የአፍሪቃ ቀንድ ምሥቅልቅል
ዓርብ፣ ሐምሌ 27 2010የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኤርትራ ላይ የጣለዉ ማዕቀብ እንዲነሳ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ከዚሕ ቀደም ያቀረቡት ጥያቄ ድጋፍም፤ ተቃዉሞ ገጥሞታል። ሰሞኑን አስመራን የጎበኙት የሶማሊያዉ ፕሬዝደንት መሐመድ አብዱላሒ መሐመድ የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚንስትር አቋም ደግፈዉ ማዕቀቡ እንዲነሳ ጠይቀዋል። ጅቡቲ ግን ከኤርትራ ጋር የገጠመችዉ የድንበር ግዛት ይገባኛል ዉዝግብ መፍትሔ እስኪያገኝ ማዕቀቡ መነሳት የለበትም ባይ ናት። የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር መድሕኔ ታደሰ እንደሚሉት የአፍሪቃ ቀንድ መንግሥታት የሁሉንም ሠላም እና ጥቅም የሚያስከብር የጋራ መርሕ ሊኖራቸዉ ይገባል። ነጋሽ መሐመድ ዝርዝር ዘገባ አለዉ።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ 20 ዓመት ያስቆጠረ ጠብ፤ ቁርቁስ፤ ዉዝግባቸዉን ባልተጠበቀ ፍጥነት ማስወገዳቸዉ ለሁለቱ ሐገራት ሕዝቦች፤ ለአካባቢዉ፤ ለሩቁም በጎ ተስፋ ነዉ። ሠላም። የዚያኑ ያሕል ፈጣኑ እርምጃ 20 ዓመት የተሸረበዉን ዲፕሎማሲያዊ ጥልፍልፍ ሜዳ ላይ ነዉ የዘረገፈዉ። ፕሮፌሰር መድሕኔ «መሳከር» ይሉታል።
ሰበቡ ኢትዮጵያ ሆነችም አልሆነች ኤርትራ ከሱዳን፤ ከጅቡቲ እና ከየመን ጋር በቀጥታ፤ ከሶማሊያ ጋርም በተዘዋዋሪ እንደተሻኮተች ነበር። ኢትዮጵያም «የጠላትሕ ጠላት» በሚል የፖለቲካ ፈሊጥ የተወዳጀቻቸዉን ሐገራት ጣጥላ ከኤርትራ ጋር መታረቅዋ ሌሎቹን አንድም የኃይል አሰላለፋቸዉን ለማሳማር ቢያጣድፍ፤ አለያም ቢያስኮርፍ ታዛቢዎች እንደሚሉት አያስደንቅም።
ሶማሊያ ካዲሱ ለዉጥ ጋር ሠልፏን አስተካክላለች። ሶማሊያ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ኤርትራ ላይ የተጣለዉ ማዕቀብ እንዲነሳ ጠይቃለች። ጅቡቲ ግን አዲሱን ግንኙነት አልፈቀደችዉም። የማዕቀብ መነሳቱን ሐሳብም ተቃዉማዋለች። ፕሮፌሰር መድሕኔ ጅቡቲን አቋም «የተጠበቀ» ይሉታል።
ፕሮፌሰር መድሕኔ እንደሚሉት የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት ለጋራ ጥቅም የጋራ መርሕ መቀየስ እንጂ እንዲሕ እንዳሁኑ አንዱን ጥሎ፤ ሌላዉን አንጠልጥሎ ዓይነት ጉዞ አይጠቅማቸዉም።
በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የወቅቱ ፕሬዝደንት የሲዊድኑ አምባሳደር ኦሎፍ ስኩግ እንዳሉት ኤርትራ ማዕቀቡ እንዲነሳላት ሥላቀረበችዉ ሐሳብ የምክር ቤቱ አባል ሐገራት ዲፕሎማቶች እየተነጋገሩበት ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ