የአገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች የስጋት ድምጽ
ሰኞ፣ ሐምሌ 18 2014የኢትዮጵያ የገቢ ምርትና ሸቀጦች ማጓጓዣ ዋነኛ መሥመር በሆነውና ኢትዮጵያን ከጅቡቲ በሚያስተሳስረው አውራ መንገድ ላይ በአገር አቋራጭ መኪኖች አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀመው ግድያ፣ ዝርፊያና እንግልት እንዲቆም ተጠየቀ። የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የአመራር አባል የሆኑ ሰው ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ስምንት አሽከርካሪዎች በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ውስጥ በታጣቂዎች እንደተገደሉ እና ሌሎች ሰባት ባልደረቦቻቸው ደግሞ በተፈፀመባቸው ጥቃት የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልፀዋል። ለ17 ዓመታት በትዳር አብረዋቸው የኖሩት የከባድና አገር አቋራጭ መኪና አሽከርካሪ ባለቤታቸው ከሳምንት በፊት የተገደሉባቸው ሴት ባለቤታቸው በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው እንዳለፈ እና የሚያስተዳድሩትን ቤተሰብ በትነው መሞታቸውን ለ ዶቼ ቬለ (DW) ተናግረዋል።
በጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ማሕበራት እና አሽከርካሪዎች ጉዳዩ አስመልክተው ከትራንስፖርትና ሎጄስቲክስ ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ከሰሞኑ ባደረጉት ውይይት መንግሥት በመስመሮቹ የሚታዩትን ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጣጠር ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ከክልል ባለሥልጣናት ጋር እንደሚመክር አስታውቋል። የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የአመራር አባል የሆኑት አቶ ዳመነ ተሾመ እንደሚሉት ኢትዮጵያ እና ጅቡቲን በሚያስተሳስረው አውራ ጎዳና ላይ ምንም እንኳን ውስን ሥፍራዎች ላይ ቢሆንም በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ ከግድያ እስከ ዝርፊያና ማዋከብ የሚደርስ ከፍተኛ ወንጀል እየተፈፀመባቸው ችግር ውስጥ ገብተው የሥራ ላይ የደህንነት ሥጋት ውስጥ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
በጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ማሕበራት እና አሽከርካሪዎች ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጠው መጠየቃቸውን የገለፁት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታጠቅ ነጋሽ «ችግሮቹን ከፀጥታ መዋቅሩ እና ከክልል አመራሮች ጋር በመሆን በዘላቂነት ለመፍታት ንግግር እንደሚደረግ ተነግሯቸዋል» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አሽከርካሪዎቹ ከሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት አንፃር ሥራ ለማቆም በሚል ባለቤቱ ያልታወቀ ቅስቀሳ ጀምረው እንደነበር ሆኖም በውይይቱ የተሳተፉት ማሕበራት እና አሽከርካሪዎች ለሐምሌ 15 ሊደረግ ታስቦ ነበር ስለተባለው ሥራ የማቆም እርምጃ የሚያውቁት እንደሌለ መግለፃቸውንም ነግረውናል።
በአገር አቋራጭ የደረቅ እና ፍሳሽ ከባድ መኪኖች አሽከርካሪዎች ላይ ተደጋግሞ የሚፈፀመው ይህ ችግር በዘላቂነት ለምን ሊፈታ እንዳልቻለ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የሥራ አመራር አባል አቶ ዳመነ ተሾመ «የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አካባቢያቸውን እራሳቸው እንዲጠብቁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ታጣቂዎች አሽከርካሪዎችን ሲረብሹ ነበር። ምክንያቱም ክልሉ ትዕዛዝ መስጠት ስላልቻለ» ብለዋል። አክለውም« በውስጣችን ያሉ ከእኛ ግን ተለይተው ሌላ ሴራ የሚሠሩ አካሎች ነበሩ» በማለት ከጉዳት አድራሾች ጋር ግንኙነት ያላቸው አሽከርካሪዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የገቢ ምርቶች ዋነኛ መስመር የሆነው የኢትዮ - ጅቡቲ መስመር ላይ ከውጪ ገቢ ምርትና ሸቀጦችን የሚያጓጉዙ አሽከርካሪዎች የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቁልፍ ተዋናይ መሆናቸውን በመግለጽ መንግሥት መስመሩን ለሾፌሮች ምቹ እንዲያደርግ ደጋግመው ይጠይቃሉ ።
ሰለሞን ሙጬ
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሠ