1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአራት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ዕግድ ስለ ኢትዮጵያ የሲቪክ ምኅዳር ምን ይናገራል?

Eshete Bekele
እሑድ፣ ጥር 4 2017

የብሔራዊ ምክክር ሒደት የጀመረችው፤ ለሽግግር ፍትሕ የምትዘጋጀው እና በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ የምታካሒደው የኢትዮጵያ መንግሥት አራት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችን አግዷል። በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በኩል የተላለፈው ዕግድ ሕጋዊ ነው? ዕግዱ ስለ ሲቪክ ምኅዳሩ ይዞታ ምን ይናገራል? ሦስት እንግዶች የተሳተፉበትን ውይይት ያድምጡ!

https://p.dw.com/p/4p2T3
Äthiopien Addis Abeba 2023 | Neues Friedensdenkmal in der Hauptstadt errichtet
ምስል Eshete Bekele/DW

እንወያይ፦ የአራት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ዕግድ ስለ ኢትዮጵያ የሲቪክ ምኅዳር ምን ይናገራል?

የኢትዮጵያ መንግሥት አራት የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችን በታኅሳስ 2017 አጋማሽ አግዷል። የታገዱት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ናቸው።

የቀረበባቸውን ክስ የማይቀበሉት የመብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በደብዳቤ ያገዳቸው የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ማብራሪያ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዕግዱ ተነስቶ ወደ ሥራቸው ለመመለስ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር ንግግር እያደረጉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

አራቱ ድርጅቶች የታገዱት ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ምክክር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አጀንዳዎች እያሰባሰበች በምትገኝበት ወቅት ነው። በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የሽግግር ፍትሕ እና በሚቀጥለው ዓመት የሚካሔደው ብሔራዊ ምርጫ የሲቪክ ድርጅቶችን የነቃ ተሳትፎ ይሻሉ።

ብርቱ ሰብአዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳት ባደረሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በመካሔድ ላይ በሚገኙ ግጭቶች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመሰነድ እና ለመመርመር የድርጅቶቹ ሚና አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል።

ሦስት እንግዶች የተሳተፉበት ይኸ ውይይት የአራቱን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ዕግድ መነሻ በማድረግ የሲቪክ ምኅዳሩን ሁኔታ ይፈትሻል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም፣ በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሰብአዊ መብቶች መርሐ-ግብር ተባባሪ ዳይሬክተር ዶክተር አባድር ኢብራሒም እና የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ ኃይለማርያም ተሳትፈዋል።

ከኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተወካይ ለመጋበዝ ዶይቼ ቬለ ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። 

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ፦

እሸቴ በቀለ