontainer
ምስል picture alliance/dpa/O.Spata

አተካሮው ግን በተለይ በቻይና ገበያ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ ለነበራቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች ራስ ምታት ሆኗል። ባይተን የተባለ የቅንጡ ተሽከርካሪዎች አምራች ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካርስተን ብራይትፌልድ ሁለቱ አገሮች በገቡበት የንግድ ውዝግብ ምክንያት ሥራቸው ፈተና ውስጥ ከወደቀባቸው አንዱ ናቸው። ብራይትፌልድ "ወደ ፊት ምን ሊፈጠር እንደሚችል አናውቅም። ሁለቱ ወገኖች የዓለም ንግድን ሳቢ እንደገና የሚያደርግ ትክክለኛ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይኸ ካልተሳካ አማራጭ አዘጋጅተናል። ቻይና ይገጣጠሙ የነበሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ደቡብ ኮሪያ ማዛወር አንዱ አማራጭ ነው። እንዲያውም ከደቡብ ኮሪያ ያለ ታሪፍ ወደ አሜሪካ ምርቶችን መላክ ይቻላል። በአሜሪካ መገጣጠምም ይቻላል" ሲሉ አማራጭ ፍለጋ የአካባቢውን አገራት ማማተር መጀመራቸውን ገልጸዋል። 

ባለፈው ግንቦት ወር የሁለቱ አገሮች ልዑካን ባደረጉት ድርድር አሜሪካውያኑ ድጎማ ማቆምን ጨምሮ ቻይና ማድረግ ይገባታል ያሉትን ጥያቄ አቅርበዋል። አሜሪካ ካቀረበቻቸው ጥያቄዎች ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት አሁኑኑ መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚችል ቻይና ምላሽ መስጠቷን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል። ቀሪው ከ30 እስከ 40 በመቶ ወደ ፊት ድርድር ሊደረግባቸው እንደሚችል ቻይና የገለጸች ሲሆን ቀሪውን ፈፅሞ ማለቷ ተሰምቷል። 

ሲኔት የተባለው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሮገር ቼንግ ግን የቻይና እና የአሜሪካ ፉክክር ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘቱ እርግጠኛ አይደሉም።  ቼንግ "በቴክኖሎጂ የበላይነቱን ለማግኘት ለከርሞው የበለጠ ፍልሚያ ይደረጋል። ቻይና በ5G የኢንተርኔት አገልግሎት እና በአርቴፊሺያል ኢንተለጀንስ በልጦ ለመገኘት ብዙ ገንዘብ ወጪ አድርጋለች። በዚህ ረገድ ቀዳሚ መሆን ይፈልጋሉ" ሲሉ ሁለቱ አገሮች አሁን የፈተናቸውን ልዩነት ቢፈቱት እንኳ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ያስረዳሉ።

እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ