1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ዜና፤ ጥር 1 ቀን፤ 20217 ዓ.ም ሃሙስ

ሐሙስ፣ ጥር 1 2017

DW Amharic አርስተ ዜና --የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት፣ በአክሱም ከተማ ትምህርት ቤቶች ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የከተማዋ ትምህርት ቢሮ የጣለውን እገዳ ለማስነሳት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን አስታወቀ።-የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ሥርዓትን የሚደነግግ አዋጅ አፀደቀ፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን ለመንግስት ለማስመለስ ያስችላል የተባለም አዋጅም ጸደቋል። የንብረት ማስመለስ አዋጅ "የፖለቲካ ማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን" ተጠይቋል። በጀርመን ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ቤት አልባ ናቸው ሲል የጀርመን ፌደራል መንግስት አኃዛዊ መረጃ ተቋም ይፋ አደረገ።

https://p.dw.com/p/4ozYC

ኢትዮጵያ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት አዋጆችን አጸደቀ

የንብረት ማስመለስ አዋጅ "የፖለቲካ ማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን" በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተጠየቀ። ዛሬ ጥር 1 ቀን በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው ይህ አዋጅ "የተወሰኑ ግለሰቦችን፣ እና ቡድኖችን ለማጥቃት ከፖለቲካ ፍላጎት የመነጨ ነው" በሚል ተቃውሞ ተነስቶበታል። የፍትሕ ተቋማት "ገለልተኛነት እና የማስፈጸም አቅም" ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት በዚህ ጊዜ ይህንን ሕግ ማጽደቅ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተው ነበር። 
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ጉባዔ፤ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ሥርዓትን የሚደነግግ አዋጅ አጽድቋል፡፡ የነዳጅ ውጤቶች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ስላላቸው እና ስትራቴጂካዊ ምርት በመሆናቸው አዋጁ አስፈላጊ መሆኑ በምክር ቤቱ ስብሰባ ተጠቅሰዋል፡፡ አዋጁ የነዳጅ ውጤቶች ከአስመጪዎች እስከ ተጠቃሚው እሰኪደርሱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለመደገፍ እንደሚያስችል  እና ተደራሽነቱም ፍትሃዊና ቀልጣፋ እንዲሆን የሚያደርግ እንደሆነም ተመልክቷል። ዜና መጽሔት ዝርዝሩን ይዟል። 

የትግራይ እስልምና ጉዳዮች የተማሪዎችን ሂጃብ ጉዳይ ወደ ሕግ እንደወሰደው አስታወቀ።

በአክሱም የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ በመልበሳቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታ ታግደዋል ያለዉ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት፥ ጉዳዩን ወደ ሕግ እንደወሰደው አስታወቀ። የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ትላንት ማታ ባሰራጨው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ 159 የሚሆኑ በአክሱም ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤቶች እንዳይገቡ የተጣለ ክልከላ አሁንም አለመነሳቱን እና በዚህ ምክንያትም የ12ተኛ ክፍል ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ዩኒቨርስቲ የመግባት ዕድላቸው ተዘግቶባቸው ብሏል። 
ጠቅላይ ምክርቤቱ ይህ ክልከላ ሃይማኖታዊ እና ዓለማዊ የሰው ልጆችን መብት የሚፃረር ብሎታል።  ችግሩን ለመፍታት የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት፥ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢካሄድም አንዳንድ ባላቸው 'የራሳቸው ሃይማኖታዊ ፍላጎት እና የትምህርት የመማር መብት' የተደበላለቀባቸው አካላት አደናቃፊነት የሙስሊም ሴት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸውን ጨምሮ ገልጿል። 
በዚህም ምክንያት ጉዳዩ ወደ ሕግ እንዳመራው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታውቋል። በአክሱም ከተማ ትምህርት ቤቶች በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተኖረው ክልከላ የሴቶች መብት ጥሰት እንዲሁም ትምህርት የመማር መብት የሚፃረር ሲል መግለጫው ጨምሮ ጠቁሟል። 
በአክሱም ከተማ የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ተቋማቱ እንዳይገቡ ማገዳቸው ተከትሎ 159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች አንድ ወር ገደማ ለሚሆን ግዜ ከትምህርት መራቃቸው የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት በቅርቡ ለዶቼቬለ መግለፁ የሚታወስ ነዉ። ምክር ቤቱ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ችግሩን መፍታት አልቻለም ሲል ወቅሷል። 
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጉዳዩን አስመልክቶ ለአክሱም ከተማ ትምህርት ፅሕፈት ቤት በሚል ደብዳቤ አሰራጭቶ ነበር። የትግራይ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ፥ በአክሱም ከተማሪዎች የአለባበስ ስርዓት ጋር በተገናኘ፥ አስቀድሞ ከአክሱም እስልምና ጉዳዮች ቀጥሎም ከትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ቅሬታዎች እንደደረሱት ገልጿል። ይሁን እና 'አዲስ አሰራር ባልወጣበት፥ አዲስ ክልከላም ይሁን አዲስ ጥያቄ' ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሶ ትምህርት ቤቶች፤ በነባር የአለባበስ ስርዓት እንዲቀጥሉ ሲል አስታዉቆ እንደነበር የሚታወስ ነዉ። 

ዩናይትድ ስቴትስ፤ ከፍተኛ የደንቃ ጠሎ በሆሊዉድ

በዩናይትድ ስቴትስ ሎስአንጀለስ ክልል በሚገኝ ደን ዉስጥ በተቀሰቀሰ ከቁጥጥር ዉጭ የሆነ ሰደድ እሳት፤ በተለይ  በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ከፍተኛ የአቧራ ክምችቶችን ጨምሮ የአየር ብክለት ማስከተሉ ተሰማ። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የካሊፎርንያ የተከሰተዉን ከፍተኛ የደን ቃጠሎ ተከትሎ ወደ ጣሊያንን ያቀዱትን ጉዞ ሰርዘዋል። በቃጠሎው በዩናይትድ ስቴትስ የታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ መኖርያ ቤቶች  መውደማቸዉ እየተዘገበ ነዉ። እስካሁን በቃጠሎዉ በትንሹ የአምስት ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ዶቼ ቬለ DW ዘግቧል።  በክልሉ አምስት ዋና ዋና የእሳት ቃጠሎ ቦታዎች ላይ ወደ 1,900 የሚጠጉ ሕንፃዎች ወድመዋል፤ ወደ 130,000 ሰዎች ቦታዉን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል ። በሽዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት እየተረባረቡ መሆኑም ተነግሯል። ከሦስት ቀናት በኋላ ቀጠሮ የተያዘለት ዓመታዊ ግዙፉ የሆሊዉዱ የኦስካር የሽልማት መድረክ በርካቶች በሰደድ እሳቱ ቤታቸዉን ጥለዉ ቦታዉን መልቀቅ በመገደዳቸዉ ምክንያት የሽልማት መድረኩ፤ ወደ ጥር 18 ቀን መተላለፉም ተሰምቷል። ትናንት ረቡዕ በሆሊውድ ኮረብቶች ላይ የተቀሰቀሰው አዲስ የሰደድ እሳት አደጋ ቦታዉ ላይ የሚገኙትን ቱሪስቶችን ብሎም የቱሪስት መስዕብ ቦታዎችን ሁሉ አደጋ ላይ መጣሉ እየተዘገበ ነዉ።  

ጀርመን፤ ዜሌንስኪና ምዕራባዉያን አጋሮቻቸዉ በራምሽታይን ጉባዔ 

ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ እና ምዕራባዉያን አጋሮቻቸዉ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምቻታቸዉ በፊት ለዩክሬን የመጨረሻ የርዳታ ለማሰባሰብ ዛሬ ጀርመን ላይ ጉባዔ ተቀምጠዋል። ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬይን ሩስያ ግጭት የአሜሪካንን ሚና መተቸታቸዉ ይታወቃል። 
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እና የምዕራቡ ዓለም አጋሮቻቸዉ ዛሬ በደቡብ ምዕራብ ጀርመን በሚገኘው የአሜሪካ የጦር አየር ማረፍያ «ራምስቴይን» ላይ ጉባዔያቸዉን በማካሄድ ላይ ናቸዉ።   የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ቮላድሚር ዜሌንስኪ "ቁልፍ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የአየር መከላከያ ስርዓታችንን ማጠናከር እና ቢያንስ የሩሲያ ወታደራዊ አየር ጥቃቶችን ከከተሞቻችን እና ከድንበሮቻችን ማራቅ እንደምንችል ማረጋገጥ ነው" ሲሉ በ X ገጻቸዉ ላይ ጽፏል።
እየተካሄደ በሚገኘዉ ጉባኤ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለዩክሬይን 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ አዲስ ወታደራዊ ዕርዳታን ጨምሮ የአየር መከላከያ ሚሳኤሎች፣ ከአየር ወደ ምድር የሚምዘገዘጉ ሚሳይሎች እንዲሁም ለኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች የሚያገለግሉ መለዋወጫ መሣሪያዎችን የሚካትት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት እና ምዕራባዉያኑ አጋሮቻቸዉ ዛሬ እያካሄዱ ባሉት ጉባዔ የዩናይትድ ስቴትሱ  ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ጥር  12  ወደ ነጩ ቤተመንግሥት ከመመለሳቸው በፊት የዛሬዉ የመጨረሻ ጉባዔያቸዉ እንደሚሆንም ታዉቋል። ይህ የዛሬዉ ጉባዔ  ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸዉ በፊት የኪየቩ መንግሥት ርዳታ እንዲያገኝ አስፈላጊዉ ግፊት ይሆናልም ተብሎ ታይቷል። ወደ ስልጣን የሚመጡት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ እንደ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ጆ-ባይደን ለዩክሬይኑ ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ ጥሩ እይታ ላይኖራቸዉ ይችላል የሚል ጥርጣሬም አለ። 

ቻይና፤ አዲስ ተላላፊ በሽታ መገኘቱ ተገለፀ

የቻይና የጤና ባለስልጣናት ኤም ፖክስ የተባለ አዲስ ተላላፊ በሽታ ማግኘታቸዉን ዛሬ አስታወቁ። ይህ በተለያዩ የዓለም ሃገራት እንደተሰራጨ የተነገረዉ ቫይረስን ተከትሎ የዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የጤና አደጋ ሲል ባለፈዉ ዓመት ማስጠንቀቅያ ማወጁ የሚታወስ ነዉ።  ሮይተርስ የቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ይፋ ያደረገዉን መረጃ ጠቅሶ ዛሬ እንደዘገበዉ፤ አዲስ ተገኘ የተባለዉ ተላላፊ በሽታ ወደ ተለያዩ ቦታዎች የተጓዘ እና ተቀማጭነቱን በዲሞክራቲክ ኮንጎ አድርጎ ከነበረ ከአንድ የዉጭ ሃገር ዜጋ መተላለፉን ያመለክታል።  ኤም ፖክስ የተሰኘዉ ተላላፊ በሽታ በቅርብ ግንኙነት እና ንኪኪ የሚተላለፍ ፤ የመተንፈሻ አካልን የሚጎዳ ጉንፋን አይነት ስሜት ያለዉ ፤ በሰዉነት ላይ መግል የተሞሉ የቁስል ምልክቶች የሚታዩበት እና በተለምዶ ቀላል ቢባልም አልፎ አልፎ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ተመልክቷል። የዓለም ጤና ድርጅት በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ (DRC) የተስፋፋው ኤምፖክስ ወረርሽኝ ወደ ጎረቤት አገሮች መስፋፋቱን ተከትሎ በሁለት ዓመት ጊዜ ዉስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ባለፈው ነሐሴ ወር ዓለም አቀፍ ለጤና አደጋ ሲል ማስጠንቀቅያ አዉጆም ነበር።  

ጀርመን፤ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ቤት አልባ ናቸው

በጀርመን ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ቤት አልባ ናቸው ሲል የጀርመን ፌደራል መንግስት አኃዛዊ መረጃ ተቋም ይፋ አደረገ። መስርያ ቤቱ ትናንት ባወጣዉ መረጃ፣ በጀርመን 531,600 ሰዎች ቋሚ የመኖርያ ቦታ የላቸዉም። ከነዚህ መካከል 439,500 ሰዎች ለድንገተኛ ጊዜ በተዘጋጁ መኖርያ ቤቶች ዉስጥ የሚኖሩ ናቸዉ። ሌሎች 60,400 ሰዎች ደግሞ ከቤተ-ዘመዶቻቸዉ ጋር ተዳብለዉ ይኖራሉ። የጀርመን አኅዛዊ መረጃ ተቋም ይፋ ሌሎች በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጀርመን ዉስጥ በጎዳና ላይ አልያም በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚኖሩ ያወጣዉ መረጃ ያሳያል።  በዚህም ጀርመን ውስጥ ቋሚ የመኖርያ ቤት የሌላቸዉ 531,600 ሰዎች ይገኛሉ ሲል ተቋሙ አስታዉቋል።  

 

 


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።