1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ በዋጋ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ምን ይፈልጋል?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥር 29 2016

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂክ ዕቅድ ከተካተቱ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ነው። ለፖሊሲው ተግባራዊነት ብሔራዊ ባንክ “ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ” ሆኖ መቋቋም እንደሚኖርበት ባለሙያዎች ይናገራሉ። መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲገጥመው የሚበደረውን የገንዘብ መጠን በኃይል መገደብንም ይሻል

https://p.dw.com/p/4c8LO
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
ከተመሠረተ 80 ዓመታት ያስቆጠረው ብሔራዊ ባንክ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ የሚያደርገው ሽግግር በኢትዮጵያ የባንክ ሥራ ታሪክ ከሚጠቀሱ ዐበይት ለውጦች አንዱ እንደሚሆን የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ።ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ በዋጋ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ምን ይፈልጋል?

በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የዋጋ ንረትን “ዝቅተኛ እና የተረጋጋ” አድርጎ ለመቆጣጠር ያቀደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚከተለውን የገንዘብ ፖሊሲ በመቀየር ላይ ይገኛል። ይኸ የፖሊሲ ለውጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከ2016 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ተግባራዊ በሚያደርገው ስትራቴጂክ ዕቅድ ከተካተቱ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ነው።

ከዓመት በፊት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ሆነው የተሾሙት አቶ ማሞ ምህረቱ “አሁን ያለውን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በዋጋ ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ማሸጋገር ቁልፍ ዓላማችን ነው” ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል።

ከተመሠረተ 80 ዓመታት ያስቆጠረው ብሔራዊ ባንክ በወለድ ተመን ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ የሚያደርገው ሽግግር በኢትዮጵያ የባንክ ሥራ ታሪክ ከሚጠቀሱ ዐበይት ለውጦች አንዱ እንደሚሆን የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይናገራሉ።

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር “ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ያላቸውን ተቀማጭ በመቆጣጠር አጠቃላይ ኤኮኖሚ ውስጥ ያለውን ገንዘብ መቆጣጠር ይቻላል የሚል አካሔድ” ሲከተል እንደቆየ ዶክተር አብዱልመናን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂክ ዕቅድ “ይኸን [አካሔድ] ሙሉ በሙሉ በመተው የወለድ ምጣኔን በመቆጣጠር የባንክ ብድርን መቆጣጠር ይቻላል” እንደሚል የገለጹት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ሽግግሩ “ከዚህ በፊት እንከተል ከነበረው መሠረታዊ ለውጥ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ብሔራዊው ባንክ ለሚያደርገው የፖሊሲ ለውጥ ግን ከዚህ ቀደም ባለሙያዎች እንደወተወቱት “ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ” ሆኖ መቋቋም ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲያጋጥመው ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን የገንዘብ መጠን መገደብ ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት ሌላው አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታ ነው።

“መንግሥትም፣ ብሔራዊ ባንክም ባንኪንግ ኢንደስትሪው ውስጥ ጣልቃ የሚገቡትን ነገር መተው መቻል አለባቸው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ጣልቃ ገብነት ከቁጥጥር እና ክትትል ጋር አይሔድም” እያሉ ይሞግታሉ። “በባንኮች የብድር አሰጣጥ እና የብድር ዋጋ አተማመን ላይ መንግሥት ጣልቃ መግባት የለበትም” የሚል አቋም ያላቸው ዶክተር አብዱልመናን “ይኼን ለማድረግ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ነጻ መሆን ያስፈልገዋል” ሲሉ ተናግረዋል። “መንግሥት እንደፈለገ ከብሔራዊ ባንክ የሚበደር ከሆነ እጠቀምበታለሁ ያለው በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ አይሰራም” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን መክረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ “አሁን ያለውን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ በዋጋ ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ማሸጋገር ቁልፍ ዓላማችን ነው” ሲሉ ናግረዋል።ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

አቶ ማሞ ምህረቱ “አዲስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ” መዘጋጀቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ተናግረዋል። ረቂቁ “የብሔራዊ ባንክ አንጻራዊ ነጻነቱን ጠብቆ፣ ግልጽ የሆነ አሰራር መሥርቶ፣ ተጠያቂ ሁኖ ቁልፍ የዋጋ ማረጋጋት ዓላማዎቹን እንዲያሳካ የሚያስችል” እንደሆነ የገለጹት ማሞ “ይኸን በቅርብ ጊዜ ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በአዋጁ ላይ የሚደረግ ለውጥ “ምን አልባት ነጻ የሆነ ማዕከላዊ ባንክ የመፍጠርን ሐሳብ ያለመ” ሊሆን እንደሚችል ዶክተር አብዱልመናን ይገምታሉ። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነጻ ሆኖ “የሚሰራበት ማዕቀፍ እና አጠቃላይ አካሔዱ ከተለወጠ” ሽግግሩ ጉልህ እንደሚሆን እምነት አላቸው። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የሚደረግ ማሻሻያ የተቋሙን ነጻነት ካላረጋገጠ እንዲሁም መንግሥት የሚበደረውን የገንዘብ መጠን ካልገደበ “ምንም ጥቅም የሌለው ጉዳይ” እንደሚሆን ዶክተር አብዱልመናን ያስጠነቅቃሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቋማዊ ነጻነቱን ከማስጠበቅ እና መንግሥት ለበጀት ጉድለት መሸፈኛ የሚበደረውን የገንዘብ መጠን ከመገደብ ባሻገር ግን አዲሱን የገንዘብ ፖሊሲ አተገባበር የሚፈታተኑ ጉዳዮች አሉ።

“የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ አጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቱን ማሻሻል ይፈልጋል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበያው ያለው ግዙፍ ድርሻ ተግዳሮች ሊፈጥር እንደሚችል ይጠቅሳሉ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “እንደ ፖሊሲ ባንክ” የሚወሰድ በመሆኑ “መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የሚያደርግ እና የገበያ ባልሆነ ሕግ እንዲመራ የሚፈቅድ ነው” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው በንግድ ባንክ ላይ ማሻሻያ ተግባራዊ ካልተደረገ “ግዙፍ የመንግሥት ባንክ መኖሩ ትልቅ ችግር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
እንደ መንግሥት የፖሊሲ ባንክ የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበያው ያለው ግዙፍ ድርሻ ለአዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ ተግዳሮት ሊፈጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

በዝቅተኛ የወለድ መጠን “ብድር የተሰጣቸው ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት” ጉዳይ ሌላው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱን የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ ፈተና ሊደቅን የሚችል ነው። “ለምሳሌ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲውን ለማስፈጸም ወለዱን በጣም ከፍ ቢያደርገው ንግድ ባንክ ምን ሊያደርግ ነው?” ሲሉ የሚጠይቁት ዶክተር አብዱልመናን አበዳሪው “[የተበደሩ የመንግሥት] ተቋማት ላይ ሊጨምርባቸው አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰኔ 2016 የዋጋ ንረትን ከ20 በመቶ በታች ለማውረድ አቅዷል። የባንኩ ዕቅድ የዋጋ ንረትን በ2017 ወደ 10 በመቶ ከዚያም በ2018 ወደ 8 በመቶ የማውረድ ህልም አለው። ይኸን ዕቅድ ማሳካት ግን ብሔራዊውን ባንክ በኃይል የሚፈትን ነው።

ለሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ስትራቴጂክ ዕቅድ ኢትዮጵያን በኃይል የሚፈታተናትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሒደት ለማቃለል ያስችላል የተባለ ውጥን ጭምር የተዘጋጀበት ነው። በሰነዱ መሠረት ኢትዮጵያ በ2016 ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለአንድ ወር ሸቀጥ ከዓለም ገበያ ለመሸመት የሚበቃ ብቻ ነው። ባንኩ ይኸን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በ2017 ለሁለት ወራት ሸቀጥ መሸመት የሚያስችል ለማድረግ አቅዷል።

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማሻሻል ግን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥራ ብቻ የሚከወን አለመሆኑ ግን የዕቅዱን ስኬታማነት የሚገዳደር ነው። የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከሀገሪቱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ፤ የግብርና ምርታማነት፣ የወጪ እና ገቢ ንግድ እንዲሁም የብድር ሁኔታ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አብዱልመናን “ጉዳዩ በብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ሥር ነው የሚል ዕምነት የለኝም” ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ገበያ ድንች ሽንኩርት እና ብር ይታያል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰኔ 2016 የዋጋ ንረትን ከ20 በመቶ በታች ለማውረድ አቅዷል። የባንኩ ዕቅድ የዋጋ ንረትን በ2017 ወደ 10 በመቶ ከዚያም በ2018 ወደ 8 በመቶ የማውረድ ህልም አለው።ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስትራቴጂክ ዕቅድ 3 ዋና ዋና ግቦች፣ 5 ዓላማዎች፣ 22 የድርጊት መርሐ-ግብሮች እና 25 አሐዛዊ የአፈጻጸም መለኪያዎች ያሉት ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ስትራቴጂክ ዕቅድ በመጪው ሰኔ 2016 “አዲስ ወይም የተሻሻለ የባንክ፣ የመድን ዋስትና፣ የሊዝ እና የማይክሮ ፋይናንስ አዋጆች” እንደሚዘጋጁ ያትታል።

በተለይ በባንክ ሥራ አዋጅ ላይ የሚደረገው ማሻሻያ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ በር የሚከፍት መሆኑን ገዥው ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል። የኢንሹራንስ ዘርፉ በአንጻሩ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋጣጣሪ ኤጀንሲ ይቋቋምለታል።

ዶክተር አብዱልመናን “ብሔራዊ ባንክ ከዚህ በፊት በጣም ድብቅ የሆነ ተቋም ነው ማለት ይቻላል” ሲሉ ይተቻሉ። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “የሚወጡት መረጃዎች በጣም የዘገዩ፣ ከህብረተሰቡ፣ ከሚዲያ እና አጠቃላይ ከኢንዱትሪው ጋር የገንዘብ ፖሊሲን በተመለከተ ያለ ኮምዩንኬሽን በጣም ዝግ ነው ማለት የሚቻል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ለዶክተር አብዱልመናን ተስፋ ሰጥቷቸዋል። “ስትራቴጂክ ዕቅዱ ግልጽነትን፣ ኮምዩንኬንሽንን የሚያበረታታ” እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አብዱልመናን “ውሳኔ አሰጣጡ በጣም በብዙ መረጃ ላይ የተመረኮዘ” እንዲሁም አጠቃላይ የገንዘብ ፖሊሲው በአዲስ አቅጣጫ የሚመራ እንደሆነ ተስፋቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ