የአፍሪቃውያን ጥላቻ በቻይና
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 10 2012ቻይና ጉዋንጁ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የኾኑ አፍሪቃውያን የቻይና ባለሥልጣናት የኮሮና ተሐዋሲ ምርመራ በግድ እንድናደርግ እና ራሳችንንም ለ14 ቀናት ለይተን እንድንቆይ በማስገደድ መድልዎ እያደረሱብን ነው ሲሉ ወቅሰዋል።»
በከተማዪቱ «ትንሿ አፍሪቃ» በመባል በምትታወቀው ሰፈር ነዋሪ አፍሪቃውያን ተማሪዎች እና ስደተኞች ባለፈው ሳምንት ከመኖሪያ አፓርትመንታቸው እንዳይወጡ መገደዳቸውን ገልጠዋል። አፍሪቃውያኑ ግዳጅ የተጣለባቸው ለተሐዋሲው ተጋላጭ መኾን አለመኾናቸው ሳይታወቅ እና የቅርብ ጊዜ የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው እንደኾነ በመናገር አማረዋል። ቻይናውያኑ የቤት አከራዮች የከተማዪቱ ነዋሪ አፍሪቃውያንን ያለአንዳች ማስጠንቀቂያ በደቦ ከመኖሪያ ቤታቸው አስወጥተውም ቤት አልባ እንዳደረጓቸው ተናግረዋል። ሆቴሎችም አፍሪቃውያኑን ማደሪያ እንደነፈጓቸው ነው የተገለጠው።
ኹኔታው አፍሪቃውያንን ከጥግ እስከ ጥግ አስቆጥቷል። የአኅጉሪቱ አመራርም ለቻይና ግልጽ ቅሬታ እና ጥያቄ አቅርበዋል። ይኽ ታዲያ ቻይና ከአፍሪቃ ጋር ለገነባቸው ዲፕሎማሲ ብርቱ ጋሬጣ ነው የኾነባት። ዲፕሎማሲያዊ ውዝግቡን ወደ ቀድሞው መስመሩ ለመመለስ ቻይና ምናልባትም ዓመታት ሊፈጅባትም ይችል ይኾናል ተብሏል።
ጉዋንጁ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የኾነው ካሜሩናዊው ሔርማን አሳ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገረው ኹኔታው እሱ እና ጓደኞቹ ከቊጥጥራቸው ውጪ ነው የኾነው።
«አንዳንድ ጊዜ የቤቱ ባለቤት ኮተትህን ሸክፈህ በፍጥነት ቤቴን ልቀቅ ሊልኽ ይችላል። ልከራከር ካልኽ ፖሊስ በአስቸኳይ ቤቱን ለቃችሁ መውጣት እንደሚያስፈልጋችሁ ነግሮናል ይሉኻል።»
አፍሪቃውያኑ ከመኖሪያቸው እንዲወጡ ከተገደዱ በኋላ አዲስ መጠለያ ማግኘት አስቸጋሪ ይኾንባቸዋል። አሳ እና ሌሎችም እንደሚሉት ወይ ብዙ እንዲከፍሉ አለያም በመጡበት እንዲመለሱ ነው የሚነገራቸው።
«አንዳንድ ጊዜ መጠለያ ከፈለግክ ተጨማሪ መክፈል ያስፈልግሃል። ቤቱ 1000 ኹዋን ማለትም 141 ዶላር ግድም የሚከፈልበት ከኾነ እጥፉን 2000 ኹዋን ትከፍላለህ። መከራከር አትችልም። ልከራከርም ብትል የሚሰማህ የለም። አዲስ ቤት ለማግኘት ለመደራደር በሞከርኩበት ወቅት ፖሊስ መጥቶ እዚያው አካባቢ እንድቆይ ነገረኝ። ከዚያም ጥበቃዎች ፖሊስ ጠሩ እና መጡ፤ እናም እዚያ ቦታ መቆየት እንደማልችል ነገረኝ።»
የኮሮና ተሐዋሲ ቻይና ውስጥ እንዳይዛመት ማድረግ መቻሉ በሚነገርበት በአኹኑ ወቅት ነዋሪዎች ከውጭ በመጡ ተጓዦች ምክንያት ኹለተኛ ዙር ወረርሽኝ እንዳያጠቃቸው በብርቱ መስጋታቸውን ይገልጣሉ። ኾኖም ጉዋንጁ ከተማ ነዋሪ የኾኑት አፍሪቃውያን ተማሪዎች እና ስደተኞች ይኽ ድርጊት ተሐዋሲውን ለመቀልበስ ከሚደረገው ትግል ጋር ተያያዥነቱ እጅግ የቀጠነ ነው ይላሉ። ይልቊንስ ዋነኛው ምክንያት በተዛባ መረጃ እና ፍርሐት የተነሳ አፍሪቃውያን ላይ የተቀሰቀሰ ጥላቻ ነው ሲሉ በከተማዪቱ ነዋሪ አፍሪቃውያን ይናገራሉ።
ኮሮና ተሐዋሲ ስያሜውን ማግኘት ያለበት መጀመሪያ ከተቀሰቀሰበት እና ዓለምን ካዳረሰበት የቻይና ውሃን ከተማ ነው የሚል ክርክር ሲነሳ ብዙዎች ተቃውመው ነበር። በተለይ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ተሐዋሲው ስያሜው መኾን ያለበት «ቻይና ቫይረስ» ነው ሲሉ አፍሪቃውያንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በርካታ ተቃውሞ ቀርቦባቸው ነበር። ቻይናውያን በተዛባ መረጃ አፍሪቃውያን ላይ ያሳዩት ድርጊት በአፍሪቃውያን ዘንድ በቀላሉ የሚፋቅ አይመስልም። ቻይና ባለፈው ዓመት ብቻ ከአፍሪቃ አኅጉር ጋር የ208 ቢሊዮን ዶላር ንግድ ማድረጓንም መዘንጋት አይገባትም ሲሉ በርካቶች ዐስጠንቅቀዋል።
ኢንከ ሙለስ/ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ