1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጀመሪያው እና ብቸኛው የኤርትራ ቢራ ፋብሪካ

ረቡዕ፣ መስከረም 3 2010

ኤርትራውያን በአገራቸው በሚመረተው ቢራ እና በአረቄ መሳዩ ዘቢብ አልኮል ኩራት ይሰማቸዋል። ሁለቱምን የሚያመርተው የአስመራ ቢራ ፋብሪካ በአገሪቱ ብቸኛው የአልኮል መጠጦች ጠማቂ ነው። የውሐ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈትነው ፋብሪካ ወደ ውጭ የሚልካቸውን ምርቶች የማሳደግ ተስፋ አለው። 

https://p.dw.com/p/2jucN
Brauerei Eritreas
ምስል Linda Staude

የመጀመሪያው እና ብቸኛው የኤርትራ ቢራ ፋብሪካ

የአስመራ ቢራ ፋብሪካ ለኤርትራ ብቸኛው የመጀመሪያውም ጭምር ነው። አንድ ቢራ በ15 ናቅፋ ለገበያ የሚያቀርበው ፋብሪካ በገበያው ተወዳዳሪ የለበትም። የአስመራ ቢራ ፋብሪካ የምርት ክፍል ኃላፊ አቶ የማነ ጸጋይ "ይህ በአገራችን ብቸኛው ቢራ ፋብሪካ ነው። ከሌሎች ጋር እየተወዳደርን አይደለም። ሌሎች ከውጭ የሚገቡ ቢራዎች እጅግ ውድ ናቸው። እናም ሰዎች የእኛን ቢራ መጠጣትን ይመርጣሉ። " ሲሉ ይናገራሉ።  አቶ የማነ "የቢራ መጥመቂያ ማሽናችን የተተከለው በ2003 ዓ.ም. ነው። ክሮነስ ከተባለ ኩባንያ የተገዛ ነው። በጣም የታወቀ የቢራ መጥመቂያ ማሽን ነው። አሁንም በሰዓት 30,000 ጠርሙስ ቢራ ነው የምናመርተው።" ሲሉም ያክላሉ። 

 ኤርትራውያን በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ባለፈው ፋብሪካ በአገራቸው የሚመረተውን ቢራ እጅግ ይወዱታል። ቢራ ፋብሪካው የተመሰረተው በሉዊጂ ሜሎቲ አማካኝነት በጎርጎሮሳዊው 1939 ዓ.ም. ነበር። ኤርትራ በጣልያን ቅኝ ግዛት ሥር ሳለች የተቋቋመው ፋብሪካ የአልኮል መጠጦች ለማምረት ነበር። ከሶስት አመታት በኋላ የሜሎቲ ቤተሰብ ከደረቅ የአልኮል መጠጦች በተጨማሪ ቢራ ማምረት ጀመረ። ትርፋቸውም በፍጥነት አሻቀበ። በጎርጎሮሳዊው 1975 ዓ.ም. እንደሌሎች የግል ኩባንያዎች ሁሉ የደርግ መንግሥት ፋብሪካውን ሲወርሰው ነገሮች ተቀያየሩ። በጎርጎሮሳዊው 1991 ዓ.ም. ደርግ በትጥቅ ትግል ከሥልጣን ወርዶ ኤርትራም ነፃነቷን አውጃ ስትገነጠል ቢራ ፋብሪካው የመንግሥት ንብረት ሆኖ ቀጠለ። 

የአስመራ ቢራ ፋብሪካ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሐንስ ሐብቴ "አብዛኛው የፋብሪካው አክሲዮኖች ባለቤት መንግሥት ነው። የግል ባለድርሻዎችም አሉን። እግጅ ጥቂት ድርሻ ነው ያላቸው። ወደ 16 በመቶ ድርሻዎች የግል ናቸው።" ሲሉ ይናገራሉ። 

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የኤርትራ መንግሥት እጁ የሚገኙ ተቋማትን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማሻገር ያደረገው ጥረት እምብዛም ፈቅ አላለም። አምባገነን እየተባለ የሚወቀሰው መንግሥት ግትር የኤኮኖሚ ፖሊሲ እና ኤርትራ የምትኮነንባቸው ድርጊቶች ባለወረቶችን አሽሽቷቸዋል። አቶ የማነ ገብረአብ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ ናቸው። አቶ የማነ ወደ ፊት ኤርትራ የባለወረቶችን ቀልብ ትስባለች የሚል ተስፋ አላቸው።
"እስካሁን ከውጭ ማግኘት የቻልንው በማዕድን ፍለጋው ዘርፍ የሚሰማሩ ባለወረቶችን ነው። እጅግ አትራፊ የሥራ ዘርፍ ነው። አሁን ሰዎች ሌሎች የሥራ ዘርፎችን እየተመለከቱ ነው ብዬ አስባለሁ። ግብርና ለእኛ እጅግ ጠቃሚ ዘርፍ ነው። ሌላው የማዕድን ፍለጋ ነው። በሁሉም ዘርፎች መዋዕለ ንዋይ ከመጣ በደስታ እንቀበላለን።"

ለአስመራ ቢራ ፋብሪካ አስተዳደር ፈታኙ ሥራ ለቢራ ጠመቃ የሚያገለግሉትን ግብዓቶች ማግኘት ነው። ለአራት አይነት መጠጦች የሚያገለግለው አልኮል ከደቡብ ሱዳን፤ ጌሾ ከጀርመን፤ የገብስ ብቅል ከተለያዩ አገሮች ወደ ኤርትራ ይጫናል። አሁንም የምርት ክፍሉ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ሐብቴ 

"አብዛኛው ጥሬ እቃ እና ግብዓት ከውጭ አገራት የሚመጣ በመሆኑ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ሁልጊዜም ችግር ነው። ነገር ግን ይኸንንም ችግር ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን። ምክንያቱም ለብቅል የምንፈልገውን ገብስ በኤርትራ ለማምረት እየሞከርን ነው።" እንደ አቶ ዮሐንስ አባባል ከሚያስፈልጓቸው ግብዓቶች 16 በመቶው በራሱ በኩባንያው ይመረታሉ። ለመጪው ጊዜ የውሐ አቅርቦቱን ለማረጋገጥ መንገድ ቀይሰዋል። 

የምርት ክፍሉ ኃላፊ የውሐ አቅርቦት በማግኘታቸው እጅጉን ደስተኛ ናቸው። ኩባንያው የምርት ሒደቱን ለማዘመን ባለፉት አመታት ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ አድርጓል። ደሕና ደሞዝ የሚከፍል ቀጣሪ ማግኘት ፈተና በሆነባት ኤርትራ ፋብሪካው 450 ሰራተኞች አሉት።  አቶ ዮሐንስ ሐብቴ ኩባንያቸው ከዚህ በላይ ሊቀጥር ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

"ብዙ የማምረት አቅሙ አለን። ነገር ግን የጥሬ እቃ፤ውሐ እና የኤሌክትሪክ ኃይል  እጥረት አንዳንድ ጊዜ በሙሉ አቅማችን ከማምረት ያግዱናል። ባለፈው ዓመት ከአገር ውስጥ ገበያ ፍላጎት ከ70 እስከ 80 በመቶውን ነው ያቀረብንው።"

ሁልጊዜም ከውጭ አገራት የሚቀርብ የግዢ ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል። ያም ቢሆን ግን እጅጉን ትንሽ ነው። እጅግ ጠቃሚ ገበያ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የሚላከው የቢራ ምርት በሁለቱ አገሮች መካከል በተፈጠረው የከረረ ጠብ ከተቋረጠ ቆይቷል። አቶ የማነ ጸጋዬ እንደሚሉት በውጭ አገራት የአስመራ ቢራ የተመረጡ ደንበኞች አሉት። 

"እነዚህን ደረቅ የአልኮል መጠጦች በውጭ አገራት ለሚኖሩ ኤርትራውያን እናቀርባለን። ሁሉም ሰው በተለይ ዘቢብ መጠጣት ይወዳል። ምርታችን ወደ አውሮጳ እና አሜሪካ ይሔዳል። ."

በኤርትራ የሚመረተው ዝባብ ከአገራቸው ድኅነት እና ጭቆና ሸሽተው ወደ ሌሎች አገራት ለተሰደዱ ወደ 1 ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች ዘንድ ተወዳጅ ነው። የአስመራ ቢራ ፋብሪካ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሐንስ ሐብቴ ኩባንያቸው በሒደት ወደ ውጭ አገራት ገበያ ተስፋፍቶ ለኤርትራ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል። "ለትርፍ የተቋቋምን ኩባንያ ነን። ትርፍ ማግኘት አለብን። እዚህ በኤርትራ በጣም የምንኮራበት ኩባንያ ነው።" ሲሉ ተናግረዋል። 
ናንሲ ኢሴንሰን /እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ