1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማብቂያ ይበጅለት ይሆን?

ሰኞ፣ ሰኔ 4 2010

ሁለት ዓመት የዘለቀዉ ጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች ፈጅቷል። በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በቢሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል። ሟች፤ ቁስለኛ፤ ስደተኛ ተፈናቃዮች አልተካሱም። የሁለቱ ሐገራት ገዢዎች ሁለት ዓመት ባደረጉት ዉጊያ አቅማቸዉ ሲዝል ግን አልጀርስ-አልጀሪያ ላይ የፈረሙት ሥምምነት ሌላ የሰላም ተስፋ መፈንጠቁ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/2zJLx
Äthiopien beginnt mit Truppenabzug aus Grenzregion zu Eritrea
ምስል picture-alliance/dpa/R. Schoonderwoerd

NM - MP3-Stereo

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ እንደገና ወሰነ።አስራ-ስድስት ዘመን ግድም በሰላምም-የለም፤ ጦርነትም የለም ረመጥ የተዳፈነዉን  ጣጣ እደገና ገለጠዉ። ባድመ እንደገና ርዕስ ሆነች። እርግጥ ነዉ የአስመራ ገዢዎች እስከ ዛሬ ቀትር ዝም እንዳሉ ነዉ።ዝም። ዉጪ ለሚኖሩ ኤርትራዉያን ግን የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ አዲስ ዉሳኔ አስደሳች ነዉ። ጥሩ ተስፋ። ኢትዮጵያዉን ከአዲስ አበባ እስከ በርሊን፤ ከባድመ-እስከ ዋሽግተን፤ ከኢሮብ እስከ ለንደን አዲሱን ዉሳኔ በመቃወም እና በመደገፍ ይከራከራሉ። ደም አፋሳሹ ጣጣ በዚሕ ያበቃ ይሆን?

የቀድሞዉ የኢትዮያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዉ «ጅል ጦርነት» ብለዉት ነበር። «እነዚሕ ችግሮች መደረግ ወዳልነበረበት ጅል ጦርነት መራን። እኛ ግዛታችንን ይዞ የነበረዉን የኤርትራን ጦር አስወግደን ቆመን።» የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት በጋመበት በ1991 የታተመ አንድ የጀርመን ጋዜጣ ግን «ጅል» ያለዉ ጦርነቱን ሳይሆን የሁለቱን ጦሮች ጠቅላይ አዛዦች ነበር። «ሁለት መላጦች ባንድ ሚዶ ይጣላሉ» በሚል ርዕሥ ተሳልቆባቸዉ ነበር።

Eritrea Soldaten beim Training im Grenzkrieg mit Äthiopien 1999
ምስል Getty Images/AFP/S. Forrest

ለተራዉ ተዋጊ ግን፤ ያዩ እንደመሰከሩት፤ በቅጡ በልቶ ያልጠገበ ወጣት ከግራም-ከቀኝም እንደ ቅጠል የረገፈበት፤  በጅምላ ቀብር «የተጨፈቀበት» ዘግናኝ ትዕይንት ነበር።

                                             

ቡሬ፤ባዳ፤ ባድመ፤ሽራሮ፤ ፆረና ዛላንበሳ ወዘተ እያልን የጦርነት ታሪክ ከመዘገብ-መዘከራችን በፊት በነበሩት ሠላሳ ዓመትም ከጦርነት ሌላ ሌላ ታሪክ አልነበረዉም። በነዚያ የጦርነት ዓመታት፤የኋላዉን የኢትዮጵ እና የኤርትራን ጦርነት «ጅል» ያሉት አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩት አማፂ ቡድን ከኤርትራ አማፂያን ጎን ተሠልፎ ለኤርትራ ነፃነት ተዋግቷል።

ሁለቱ ሸማቂዎች አስመራ እና አዲስ አበባ ላይ ሁለት መንግሥት ባቆሙ ማግስት ኤርትራ ነፃ ሐገር መሆንዋ ዓለም አቀፍ እዉቅና እንዲያገኝ፤ የአቶ መለስ ፓርቲ በፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ መስክ ተፋልሟል።

                               

Eritrea Kinder spielen 1991 auf zerstörtem äthiopischen Panzer
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

«ኤርትራ ከኢትዮጵያ (ተነጥላ) ነፃ ከወጣች በኋላ፤ ነፃ መዉጣትዋን እኔም እደግፈዉ ነበር። ምክንያቱም የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎት በመሆኑ።»

የኢትዮጵያ መሪ፤ እና ፓርቲያቸዉ የኤርትራን ሕዝብ ፍላጎት ለማስከበር፤  የሚገዟትን ሐገር ወደብ አልባ እስከማስቀረት ድረስ በጦርሜዳም፤ በፖለቲካ ዲፕሎማሲም ያደረጉት ትግል በርግጥ በ1985 ለታጋዮቹ በድል ተጠናቅቋል። ድሉ ሰላሳ ዓመታት ያስቆጠረዉ ጦርነት ፍፃሜ መስሎም ብዙዎችን አስቦርቆ ነበር። ኤርትራዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት ደግሞ ደስታዉ በተለይ ለኤርትራዉያን ገደብ አልነበረዉም።

                 

ያቺ የቀይ ባሕር ዳርቻ ግዛት፤ ከጦርነት ሌላ ብዙ ታሪክ የላትም። ጥንት አረቦች፤ ቱርኮች፤ ግብፆች  በየዘመናቸዉ እየገደሉ-ኖረዉ፤ ተገድለዉ ጠፍተዉባታል። ድሮ ጣሊያኖች፤እንግሊዞች፤ ደርቡሾች ገድለዉ፤ ገዝተዉ፤ ተገድለዉ ተባረዉባታል። ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ የነበረዉ የኢትዮጵያ ታሪክ የዲፕሎማሲ፤ የሰላማዊ ዉሕደት፤ የቅኝ ግዛት ይባል የጦርነት ድር- ማጉ የዚያች  ሰሜናዊ ግዛት የማን-ምንነት ጣጣ ነዉ።ኤርትራ።

 

«ገደብ አልባዉ ደስታ» ሰባት ዓመት ሳይሞላዉ በጦርነት እቶን መደፍለቁ ነዉ ቀቢፀ ተስፋዉ።ሚያዚያ 1990።ኤርትራዊቱ የሠብአዊ መብት ተሟጋች ሠላም ኪዳኔ «አስደንጋጭ» ይሉታል።

 ሁለት ዓመት የዘለቀዉ ጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የሁለቱን ሐገራት ወጣቶች ፈጅቷል። በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በቢሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።ሟች፤ ቁስለኛ፤ ስደተኛ ተፈናቃዮች አልተካሱም።የሁለቱ ሐገራት ገዢዎች ሁለት ዓመት ባደረጉት ዉጊያ አቅማቸዉ ሲዝል ግን አልጀርስ-አልጀሪያ ላይ የፈረሙት ሥምምነት ሌላ የሰላም ተስፋ መፈንጠቁ አልቀረም።

በስምምነቱ መሠረት የተሰየመዉ የድንበር አካላይ ኮሚሽን ሚያዚያ 1994 ይፋ ያደረገዉ ዉሳኔ  የአዲስ አበባ ገዢዎችን በድል አድራጊነት «የማንቀበራሩ» ዚቅ ግን በርግጥ እስከ ዛሬ ከነሱ ሌላ በግልፅ ያወቀዉ ካለ እሱ አይታወቅም።የያኔዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ስዩም መስፍን።

                                  

«ኤርትራ በሐሰት ይገባኛል ብላ፤ ግንቦት 1990 ወርራ የያዘቻት ባድመ እና አካባቢዋ አሁን ኮሚሽኑ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት የኢትዮጵያ ግዛት ናቸዉ።»

ትልቁ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ቢያንስ የአዲስ አበባን ሕዝብ በዉሸት ባደባባይ አስጨፍረዉታል።የኢትዮጵያ ገዢዎች ዋሹ ወይም ተሳሳቱ ካልን አዲስ አበቦችም በርግጥ ለመጨፈር ቸኮለዉ ነበር ማለታችን ሐቅ ነዉ።

የድንበር አካላይ ኮሚሽኑ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት ኢትዮጵያ እስከ ጦርነቱ ድረስ ከምትቆጣጠረዉ ግዛት  በርካታ አካባቢዎች በኤርትራ ግዛዛት ተካለዋል።ከጦርነቱ በኋላ ከሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) አባልነት የተባረሩት የቀድሞ የፓርቲዉ መሪዎች እንደፃፉት በኮሚሽኑ ዉሳኔ መሰረት ባድመ የኢትዮጵያ አይደለችም። የዛላ አንበሳ አካባቢ የኢትዮጵያ ግዛት አይደለም። የኢሮብ እና የአፋር ሕዝብ ከሠፈሩበት አካባቢዎችም የተወሰኑት የኢትዮጵያ ግዛቶች አይደሉም። ባጠቃላይ ወደ 800 ካሬ ኪሎ ሜትር ግዛት  ኢትዮጵያ አጥታለች።

Eritrea Bevölkerung feiert Referendum 1993
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

የድንበር አካላዩ ኮሚሽን ዉሳኔ ይግባኝ የማይባልበት ገዢ ወይም አሳሪ በመሆኑ አልቀበልም ማለት አይቻልም። ሁለቱም ሐገራት ዉሳኔዉን ተቀብለዋል። ለግቢራዊነቱ ግን ድርድር እንዲደረግ ኢትዮጵያ እስካለፈዉ ሳምንት ስትጠይቅ ነበር። ኤርትራ ጥያቄዉን አልተቀበለችዉም። የሁለቱ መንግሥታት አቋም የአልጀርሱ ስምምነት የፈነጠቀዉን የሠላም ተስፋ ጨርሶ አጨናጉሎታል።

ባለፈዉ ሳምንት ግን ዶክተር አብይ አሕመድ የሚመሩት የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዴግ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት  የድንበር አካላይ ኮሚሽኑን ዉሳኔ ሙሉ በሙሉ ገቢር እንደሚያደርግ ወስኗል። ዉሳኔዉን የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዉድቅ አድርገዉታል። የኢሮብ እና የባድመ ነዋሪዎችም ባደባባይ ሰልፍ ተቃዉመዉታል። ብዙዎች ግን ለሠላም ጠቃሚ ይሉታል።

ናይጄሪያ እና ካሜሩንን ያወዛግቡ የነበሩ አዋሳኝ ግዛቶች ሲካለሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዋሳኝ ቡድን አባል የነበሩት ኢትዮጵያዊዉ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ያቆብ ኃይለማርያም እንደሚሉት ግን አሁን ያለዉ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰነዉን ከመወሰን ዉጪ ምርጫ የለዉም።                               

ኤርትራዊቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ወይዘሮ ሠላም ኪዳኔ እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግስት ዉሳኔ ተስፋ ሰጪ ነዉ። የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባሳለፈዉ ዉሳኔ መሠረት የድንበር ኮሚሽኑ ከዚሕ ቀደም ካርታ ላይ በቀለም ያሰመረዉ ድንበር በሁለቱ ሐገራት መሬት መሐል ይከለላል። እንደገና ዶከተር ያቆብ።

                                   

 የኤርትራ መንግስት  እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ በይፋ ያለዉ ነገር የለም። ከዚሕ ቀደም ግን ኢትዮጵያ ዉሳኔዉን አክብራ በኃይል ከያዘችዉ ግዛት ለቅቃ መዉጣት እንጂ «ድርድር አስፈላጊ አይደለም» በማለት በተደጋጋሚ አስታዉቋል። ዶክተር ያቆብ እንደሚሉት ግን ካለድርድር ድንበር ማካለል አይቻልም። ኢትዮጵያም የወድብ ጥያቄ ማንሳት አለባት።የኤርትራ መንግሥትን የሚቃወመዉ የኤርትራ አፋር የስደት መንግስት የተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዓሊ መሐመድ ዑመር የሁለቱ ሐገራት ዉዝግብ በድርድር መፈታቱን ድርጅታቸዉ ይደግፈዋል። ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ ብትጠቀም ድርጅታቸዉ ይደግፋልም።ይሁንና  አቶ ዓሊ እንደሚሉት የትኛዉም ድርድር ባለቤቱን አፋርን ማካተት አለበት።

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲን  ዉሳኔ አቶ ዓሊ እንደሚሉት ለሠላም ጠቃሚ ነዉ።የኤርትራ መንግሥትን ዝምታ እና የእስካሁን ምክንያት ግን «ሥልጣኑን ለማራዘም» ብለዉ ያስባሉ። ወይዘሮ ሠላም ኪዳኔም ግን ብዙ ይጠብቃሉ።

Äthiopien Proteste gegen die EEBC-Entscheidung
ምስል DW/A. Desta

የፖለቲካ  ተንታኝ አብዱረሕማን ሰዒድ ግን የኤርትራ መንግስት ከሕዝብ የቀረበ እና የሚቀርብለትን ጥያቄ መቀበሉን ይጠራጠራሉ። የኢትዮጵያ መንግስትን ዉሳኔን ግን ያወድሱታል።

ዶክተር ያቆብ እንደሚሉት ከእንግዲሕ ኳሷ ኤርትራ መንግሥት ሜዳ ላይ ናት። አስመሮች ያጎኗት ይሆን ወይስ ይዘብጧት። እናስ ወዴት? ለማየት-መስማት ያብቃን። ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ