የኅዳር 19 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ኅዳር 19 2015በቀተር የዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ቤልጂዬምን አስተማማኝ በሆነ መልኩ 2 ለ0 ድል በማድረግ ኃያል ቡድን መሆኑን አስመስክሯል። የትናንቱ የቤልጂየም ሽንፈት ያበሳጫቸው ደጋፊዎች ባስነሱት ሁከት የቤልጂየም እና ሆላንድ ከተሞች ትናንት ሲናጡ አምሽተዋል። በዛሬ ግጥሚያ ደግሞ የግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ድክመት የታየበት የካሜሩን ቡድን ከሠርቢያ ጋር ገጥሞ አቻ ወጥቷል። ጋና ተጋጣሚዋ ደቡብ ኮሪያን 3 ለ2 አሸንፋ እንደ ሞሮኮ የማለፍ ዕድሏን አስፍታለች። ቱኒዝያ ከምድቧ መጨረሻ ሆና በአንድ ነጥቧ ተወስናለች። የመጨረሻ ግጥሚኢዋን የምታደርገው ከጠንካራው የፈረንሳይ ቡድን ጋር በመሆኑ የመሰናበቷ ነገር ከወዲሁ ባይቋጭም ዕድሏ ግን እጅግ የጠበበ ነው። በሌሎች ምድቦች ጃፓን ባልተጠበቀ መልኩ በኮስታሪካ መሸነፉ እንደሚሰናበት አረጋግጦ ተስፋ የቆረጠው የጀርመን ቡድን እንዲያንሰራራ አድርጓል።
የዓለም ዋንጫ
የቀተር የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ በርካታ ያልተጠበቁ ክስተቶችን እያስተናገደ ነው። የደቡብ ኮሪያው አሰልጣኝ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ከመሀል ዳኛው ጋር በባከነ ሰአት ጉዳይ ውዝግብ በመፍጠራቸው የቀይ ካርድ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ጨዋታ ጋና ደቡብ ኮሪያን 3 ለ2 አሸንፋ 3 ነጥብ አግኝታለች። ደቡብ ኮሪያ በአንድ ነጥብ ከምድቡ መጨረሻ ላይ ትገኛለች። 3 ነጥብ ይዛ ምድቡን የምትመራው ፖርቹጋል 1 ነጥብ ካላት ኡራጋይ ጋር ይጫወታሉ። በበርካቶች ዘንድ የሚጠበቁት ብራዚል እና ስዊትዘርላንድ እየተጋጠሙ ነው።
ዛሬ በነበረ ሌላ ግጥሚያ ካሜሩን ከሠርቢያ ጋር ሦስት እኩል ተለያይቷል። የካሜሩን እና ሠርቢያ ጨዋታ ዛሬ ኧል ጃኑብ ስታዲየም ውስጥ 3 ለ3 እንደተጠናቀቀ ስለጨዋታው እንዲነግረን የሃትሪክ የስፖርት ጋዜጣ ባለቤት እና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ይስሐቅ በላይን በስልክ አነጋግሬው ነበር። በካሜሩን እና ሠርቢያ ግጥሚያ በእርግጥ 29ኛ ደቂቃ ላይ በዦን ሻርል ካስቴሌቶ በኩል ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረችው ካሜሩን ነበረች። ሆኖም የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ 45 ደቂቃ ተገባዶ በባከኑ ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ካሜሩን ላይ ሁለት ግቦች በተከታታይ ተቆጥረዋል።
በ46ኛው ደቂቃ በስትራሂንያ ፓቭሎቪች በኩል ካሜሩን ላይ የተቆጠረባት የመጀመሪያ ግብ በግብ ጠባቂ ስህተት ነው። ግብ ጠባቂው ከግቡ አቅራቢያ እንደወጣ ኳሱን በቡጢ ጠልዞ ማውጣት ነበረበት። አለበለዚያ ከግብ ክልሉ ላይ ሆኖ ኳሷን ለማጨናገፍ መጣር ይገባው ነበር። ሠርጌይ ሚሊንኮቪች-ሣቪች 48ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ሁለተኛውም ግብ ቢሆን የተከላካይ ስህተት ነው። የካሜሩን ተጨዋች ፍጹም ቅጣት ምት ክልል አቅራቢያ ሆኖ ኳሷን ከማሽሞንሞን ይልቅ በፍጥነት ከግብ ክልል ማስወጣት ነበረበት። ያን ባለማድረጉ የሰርቢያ ሳተና ተጨዋቾች ኳሷን ቀምተው ለውጤት አብቅተዋል። ሦስተኛው ግብ በአሌክሳንደር ሚትሮቪች በቀላሉ ከመቆጠሩ አንጻር በልምምድ ወቅት እንደሚታየው መሀል ባልገባ አይነትም ይመስል ነበር። በአጠቃላይ በዛሬው ጨዋታ የካሜሩን ቡድን እጅግ ደካማ መከላከል ታይቶበታል። ግብ ጠባቂውም ደካማ ነበር። ይስሐቅ ከግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ባሻገር መሀሉም ልክ አልነበረም ብሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጨዋታው ተቀይሮ ካሜሩን ጠንካራ ሆኗል። ለዚያ ደግሞ በአፍሪቃ ዋንጫ ላይ ድንቅ ብቃቱን ያየንለት አጥቂ ቪንሰንት አቡባከር ተቀይሮ መግባቱ ያመጣው ነው። አቡባከር 63ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል፤ 66ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ለኤሪክ ማክሲም ቼፖ ሞቴንግ አመቻችቶ በማቀበል ግብ እንዲቆጠር አስችሏል። የካሜሩን አሰልጣኝ ቪንሰንት አቡባከርን በመጀመሪያው አጋማሽ ተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠው መቆየታቸውንም፦ «የአሰልጣኙን ውሳኔ ተጋፋ አልባል እንጂ ትክክል አይደለም» ብሏል።
በነገራችን ላይ ከ12 ዓመት በፊት ሁለቱ ቡድኖች ለወዳጅነት ባደረጉት ግጥሚያ ሠርቢያ ካሜሩንን 4 ለ3 አሸንፋ ነበር። አንተ ወደ ቀተር ሄደህ ዐርብ ዕለት የሚደረገውን የካሜሩን እና ብራዚል ጨዋታን ጨምሮ ሌሎች ጨዋታዎችንም ከቦታው በቀጥታ ልትመለከት ነው? የብራዚል ፈጣን እና የኳስ ጥበብ የተካኑ አጥቂዎች በካሜሩን ደካማ ተከላካዮች የሚቆሙ «አይመስለኝምምም» ብሏል።
ይስሐቅ በላይ ከቀተር ደግሞ ስታዲከም ገብቶ በቀጥታ የተመለከተውን ለአድማጮቻችን ያቀርብልናል። ሳምንት ጠብቁት።
ከዚሁ ከዓለም ዋንጫ ሳንወጣ፦ ሞሮኮ በአስደማሚ ብቃት ቤልጂየምን ትናንት ኧል ቱማማ ስታዲየም ውስጥ 2 ለ0 ድል ማድሯጓ በሞሮኮ ደጋፊዎች ዘንድ ፌሽታን ሲፈጥር የቤልጂየም ደጋፊዎችን እጅግ አበሳጭቷል። ኢንዲፔንደንት የተባለው የድረገጽ ጋዜጣ እንደዘገበው የቤልጂየም በሞሮኮ መሸነፍ ያበሳጫቸው የቤልጂየም ደጋፊዎች አደባባይ በመውጣት ቁጣቸውን ተሽከርካሪዎችን በማቃጠል እና ድንጋይ በመወርወር ገልጠዋል። ደስታቸውን ለመግለጥ የወጡ የሞሮኮ ደጋፊዎችን የሚያውኩ ድርጊቶች ተከስቶም ሁኔታው ወደ ኹከት ተቀይሯል። ፖሊስ በዐሥራዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ አንድ ሰው ማሰሩንም ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል።
የቤልጂየም ዋና ከተማ ብራስልስ ከንቲባ ፊሊፕ ክሎዝ ኹከት ፈጣሪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ፖሊስም በከፍተኛ ደረጃ ጎዳናዎችን እንዲያስጠብቅ ትእዛዝ እንደተሰጠው ተናግረዋል። ስለ ኹከተኞቹ ሲናገሩም፦ «እነሱ ኳስ ደጋፊዎች አይደሉም፤ ኹከተኞች እንጂ። የሞሮኮ ደጋፊዎች እዚያ የነበሩት ድላቸውን ለማክበር ነበር» ብለዋል። ከቤልጂየም ባሻገር የኔዘርላንድ ዋና ከተማ አምስተርዳም፣ ዘ ሔግ እና ሮተርዳምን በመሳሰሉ ከተሞች ብጥብጥ እንደነበር ተዘግቧል። የቤልጂየም ጨምሮ በተጠቀሱት ከተሞች የሚኖሩ ከሰሜን አፍሪቃ የፈለሱ ሰዎች በተለይ ከሀገሬው ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ጋር የቆዩ የፖለቲካ ቁርሾዎች ውስጥ የገቡ መሆናቸው ይታወቃል።
ነገ ከሚኖሩ ጨዋታዎች መካከል የዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን ጨዋታ ከእግር ኳሱም ባሻገር በበርካቶች ዘንድ የሚጠበቅ ነው። ኢራን የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን ከዓለም ዋንጫ እንዲሰናበት ጥሪ አስተላልፋለች። የዩናይትድ ስቴትስ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢራን ተቃዋሚዎችን ለመደገፍ ሲል ትክክለኛ ሠንደቅ ዓላማዬን ቀይሮ ሌላ ባንዲራ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ለጥፏል ስትል ነው ቡድኑ እንዲባረር የጠየቀችው። የሁለቱ ሃገራት ግጥሚያ ከእግር ኳስም ባሻገር በፖለቲካ የተተበተበ መሆኑ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል።
ትናንት ከነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች መካከል ጃፖን ባልተጠበቀ መልኩ በኮስታሪካ 1 ለ0 ተሸንፋለች። ይህ ውጤት አበቃለት የተባለው የጀርመን ቡድን ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጎታል። ጀርመን ትናንት ከስፔን ቡድን ጋር አንድ እኩል ተለያይቶ አንድ ነጥብ ተጋርቷል። የትናንቱን የስፔን እና ጀርመን ግጥሚያ ጀርመን ውስጥ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቴሌቪዥን ተከታትለውታል። ቁጥሩ በጀርመን የቴሌቪዥን ኮታ ባለፉት 11 ወራት ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ከተመዘገበባቸው ዝግጅቶች መካከል ሁለተኛው ተብሎለታል። በጎርጎሪዮሱ 2022 ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበበት ዝግጅት የሴቶች የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ የፍጻሜ ግጥሚያ ነበር። በወቅቱ 17,9 ሚሊዮን ሰዎች ጨዋታውን በቴሌቪዥን ተከታትለውታል።
በትናንቱ ውጤት መሰረት የጀርመን ቡድን 1 ነጥብ ብቻ ይዞ በምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ቢገኝም በዓለም ዋንጫ የመቆየቱ ጉዳይ በቀጣይ 3 ነጥብ ካለው ኮስታሪካ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ውጤት ይወስናል። በምድቡ ጃፕን 3 ነጥብ ይዞ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ምድቡን ስፔን በ4 ነጥብ ይመራል። የጀርመን ቡድን ደጋፊዎች እና ጋዜጠኞች ቡድናቸው ኮስታሪካን እንደሚያሸንፍ ከወዲሁ በእርግጠንነት እየተናገሩ ነው። ፍራቻቸው ጃፓን በስፔን ይሸነፋል ወይ የሚለው ነው። ጃፓን ከስፔን ጋር አቻ ከወጣ ጀርመን ለማለፍ ኮስታሪካን በ2 ግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ጃፓን ካሸነፈ ግን ጀርመን ስፔንን በልጦ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ኮስታሪካን ከ7 ግብ ልዩነት በላይ ሊያሸንፍ ይገባዋል። ያም በመሆኑ ሐሙስ ማታ በተመሳሳይ ሰአት የሚደረጉት የጀርመን ከኮስታሪካ እና የጃፓን ከስፔን ግጥሚያዎች ከወዲሁ አጓጊ ሆነዋል። ጀርመን ዘንድሮም እንደ ሩስያው የዓለም ዋንጫ ገና ከማለዳው እንዳይሰናበት በብዙዎች ዘንድ ስጋት አጭሯል።
በትናንቱ ግጥሚያ ግን አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ሦስቱንም ወሳኝ አማካዮቻቸውን አሰልፈው የጨዋታ መስመሩን መቀያየራቸው ከሽንፈት አድኗቸዋል። በኒክላስ ፉይልክሩግ ብቸኛ ግብም የጀርመን ቡድን ተስፋ በደብዛዛውም ቢሆን እንዲያጨለጭል አድርገዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ