የአማራ ክልል የጸጥታ ሁኔታ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 13 2014በአማራ ክልል ሕግ ለማስከበር መንግሥት ጀመርኩት ካለው እርምጃ በኋላ በተለያዩ ከተሞች ግጭቶች ተቀስቅሰዋል። በወልዲያ ትላንት ማታ የጸጥታ አስከባሪዎች ተኩስ ከፍተው ለጊዜው ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች መገደላቸውን እና ዘጠኝ መቁሰላቸውን የዐይን እማኞች ተናግረዋል። ትላንት ግጭት የነበረባቸው ሞጣ እና መራዊ ከተሞች መረጋጋት መጀመራቸውን የከተሞቹ ነዋሪዎች ተናግረዋል። አለምነው መኮንን ተጨማሪ ዘገባ አለው።
ሰሞኑን በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ አለመረጋጋቶች እየተሸሻሉ መሆናቸውን የየአካባቢው ነዋሪዎች አመልክተዋል፣ ሥለደረሰው ጉዳት አሁን የተደራጀ መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ የመንግስት ባለስልጣናት ተናግረዋል፣ ከባሕር ዳር ሞጣና ከአዲስ አበባ ሞጣ ተዘግቶ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ትናንት ከሰዓት በኋላ መጀመሩም ታውቋል፣ የአማራ ክልል መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ውስጥ በርካታ የህገወጥነት ተግባራት ሰፍኗል ሲል ሰሞኑን ለብዙሀን መገናኛ አሳቀወቋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ይህን “ህገወጥነት” ያሉትን ተግባር ለማስቆም የክልሉ መንግስት ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል::
ይህን ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ ተከትሎ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የከተማ ወጣቶችና የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተጋጭተው የሰው ህይወት መጥፋቱንና የአካል ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡
አንድ የሞጣ ከተማ ነዋሪ በግጭቱ የሞቱና የቆሰሉ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመው አሁን በከተማዋ መረጋጋት መኖሩንና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ክፍት መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
ሆስፒታል አካባቢ እንደሚሰሩ የነገሩን የወልዲያ ከተማ ነዋሪም ትናንትና አንድ የታሰረ ሰው እንዲፈታ በጠየቁ ወጣቶችና በፀጥታ ኃይሉ መካከል ግጭቶች ተፈጥረው ህይወት የጠፋ ሲሆን 9 ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ ቆስለው መተኛታቸውን ማየታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማሪያም አምባዬ አሁን በወልዲያ ከተማ መረጋጋት መፈጠሩን አመልክተው ስለደረሰው ጉዳት አሁን መረጃ እንደማይሰጡ አስረድተዋል፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን መራዊ ከተማም ትናንት አለመረጋጋት የነበረ ቢሆንም አሁን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳለ ነዋሪዎች አመልክተዋል፣ የዞኑ ባለስልጣናት ተጨማሪ አስተያየት ለመስጠት እንደማይችሉ ለዶቼ ቬለ ገልጠዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ አማራ ክልል አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ ዛሬ ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ የህግ ማስከበሩ ዓላማ ክልሉን ለማዳከም የሚሰሩ ኃይሎችን መልክ ለማስያዝ ነው ብለዋል
ስህተታቸውን አርመው ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ከሚፈልጉ አካላት ጋር ለመወያየት መንግስት ዝግጁ ነው ያሉት ዶ/ር ሰማ፣ ከእኔ በላይ ላሳር የሚል ካለ ግን ትዕግስት የለንም ነው ያሉት፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ህግን ለማስከበር በተባለው እንቅስቃሴ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥርስር መዋላቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ