የነሐሴ 9 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ነሐሴ 9 2014ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ባደረገው ሁለተኛ ግጥሚያው ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል በተከታታይ ተጋጣሚዎቻቸውን ድል ማድረግ ችለዋል። ሊቨርፑል የዋነኛ ተፎካካካሪነቱን ስልት ላለማጣት ዛሬ ማታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን እና ዋነኛ ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሁለኛ ጨዋታቸውንም አሸንፈዋል። ላይፕትሲሽ በሁለተኛ ጨዋታውም አቻ ወጥቷል። በላሊጋው ባርሴሎና ነጥብ ሲጥል፤ ሪያል ማድሪድ አሸንፏል። የከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ባለድሉ ታይሰን ፉሪ መቧቀሱ በቃኝ ብሏል።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች የቸልሲው እና የቶትንሀም ሆትስፐሩ አሰልጣኞች ዱላ ቀረሽ ፍጥጫ ዋነኛ መነጋገሪያ ኾኗል። እንዲያ ግንባር ለግንባር ተጋጥመው፤ ቡጢ ባይሰናዘሩም ደም ስሮቻቸው ተግተርትሮ ቡጢ የጨበጡ እጆቻቸውን ወደታች ወጥረው ግን ተጩዋጩኸዋል። በስተመጨረሻም በተናጠል በሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች በድርጊታቸው መዝናናታቸውን አሰልጣኞቹ ተናግረዋል። ጀርመናዊው ቶማስ ቱኁል እና ጣሊያናዊው አቻቸው አንቶኒ ኮንቴ።
ቸልሲ በ2017 የፕሬሚየር ሊጉ የበላይ ኾኖ ባጠናቀቀበት ስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየሙ ትናንት እንግዳው ያደረገው ቶትንሀም ሆትስፐርን በልጦ ነበር ጨዋታውን የጀመረው። ቸልሲ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብ ክልል ተጠግቶ በካይ ሐቫርትስ ያደረገው ሙከራ ለቶትንሀም አስደንጋጭ ነበር። በአንቶኒዮ ኮንቴ የሚመራው ቶትንሀም ከድንጋጤው ሳይወጣ በተገኘው የማዕዘን ምት የተላከችውን ኳስ የቸልሲው የኋላ ተከላካይ ካሊዱ ኩሊባሊ መሬት ሳታርፍ ወደጎን ተዘምዝዞ በመምታት በድንቅ ኹኔታ ከመረብ አሳርፏታል። ምዕራብ ለንደን የሚገኘው ስታንፎርድ ብሪጅ ስታዲየምም በአንድ እግሩ ቆሟል። ከበረኛው አጠገብ የነበረው ራሒም ስተርሊንግ በፍጥነት ጭንቅላቱን ዝቅ ባያደርግ ኖሮ ኳሷ ትጨናገፍ ነበር።
60ኛው ደቂቃ ላይ የቶትንሀም አጥቂ ሐሪ ኬን ግሩም የሚባል የግብ ሙከራ አድርጎ ነበር። ኳሷ ግን ለጥቂት ከግብ ጠባቂው በስተቀኝ ከግቡ ቋሚ በቅርብ ርቀት ወደ ውጪ ወጥታለች። 68ኛው ደቂቃ ላይ ጆርጂንዮ ኳሷን መቆጣጠር ባለመቻሉ በተፈጠረ ስህተት ፒዬር ኤሚል ሆይቢዬርግ በዛው በበረኛው በስተቀኝ በኩል መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል። በአሰልጣኝ መስመርም ዱላ ቀረሽ ፍጥጫ ተከስቷል። ግቧ እንደተቆጠረች በደስታ ጮቤ የረገጡት አሰልጣኝ አንቶኒ ኮንቴ ወደ ቸልሲው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል አቅጣጫ በመሮጥ ደስታቸውን ይገልጣሉ። ቱኁልም በንዴት ወደ ቶትንሀሙ አሰልጣኝ ቀርበው ግንባራቸውን ወደ አሰልጣኙ ግንባር አስጠግተው በንዴት ይጮሃሉ። በረዳት ዳኞች እና ሌሎች ገላጋይነት አሰልጣኞቹ ቡጢ ከመሰናዘር ተርፈዋል። ቶማስ ቱኁል ከአንኒ ኮንቴ ጋር መፋጠጣቸው ብዙም ሊጋነን አይገባም ብለዋል።
«ሁለታችንም ለቡድኖቻቸን ተፋልመናል። እናም ያ ተከስቷል። በጣም ፍትጊያ የነበረበት ጨዋታ ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ ጫፍ ደርሰው ነበር። ያም በመሆኑ ነገሩ በሁለታችንም በኩል ተጋግሏል። አዎ፤ እሱም እንደ እኔ የተዝናናበት ይመስለኛል። ምንም መጥፎ ነገር አልነበረም ሰዎች፤ ምንም።»
ፍጥጫውንም ሁለት ተጨዋቾች ሜዳ ውስጥ እንደሚያደርጉት አይነት ንትርክ ግን ደግሞ ማንም ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ የፕሬሚየር ሊግ አካል አድርጋችሁ ዕዩት ሲሉም አክለዋል። የቶትንሀም ሆትስፐር አሰልጣኝ አንቶኒ ኮንቴ ከቸልሲው አሰልጣኝ ጋር በነበረው ፍጥጫ እሳቸውም ተዝናንተውበት እንደነበር በጋዜጠኞች ተጠይቀው በበኩላቸው ቀጣዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
«መዝናናት? በተፈጠረው ነገር ሁለታችንም የተዝናናን ይመስለኛል። በሚቀጥለው ግን በደንብ ትኩረት አድርገን እንጨባበጣለን። እንዲያ ችግሩን እንፈታዋለን። እሱም የራሱ እኔም የራሴ መቀመጫ ጋር እንወሰናለን።»
አሰልጣኞቹ ከጨዋታው በኋላ በድርጊታቸው «ተዝናንተንበታል» ይበሉ እንጂ ሜዳ ውስጥ እጅግ ተበሳጭተው እንደነበር ሊሸሽግቱት አይችሉም። አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል በእርግጥ ከአሰልጣኝ አንቶኒ ኮንቴ ጋር ከመፋጠጣቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ካይ ሐቫርትስ ላይ የተፈጸመው ጥፋት ያለ ቅጣት መታለፉ እጅግ ሳያበሳጫቸው አልቀረም። 77ኛው ደቂቃ ላይ ራሒም ስተርሊንግ በድንቅ ኹኔታ ያቀበለውን ኳስ ከተከላካይ ነጻ ኾኖ ይጠብቅ የነበረው ሪይስ ጄምስ በማስቆጠር ቸልሲ 2 ለ1 እንዲመራ አስችሏል። በዕለቱ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ኮንቴ ቶትንሀሞች ኳስ መቆጣጠር ሲሳናቸው በፍጥነት ለብራሒም ስተርሊንግ ማቀበሉ እና ስተርሊንግም ራሱ ከመሞከር ይልቅ ነጻ ኾኖ ይጠብቀው ለነበረው ሪይስ ጄምስ ኳሷን ማቀበሉ ለቸልሲ ድንቅ የቡድን ሥራ ተብሎ የሚወደስለት ነው።
መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ የተጨመረው 6 ደቂቃ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች ሲቀሩ ግን ቸልሲን ፍጹም የሚያበሳጭ ክስተት ተፈጠረ። ቶትንሀም ሆትስፐር ከግብ ጠባቂው በስተግራ በኩል የማዕዘን ምት አገኘ። በኢቫን ፔሪሲች በግሩም ኹኔታ የተላከውን ኳስ የቶትንሀሙ ወሳኝ አጥቂ ሐሪ ኬን ዘሎ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፏታል። ቶትንሀም ሆትስፐሮችን ከሽንፈት በማዳን ያስጨፈረ፤ ቸልሲዎችን አሸንፈው ሦስት ነጥብ እንዳይዙ ያደረገ አጋጣሚ።
ጨዋታው ሁለት እኩል ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች ነጥብ ቢጋሩም በስተመጨረሻ በአሰልጣኞች መካከል የተከሰተው መጥፎ ድርጊት ነው። ጨዋታ ሲጠናቀቅ እንደ ደንቡ አሰልጣኞች ይጨባበጣሉ። አንቶኒ ኮንቴ እና ቶማስ ቱኁል ሲጨባበጡ ግን ዳግም ግብግብ ተፈጥሯል። የቸልሲው አሰልጣኝ ሲጨብጧቸው ሌላ ቦታ እየተመለከቱ ሊያልፉ የነበሩት የቶትንሀሙ አሰልጣኝ እጅን ጨብጠ በመያዝ አልለቅም ይላሉ። አንቶኒ ኮንቴ ደጋግመው፦ «ምንድን ነው የምትፈልገው?» ሲሉ ተደምጠዋል። ቶማስ ቱኁልም በጣቶቻቸው ዐይኖቻቸውን ደጋግመው ዐሳይተዋል። ስትጨብጠኝ ዐይኔን እያየህ በሚል መልኩ። በዚህ ወቅትም አሰልጣኞቹ የተገላገሉት በአካባቢው በነበሩ ረዳቶቻቸው እና ዳኞች ነው። ሁለቱም ለድርጊታቸው የቀይ ካርድ ተሸክመው ወደ ቤታቸው አምርተዋል።
በመጀመሪያ ግጥሚያው ክሪስታል ፓላስ ሜዳ ኼዶ 2 ለ0 ያሸነፈው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት በሜዳው ኤሚሬትስ ስታዲዬም ላይሰተር ሲቲን አስተናግዶ 4 ለ2 ሸንቶታል። በዕለቱ ጋብሪዬል ጄሱስ ሁለት ግቦችን በተከታታይ አስቆጥሯል። ሁለቱ ግቦች የግራኒት ሻቃ እና ጋብሪዬል ማርሺያል ናቸው። ለላይስተር ሲቲ ዊሊያም ሳሊባ እና ጄምስ ማዲሰን አስቆጥረዋል። በዚያኑ ቀን በነበረው ሌላ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ዘና ብሎ በርመስን 4 ለ0 ድል አድርጓል። በመጀመሪያ ግጥሚያው ዌስትሀም ሜዳ አቅንቶ የነበረው ማንቸስተር ሲቲ 2 ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል። በቅዳሜው ጨዋታ ኢልካይ ጉንዶዋን፤ ኬቪን ዴ ብሩወይነ፤ ፊል ፎደን እና በገዛ መረቡ ጄፈርሰን ሌርማ ናቸው ግቦቹን ያስቆጠሩት።
በሌሎች ግጥሚያዎች፦ አስቶን ቪላ ኤቨርተንን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ብራይተን ከኒውካስል ዩናይትድ እንዲሁም ፉልሀም ከዎልቨርስሀምፕተን ዋንደረርስ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ሳውዝሐምፕተን ከሊድስ ዩናይትድ ሁለት እኩል ወጥተዋል። ትናንት ወደ ኖቲንግሀም ፎረስት ያቀናው ዌስትሀም ዩናይትድ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል።
ከምንም በላይ ግን ማንቸስተር ዩናይትድ ዳግም መሸነፉ ደጋፊዎቹን እጅግ አበሳጭቷል። ባለፈው የመጀመሪያ ጨዋታው በሜዳው ኦልድትራፎርድ በብራይተን የ2 ለ1 ሽንፈት ያስተናገደው ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት በብሬንትፎርድ የ4 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። ባለፈው በብራይተን የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመካስ ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ቀዳሚ ተሰላፊ ያደረጉት አሰልጣኝ ቴን ሐግ እሳቸውንም፤ ቡድናቸውንም ሆነ ደጋፊዎቻቸውን እጅግ ያሳፈረ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
የኦስትሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጀርመናዊው ራልፍ ራኚክ ማንቸስተር ዩናይትድ ተፎካካሪ ለመሆን 10 አዲስ ተጨዋቾችን ማስፈረም ይገባዋል ሲሉ ያቀረቡት ትችት ቅዳሜ ዕለትም ሜዳ ላይ በሚገባ ተንጸባርቋል። የማንቸስተር ዩናይትድ በብራይተን መሸነፍ መጥፎ ነበር ማለት ይቻላል፤ በብሬንትፎርድ በሰፋ የግብ ልዩነት እንዲያ መረምረሙ ግን ለቡድኑ እጅግ አሸማቃቂ ነው። አራቱ ግቦች ከ10ኛው ደቂቃ ጀምሮ በ18ኛው፤ 30ኛው እና 35ኛው ደቂቃ በተከታታይ መቆጠራቸው የማንቸስተር ዩናይትድ ድከምትን ያጎሉ ናቸው። በተለይ የመጀመሪያዋ ግብ በግብ ጠባቂው እና በክሪስቲያኖ ሮናልዶ ድክመት የተቆጠረች ናት። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ኳስ በቀላሉ መቀማቱ፤ ግብ ጠባቂው ዴ ጊያ የተልፈሰፈች ኳስ መያዝ አለመቻሉ ብርቱ ድክመት ነበሩ። ሁለተኛውም ግብ ቢሆን በኤሪክሰን ጥፋት የተቆጠረ ነው።
በአጠቃላይ የብሬንትፎርድ ተጨዋቾች ልዩ ብቃት በታየበት መልኩ ነበር ግቦቹን ያስቆጠሩት። ብሬንትፎርድ ባለፈው ከላይስተር ሲቲ ጋር ሁለት እኩል የወጣ ሲሆን፤ በመቀጠል የፊታችን ቅዳሜ ፉልሀምን ይገጥማል።
ዛሬ ማታ ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊግ ሁለተኛ ግጥሚያውን ከክሪስታል ፓላስ ጋር ያከናውናል። ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ካደረጓቸው ግጥሚያዎች መካከል ከአምስት ዓመት በፊት ክሪስታል ፓላስ ሊቨርፑልን 2 ለ1 ማሸነፉ ይነገርለታል። ከዚያ ውጪ ግን ሊቨርፑል በተለያዩ ግጥሚያዎች አሞራዎቹን 10 ጊዜ በተከታታይ ድባቅ መትቷል። በፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ደግሞ ክሪስታል ፓላስ 13 ጊዜ ከሊቨርፑል ጋር ተገናኝቶ በዘጠኙ ሽንፈት ገጥሞታል።
ሊቨርፑል ላለፉት 18 ጊዜያት በሜዳው ባደረጋቸው የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ተሸንፎ ዐያውቅም። ለመጨረሻ ጊዜ ሊቨርፑል በሜዳው የመጀመሪያ ግጥሚያውን የተሸነፈው በቸልሲ ሲሆን፤ እሱም የዛሬ 19 ዓመት ነው። ከዚያ ባሻገር ሊቨርፑል ባለፉት 20 የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎቹ አንድም ጊዜ ሽንፈት ገጥሞት ዐያውቅም። ይህም ሳይሸነፍ ለረዥም ጊዜ በመቆየት ረዥሙ ተብሎለታል። በአንጻሩ ክሪስታል ፓላሶች ካለፉት ሦስት የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎቻቸው በሁለቱ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
ሊቨርፑል በጉዳት የተነሳ አሌክስ ኦክሌድ ቻምበርላይን፤ ቲያጎ አልካንታራ፤ ኩርቲስ ጆንስ፤ ዲዬጎ ጆሴ ታይክሴሪያ እና ኢብራሒም ኮናቴን በጉዳት፤ ናቢ ኪዬታን በኅመም እንዲሁም ኮስታስ ትሲሚካስን በሌላ ምክንያት ማሰለፍ ባይችልም ዛሬ ማታ ግን በሜዳው አንፊልድ ላይ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ባለፈው የመጀመሪያ ግጥሚያው ከፉልሀም ጋር ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ሲጋራ፤ የፕሬሚየር ሊጉ ዋነኛ ተፎካካሪ ማንቸስተር ሲቲ ሁለቱንም ጨዋታዎቹን በሰፋ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል። አርሰናልም እስካሁን ሁለቱንም ጨዋታቸውን በሰፋ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ከቻሉ ቡድኖች ውስጥ ይመደባል።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያ ላይፕትሲሽ ከኮሎኝ፤ ቬርደር ብሬመን ከሽቱትጋርት እንዲሁም ሻልከ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር በተመሳሳይ የግብ ልዩነት ሁለት እኩል ወጥተዋል። ቦሁም በሆፈንሀይም 3 ለ2 ሲሸነፍ፤ አውግስቡርግ ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ1 አሸንፏል። ሔርታ ቤርሊን ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል። ትናንት በነበረ ግጥሚያ ማይንትስ ከዑኒዮን ቤርሊን ጋር ያለምንም ግብ ሲለያዩ፤ ባየርን ሙይንሽን ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 አሰናብቷል። ለባየርን ሙይንሽን ጃማል ሙሳይላ እና ቶማስ ሙይለር አስቆጥረዋል።
ላሊጋ
በስፔን ላሊጋ፦ ባርሴሎና ከራዮ ቫሌካኖ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ሴልታ ቪጎ እና ኤስፓኞል ሁለት እኩል ሲወጡ፤ ቪላሪያል ሪያል ቫላዶይድን 3 ለ0 አሸንፏል። ሪያል ማድሪድ አልሜሪያን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ቫሌንሺያ ጂሮናን እንዲሁም ሪያል ሶሴዳድ ካዲዝን 1 ለባዶ አሸንፈዋል።
ለደቡብ አፍሪቃው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ተሰልፎ የሚጫወተው ኢትዮጵያዊው አጥቂ አቡበከር ናሰር በሳምንቱ መጨረሻ የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል። 76ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ አቡበከር ለራሱ የመጀመሪያ ለቡድኑ አራተኛ የሆነችውን ግብ ካይዘር ቺፍስ ቡድን ላይ በማስቆጠር ተስፋ የሚጣልበት አጥቂ መሆኑን ዐሳይቷል። በሌላ የሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተሰማ ዜና፦ ኮሎምቢያ ውስጥ በተከናወነው የዓለም እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ፉክክር ላይ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ደማቅ የጎዳና ላይ አቀባበል ሥነስርዓት መከናወኑም ተዘግቧል።
ቡጢ
የከባድ ሚዛን ቡጢ ባለድሉ ታይሰን ፉሪ ከቡጢ ዓለም መሰናበቱን በሳምንቱ መጨረሻ ይፋ አድርጓል። ታይሰን ፉሪ ወደ ቡጢ መድረክ በመመለስ ከሀገሩ ልጅ ብሪታንያዊው ዴሬክ ቺሶራ ጋር ለመቧቀስ ፍላጎት እንዳለው ሰሞኑን ሲገልጥ ነበር። ታይሰን ፉሪ ሚያዝያ ወር ላይ ዌምብሌ ስታዲየም ውስጥ ዲሊያን ዋይተን ባሸነፈበት ወቅት የመቧቀሻ ጓንቱን እንደሚሰልቅ ለባለቤቱ ቃል ገብቶ ነበር። ከዚያ በፊት ግን ከአንቶኒ ጆሹዋ ጋር የመፋለም ፍላጎትም ነበረው። ባሳለፍነው ዐርብ ከቡጢ ዓለም መሰናበቱን ይፋ አድርጓል። 34 ዓመቱ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ