የኤርትራዉ ፕሬዚደንት ለጉብኝት መቃዲሾ ናቸዉ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 4 2011የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለመጀመርያ ጊዜ ሶማልያን ለመጎብኘት መቃዲሾ ገቡ። የሶማልያዉ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ በመቃዲሾ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ማረፍያ ተገኝተዉ አቀባበል አድርገዉላቸዋል። የኤርትራዉ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ቢሮ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ከጀመረች ወዲህ በቀጠናዉ ሌላ ፈጣን ግንኙነት መጀመሩን አመላካች ነዉ ሲል አስታዉቋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ መቃዲሾ ዓለም አቀፍ የአዉሮፕላን ማረፍያ ሲደርሱ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ እንደነበር የሮይተርስ የዜና ወኪል የዓይን እማኞች ከቦታዉ ጠቅሶ ዘግቧል። ይህ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ታሪካዊ ጉብኝት የሦስቱ ሃገራት መንግሥታት ማለትም የኢትዮጵያ፤ የኤርትራና እና የሶማልያ መሪዎች ከዚህ ቀደም ያካሄዱት ጉባዔ አካል ነዉ ሲሉ የኤርትራዉ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ባሰራጩት መረጃ ገልፀዋል። ኢትዮጵያ፤ ኤርትራና ሶማልያ በመካከላቸዉ የነበረዉን የሻከረ አልያም ቀዝቃዛ ግንኙነት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈዉ ሚያዝያ ወር ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግንኙነታቸዉን ማደስ መጀመራቸዉ ይታወቃል። የኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ግንኙነት ከተጠናከረና በአፍሪቃዉ ቀንድ ያለዉ ሁኔታ መሻሻል ካሳየ በኋላ ሶማልያና ኤርትራ የዴፕሎማቲክ ግንኙነታቸዉን ለመመስረተት እቅድ እንዳላቸዉ ባለፈዉ ሐምሌ ወር ማስታወቃቸዉ አይዘነጋም። ከስልጣን የወረደዉ ያለፈዉ የሶማልያ አስተዳደር ኤርትራ በሶማልያ የሚንቀሳቀሰዉን የደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን ታስታጥቃለች ሲል ቢወነጅልም፤ ዉልነጀላዉን የአስመራዉ መንግሥት ሃሰት ሲል በተደጋጋሚ ማጣጣጣሉ አይዘነጋም። ይህንኑ የሶማልያ መንግሥት ዉንጀላ ተከትሎ የአስመራዉ መንግሥት ጠላት ከሆነዉ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተቀነባበረ የሃሰት ዉንጀላ ነዉ ሲል መልስ መስጠቱም ይታወሳል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ