1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የነሐሴ 24 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ነሐሴ 24 2013

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው በግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ክብረወሰን ሰብራለች። በወዳጅነት የእግር ኳስ ግጥሚያ ኢትዮጵያ ዩጋንዳን 2 ለ1 አሸንፋለች። በጃፓን ፓራሊምፒክ ጀርመን የመጀመሪያውን ወርቅ በትሪያትሎን አግኝቷል። ሊዮኔል ሜሲ ለፓሪ ሳንጃርሞ የመጀመሪያ ግጥሚያውን አከናወነ። በትናንቱ ግጥሚያ እምባፔ ኮከብ ኾኖ አምሽቷል።

https://p.dw.com/p/3zg2k
Frankreich Francien Niyonsaba und Ejigayehu Taye
ምስል Haimanot Tiruneh/DW

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው በግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር አየርላንድ ውስጥ ክብረወሰን ሰብራለች። በወንዶች ፉክክርም ድሉ የኢትዮጵያ ነበር። በወዳጅነት የእግር ኳስ ግጥሚያ ኢትዮጵያ ዩጋንዳን 2 ለ1 አሸንፋለች። በጃፓን ፓራሊምፒክ የአካል ጉዳተኞች የስፖርት ውድድር ጀርመን የመጀመሪያውን ወርቅ ትናንት በትሪያትሎን አግኝቷል። በጠረጴዛ ቴንስም ወርቅ ቀንቶታል። ሊዮኔል ሜሲ ለፓሪ ሳንጃርሞ ከፈረመ ከ19 ቀናት በኋላ ትናንት የመጀመሪያ ግጥሚያውን አከናውኗ። በትናንቱ ግጥሚያ እምባፔ ኮከብ ኾኖ አምሽቷል። ቸልሲ በ10 ተጨዋቾች አንፊልድ ላይ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። አርሰናል በማንቸስተር ሲቲ ተንኮታኮቷል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ግብ አዳኙ ሮቤርት ሌኛንዶቭስኪ ላይ የሚደርስበት አልተገኘም። ትናንት ሔትትሪክ ሠርቶ ለቶማስ ሙይለርም ግብ አመቻችቷል። 

Tokyo 2020 Paralympics-Hingucker/30.08.2021
ምስል Athit Perawongmetha/REUTERS

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው አየርላንድ ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ትናንት ክብረወሰን ሰብራለች። በርቀቱ ተይዞ የቆየውን ሰአት ከ64 ደቂቃ በማውረድ ነው የዓለምዘርፍ ክብረወሰን ያስመዘገበችው። ቀደም ሲል ክብረወሰኑ በኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች 64 ደቂቃ ከ02 ሠከንድ የተያዘ ነበር። የዓለምዘርፍ የግማሽ ማራቶኑን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 63:43 ደቂቃ ነው። ከውድድሩ በኋላም በሰጠችው ቃለ መጠይቅ «ሕልሜ ዕውን ኾኗል» በማለት በሕይወቷ ሙሉ የለፋችበትን ፍሬ በማየቷ ደስታዋን ገልጣለች።

አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው በጃፓን ቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳታፊ አልነበረችም። በወቅቱ ሔንጌሎ ውስጥ በነበረው የ10,000 ሜትር የማጣሪያ ውድድር 30:20.77 በመሮጥ በአራተኛነት ነበር ያጠናቀቀችው። ይህ እንደ ኦሎምፒክ ላሉ ወሳኝ ውድድሮች ለመታጨት ወቅታዊ የአትሌቶች ብቃት ላይ ብቻ መመስረት የሚኖረውን ተፅዕኖ ያመላክታል። ምናልባትም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ ነው። አየርላንድ ውስጥ በተከናወነው የግማሽ ማራቶን የወንዶች ፉክክርም ጀማል ይመር በአንድ ሰዓት ከ29 ሰከንዶች በመሮጥ አንደኛ ወጥቷል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ተስፋሁን አካልነው በአንድ ሰከንድ ብቻ በመዘግየት ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል። የኬንያው ሻድራክ ኪሚኒንግ ከውድድሩ አሸናፊ ጀማል በሁለት ሰከንዶች ብቻ ዘግይቶ ሦስተኛ ወጥቷል።

ፓሪስ ከተማ ሻርሌ ስታዲየም ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነው የፓሪስ ዲያመንድ ሊግ ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሁለተኛ እና የአምስተኛ ደረጃ አግኝተዋል። አትሌት እጅጋየሁ ታየ በሦስት ሺሕ ሜትር በተደረገ ውድድር ሁለተኛ በመውጣት አጠናቃለች። አትሌት ፋንቱ ወርቁ የአምስተኛ ደረጃን አግንታለች። ውድድሩን ክብረወሰን በመስበር በበላይነት ያጠናቀቀችው የቡሩንዲዋ ፍራንሲን ንዮንሳባ ነች። 

Tokyo 2020 Olympics - Tag 7
ምስል Martin Rickett/empics/picture alliance

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና፦ ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ በተካኼደው የፓራሊምፒክ የ1,500 ሜትር የሴቶች የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት ገዛኸኝ አሸናፊ ሆናለች። ትዕግስት በፓራሊምፒክ ውድድር ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ በማስገኘት የመጀመሪያዋ አትሌት ናት። በተያያዘ ዜና፦ በፓራሊምፒክ ውድድር ጀርመን የመጀመሪያውን ወርቅ ትናንት በትሪያትሎን ወስዷል። በጠረጴዛ ቴንስም ትናንት ወርቅ ሲያገኝ፤ በ100 ሜትር ዝላይ ደግሞ ዛሬ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል።  

እግር ኳስ

ወደ እግር ኳስ ዜና ስንሻገር ደግሞ፦ ኢትዮጵያ ዩጋንዳን ትናንት በወዳጅነት ግጥሚያ 2 ለ1 አሸነፋለች። ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ የመጀመሪያ ግጥሚያዋን የፊታችን ዐርብ ማታ ከጋና ጋር ታከናውናለች። አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከአንጎላ ጋር የምትገጥመው ግብፅ ወሳኝ አጥቂ የሊቨርፑሉ ሞሐመድ ሣላኅ እንደማይሰለፍ ተገልጧል። ሞ ሣላኅ የማይሰለፈው እንግሊዝ ውስጥ ባለው የኮሮና ተሐዋሲ የጉዞ ገደብ የተነሳ ነው። ግብጽ በኮሮና የተነሳ በብሪታንያ የጉዞ «ቀይ መዝገብ» ውስጥ ትገኛለች። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) እና የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንሥትር ቦሪስ ጆንሰን የአፍሪቃ ተጨዋቾችን ለጉዞ እንዲፈቅዱ ያቀረቡት ማመልከቻ አለመሳካቱም ተዘግቧል።

ግብፃዊው አጥቂ ሞ ሣላኅ ቡድኑ ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በሜዳው አንፊልድ ከቸልሲ ጋር በነበረው ግጥሚያ አቻ የምታደርገውን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል። በዕለቱ ግጥሚያ የቸልሲው ሪቼ ጄምስ ግብ የምትኾን ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ ማጠናቀቂያ ላይ በእጁ በማውጣቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ሞ ሣላኅ ከመረብ ያሳረፈው የተገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት በመምታት ነው። ከእረፍት መልስ የቸልሲው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኅል በአብዛኛው በመከላከል ላይ የተመሰረተ ጨዋታቸው ሊቨርፑልን በሜዳው እንዳያሸንፍ አድርጎታል።

UEFA Champions League Finale | Tottenham Hotspur v FC Liverpool Mo Salah
ምስል AFP/G. Bouys

በሌሎች ጨዋታዎች፦ ማንቸስተር ሲቲ አርሰናልን 5 ለ0 በኾነ ሰፊ ልዩነት አንገት አስደፍቷል። አርሰናል እስካሁን ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ተሸንፎ 9 የግብ እዳ አለበት። ገና ሦስተኛ ዙር ጨዋታ ቢሆንም አርሰናል እንደኖርዊች ሲቲ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ለመስፈር ተገዷል። አስቶን ቪላ ከብሬንትፎርድ ጋር አንድ እኩል ሲወጣ፤ ኒውካስትል ዩናይትድ ከሳውዝሐምፕተን እንዲሁም ዌስትብሮሚች ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ ጋር ሁለት እኩል ተለያይተዋል። ኤቨርተን ብራይተንን 2 ለ0፤ ላይስተር ሲቲ ደግሞ ኖርዊች ሲቲን 2 ለ1 አሸንፈዋል።

ትናንት በተደረጉ ሦስት ግጥሚያዎች በርንሌይ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ቶትንሀም ሆትስፐር ዋትፎርድን እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ዎልቨርሀምፕተንን አንድ ለዜሮ ድል አድርገዋል። ቶትንሀም በትናንቷ ብቸኛ ግብ ነጥቡን 9 አድርሶ በመሪነት ተኮፍሷል። ዌስትሀም፤ ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ቸልሲ እና ሊቨርፑል በተመሳሳይ 7 ነጥብ፤ አምስት የግብ ክፍያ እና አንድ የግብ እዳ እኩል ደረጃ ይዘዋል። ተመሳሳይ 7 ነጥብ ያለው ኤቨርተን ከሌሎቹ በአንድ የግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ውድድር ደግሞ፦ ባየር ሙይንሽን ሔርታ ቤርሊንን በሰፋ የግብ ልዩነት 5 ለ0 አንኮታኩቷል። ሙይንሽን አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ውስጥ በ25,000 ተመልካች ፊት በተከናወነው ግጥሚያ ቀዳሚዋን ግብ 6ኛው ደቂቃ ላይ ለቶማስ ሙይለር ያመቻቸው ግብ አዳኙ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ነው። በቅዳሜው ግጥሚያ ፖላንዳዊው አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ሦስት ግቦችን አከታትሎ በማስግባት ሔትትሪክ ሠርቷል። ታዳጊው ጃማል ሙሳይላም 49ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ግብ አስቆጥሯል።

Fußball Bundesliga Robert Lewandowski
ምስል Matthias Schrader/AP Photo/picture alliance

ቮልፍስቡርግ ላይፕትሲሽን 1 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በዑኒዮን ቤርሊን የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ፍራይቡርግ ሽቱትጋርትን 3 ለ2፤ ማይንትስ ግሮይተር ፊዩርትን 3 ለምንም አሸንፈዋል።  አውግስቡርግ በባየርን ሌቨርኩሰን የ4 ለ1 ሽንፈት ሲገጥመው፤ ኮይልን ቦኹምን ኮይልን ከተማ በሚገኘው ራይን ኢነርጂ ስታዲየም ውስጥ 2 ለ1 ረትቷል። አርሚኒያ ቢሌፌልድ ከፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል ወጥቷል። ዶርትሙንድ ሆፈንሃይምን 3 ለ2 አሸንፏል።

ለፓሪ ሳንጃርሞ በፈረመ በ19ኛ ቀኑ ትናንት የመጀመሪያ ግጥሚያውን ያደረገው አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ የ24 ደቂቃዎች የሜዳ ቆይታው እምብዛም ነበር። ብራዚሊያዊ ጓደኛው ኔይማርን በ66ኛው ደቂቃ ላይ የተካው ሊዮኔል ሜሲ እንደ ኬሊያን ምባፔ የጎላ ብቃቱን ዐላሳየም። በትናንቱ ግጥሚያ ተጋጣሚ ቡድኑ ሬሚ ላይ 2 ግቦችን ያስቆጠረው ኬሊያን ምባፔ የምሽቱ ኮከብ ኾኖ ገኖ ወጥቷል። በፍጥነት እና ቅልጥፍናም የተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾችን ሲያስጨንቅ ቆይቷል።

Jacques Rogge, früherer IOC-Präsident ist verstorben
ምስል Sergei Bobylev/ITAR-TASS/imago

ዣክ ሮጀ በ79 ዓመታቸው አረፉ

የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) የቀድሞ ፕሬዚደንት ዣክ ሮጀ ትናንት በ79 ዓመታቸው ዓረፉ። ዣክ ሮጀ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2001 እስከ 2013 ድረስ የኮሚቴው ፕሬዚደንት ኾነው አገልግለዋል። ከዚያም የድርጅቱ የክብር ፕሬዚደንት ነበሩ። ዣክ ሮጀ፦ ጌንት ቤልጂየም በሚገኘው የሕክምና ተቋማቸው የአጥንትና መገጣጠሚያዎች ቀዶ ጠጋኝም ነበሩ። በተቋማቸው አምስት ሺህ ኅሙማንን የተመለከቱ ሲሆን፤ ስምንት መቶ የቀዶ ጥገናዎችንም ማከናወናቸው የሕይወት ታሪክ ጽሑፋቸው ያትታል። የሕክምና ባለሞያው የቀድሞ የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚደንት በኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ላይ ያላቸው ጠንካራ የተቃውሞ አቋምም ይታወቃሉ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ