1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ መ/ብዙኃን እና የቻይና ተፅዕኖ

ሰኞ፣ ጥር 6 2005

ቻይና እአአ በ 2012 ዓም የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ በአፍሪቃ ያፈሰሰችው ግንዘብ 45 ቢልዮን ዶላር ነበር። ይህም የቻይና እና የአፍሪቃ የንግድ ግንኙነት ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ ጨምሮዋል።

https://p.dw.com/p/17JQ4
Screenshot der Internetseite "CCTV Afrika " vom 03.01.2013. Link: http://cctv.cntv.cn/lm/africalive/01/index.shtml ***ACHTUNG: Das Bild darf nur im Zusammenhang mit der Berichterstattung zu "CCTV Afrika ." verwendet werden.***
ሲ ሲ ቲቪ አፍሪቃምስል cctv.cntv.cn

ይህችው ግዙፏ እሥያዊት ሀገር በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በአፍሪቃ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ውስጥ ስም ለማትረፍ በመሞከር ላይ ትገኛለች። በዚህም መሠረት በወቅቱ የሀገርዋን « ሲ ሲ ቲቪ አፍሪቃ፡ ሺንዋ የዜና ወክል እና የቻይና ዓለም አቀፍ ራድዮ» በአፍሪቃ ተክላለች። በመጨረሻ ባነቃቃችው ፕሮዤዋ አማካኝነትም በአፍሪቃ የራስዋን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋዜጣን ማሳተም እና ካለፉት ጥቂት ሣምንታትም ወዲህ ጋዜጣውን በኬንያ መሸጥ ጀምራለች።
ቻይናውያኑ በአፍሪቃ የመገናኛ ብዙኋን ዘርፍ ገበያ ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመሩ ሰንበት ብሏል። ገንዘባቸውን በዘመናዩ ሥነ ቴክኒክ ዘርፍ ያሰራሉ፤ ለአፍሪቃውያን ጋዜጠኞችም በቻይና የትምህርት ዕድል ይሰጣሉ፤ የራሳቸውን የራድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያንም ይተክላሉ። በአፍሪቃ የመገናኟ ብዙኃን ዘርፍ ውስት የቻይና ሕልውና እየጎላ መምጣቱ የሚያስገርም አይደለም ይላሉ ደራሲዋ እና የብሪታንያውያኑ ዜና አገልግሎት ድርጅት፡ ቢቢሲ የአፍሪቃ አጥኚ ሜሪ ሀፐር።
« ይህ የማይቀር ሂደት ነው። ቻይናን ስትመለከት ይህችው ሀገር በአፍሪቃ ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ባለፉት ዓመታት ዓይኗን ካሳረፈች ወዲህ ትልቋ የንግድ አጋር ሆናለች። ምዕራቡን ተክታለች። »
የቻይና የእንግሊዝኛ ቋንቋ የ« ሲ ሲ ቲቪ » እአአ ባለፈው 2012 ዓም በአፍሪቃ ስርጭቱን ማስተላለፍ ጀምሮዋል። ከዜና መጽሔቶች፡ ከውይይት እና ከዘጋቢ ታሪኮች ጎን ለእጅ ስልክ ተጠቃሚዎች አንድ የኢንተርኔት ቴሌቪዥን ዝግጅት ከፍቶዋል። በቅርብ ጊዜም ውስጥ በአፍሪቃ አንድ መቶ ቻይናውያን ዘጋቢዎችን ለመቅጠር ዕቅድ ተይዞዋል። ከዚህ ሌላም ሺንዋ የቻይና የዜና ወኪል ከአንድ የኬንያውያኑ የእጅ ስልክ ተቋም ጋ ባንድነት ከሰሀራ በስተደቡብ ለሚገኙት አፍሪቃውያት ሀገራት የመጀመሪያውን የእጅ ስልክ ዜና አገልግሎትን እየሰጠ ይገኛል። ቻይና በአፍሪቃውያኑ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ውስት እንዲህ በሰፊው ለመንቀሳቀስ ያነሳሳት ምክንያት ምን ይሆን፣ ሜሪ ሀፐር፡
« ቻይና የኤኮኖሚ ጥቅሟን ብቻ ለማስጠበቅ ስትል ነው በአፍሪቃ ጠንካራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያለችው። ለዚህም ከምዕራቡ ፕሬስ አሉታዊ ዘገባ ቀርቦባታል። ይሁንና፡ በዚህ የተነሳ ቻይና ሂደቶችን ለአፍሪቃውያኑ በተለይ በብዛት የምዕራባውያኑ ተፅዕኖ ያረፈባቸው መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት ሳይሆን በራስዋ መንገድ የማቅረብ ፍላጎት አላት። »
ቻይና ይህንን ዕቅዷን በህትመቱ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍም አጠናክራ ቀጥላለች። « ቻይና ደይሊ አፍሪካ ዊክሊ » በሚል የሚጠራው ሣምንታዊ መጽሔት ካለፈው ታህሳስ 2012 ዓም ወዲህ ኬንያ መዲና ናይሮቢ እየታተመ ይወጣል። የምዕራብ አፍሪቃ የመገናኛ ብዙኃን መናኸሪያ በምትባለው ናይሮቢ ውስጥ ቻይናውያኑ የራድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸውን ጽሕፈት ቤቶች ከፍተዋል። በናይሮቢ ስራ ከጀመሩት የቻይና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መካከል ከሀምሣ በሚበልጡ ቋንቋዎች ስርጭት የሚያስተላልፈው የቻይና የመንግሥት ዓለም አቀፍ ራድዮ»ራድዮ ጣቢያ ይገኝባቸዋል። ተቋሙ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በኬንያ መስራት መጀመሩን ያነጋገርነው አንድ እዚያ ተቀጥሮ የሚሰራ ኬንያዊ ጋዜጠኛ ገልጾዋል። ለምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን ቃለ ምልልስ መስጠት ያን ያህል በተቋሙ የሚደገፍ ባለመሆኑ ጋዜጠኛው ማንነቱ እንዲታወቅ አይፈልግም።
« ዘገባዎቻችንን በመጀመሪያ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከጻፍን በኋላ ወደ ኪስዋሂሊኛ ይተረጎማል።ይሁንና፡ ዘገባዎቻችንን በቀጥታ ከናይሮቢ አናስተላልፍም። በዚህ ፈንታ ሁሉን የተቋሙ ዋና መንበር ወደሚገኝበት ወደ ቻይና መዲና ፔኪንግ እንልከዋለን። ከዚያ ነው የጻፍናቸው ታሪኮች የሚተላለፉት። ከዚህ ሌላ ደግሞ የቻይናውያኑን የአሰራር ዘዴ በሚገባ እንድናውቅ እየተባለ በየጊዜው ወደ ፔኪንግ በመሄድ ስልጣና መውሰድ አለብን። »
ፔኪንግ ቁጥጥር ሳንሱር ሳታደርግበት የሚተላለፍ ዘገባ የለም። ቀደም ባሉ ጊዚያት በኬንያውያኑ ራድዮ ጣቢያ ይሰራ የነበረው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ይህ የአሰራር ዜዴ ቀላል እንዳልሆነ ነው ያመለከተው።
« አሉታዊ ስለሆኑ ጉዳዮች አንዘግብም። ይሁንና፡ እንደ አንድ ጋዜጠኛ ሁሌም ጥሩ ፍፃሜ ስለሌላቸው እና ገሀዱን በተጨባጭ ስለሚያሳዩ ጉዳዮች፡ እንዳሉ መዘገብ አለብህ። የኬንያውያኑ መገናኛ ብዙኃን ስለ ሁሉም ጉዳይ ዘገባ ያቀርባሉ። በዓለም አቀፉ የቻይና ራድዮ ዘንድ ግን በዘገባ አቀራረባችን ላይ ብዙ ምርጫ እናደርጋለን። »
እንደኬንያዊው ጋዜጠኛ አስተያየት፡ አፍሪቃውያኑ አድማጮች ዘንድ ተወዳጅነትን ለማግኘት እየተባለ ለጥሩው የአፍሪቃ ጎን ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል።
የቢቢሲ የአፍሪቃ አጥኚ ደራሲዋ ሜሪ ሀፐር ግን ከኬንያዊው ጋዜጠኛ ለየት ያለ አመለካከት ነው ያላት። የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለ አፍሪቃ አሉታዊ ዘገባ ለብዙ ጊዜ ሲያቀርቡ ቆይተዋል የምትለው ሀፐር አሁን ቻይናውያኑ የምዕራቡ ተፎካካሪዎች በአፍሪቃውያኑ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ላይ አዲስ አሰራር ይዘው መቅረባቸው የሚደገፍ ሆኖ አግኝታዋለች።
« እንደማስበው፡ ወደፊት ብዙ ዓለም አቀፍ እና አፍሪቃውያን የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በአፍሪቃ መንቀሳቀሳቸው አይቀርም። አህጉሩ ብዙ ገንዛብ አለው፤ በመገናኛ ብዙኃኑ ዘርፍ ደግሞ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ በዘመናይ መንገድ ተቀናጅቶዋል። እና የተለያዩ ወገኖች በአፍሪቃውያኑ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ መሰማራታቸው፡ አንዱ ከሌላው ይበልጥ ተፅዕኖ ለማሳረፍ እስካልሞከረ ድረስ ጥሩ ነው። »
ይሁንና፡ ታዛቢዎች እንደሚሉት በአፍሪቃ የቻይና እንቅስቃሴ እየተጠናከረ መሄዱ መጥፎ ጎንም አለው ። እንደ,ርሱ አስተያየት፣ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃኑን ዘርፍ ለመቆጣጠሪያ የሚበጅ አውታር በመትከሉ ተግባር መንግሥትን እንደረዱና ከዚያን ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ የሚገኙ የተቃዋሚ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በየጊዜው እየታፈኑ ተዘግተዋል፣ በመንግሥት አንጻር ሂስ የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞችም ወደ ወህኒ ወርደዋል።
ናዲና ሽቫርስቤክ/አርያም ተክሌ
መስፍን መኮንን

Screenshot der Internetseite "China Radio International " vom 03.01.2013. Link: http://english.cri.cn/ ***ACHTUNG: Das Bild darf nur im Zusammenhang mit der Berichterstattung zu "China Radio International ." verwendet werden.***
የቻይና ዓለም አቀፍ ራድዮምስል english.cri.cn
Screenshot der Internetseite "China Daily " vom 03.01.2013. Link: http://www.chinadaily.com.cn/cndy/2012-12/14/content_16016342.htm ***ACHTUNG: Das Bild darf nur im Zusammenhang mit der Berichterstattung zu "China Daily ." verwendet werden.***
ቻይና ዴይሊምስል chinadaily.com.cn
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ