1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 22 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 22 2013

ኤቨርተን ዛሬ ማታ ወሳኝ ግጥሚያውን ያከናውናል። ከበላዩ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ከተደጋጋሚ ሽንፈት በኋላ ለድል በቅቷል። ማንቸስተር ሲቲ ዘና ብሎ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተኮፍሷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ኮሎኝን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያንኮታኮተው መሪው ባየር ሙይንሽን ከላይፕትሲሽ ጋር በተቀራራቢ ነጥብ ልዩነት ተፋጧል።

https://p.dw.com/p/3q4Pv
Deutschland Bundesliga Hertha BSC gegen RB Leipzig
ምስል AFP/O. Andersen

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ኤቨርተን ዛሬ ማታ ወሳኝ ግጥሚያውን ያከናውናል። ከበላዩ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ከተደጋጋሚ ሽንፈት በኋላ ለድል በቅቷል። ማንቸስተር ሲቲ ዘና ብሎ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተኮፍሷል። በጀርመን ቡንደስሊጋ ኮሎኝን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያንኮታኮተው መሪው ባየር ሙይንሽን ከላይፕትሲሽ ጋር በተቀራራቢ ነጥብ ልዩነት ተፋጧል። በሻምፒዮንስ ሊጉ ጀርመንን ከወከለው ሌላኛው ቡድን ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር የፊታችን ቅዳሜ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት ይጠበቃል። ዶርትሙንድ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ፤ ባየር ሙይንሽን በሳምንቱ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ለመጫወት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል። በጎልፍ ስፖርት ታሪክ የዘመናችን ድንቅ ተጨዋች ታይገር ውድስ ከደረሰበት የተሽከርካሪ አደጋ ለመዳን ረዥም ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችል ተዘግቧል። የእንግሊዝ ዝነኛ የእግር ኳስ ተጨዋች የነበረው ዴቪድ ቤክሃም አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲን ወደ ኢንተር ሚያሚ ለማስመጣት ምኞት እንዳለው ገልጧል። 

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለመያዝ የሚረዳውን ውጤት ለማግኘት ዛሬ ማታ ኤቨርተን ከሳውዝሀምፕተን ጋር ይጋጠማል። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ40 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኤቨርተን የዛሬውን ጨዋታ ቢያሸንፍም ግን በግብ ክፍያ በሊቨርፑል ስለሚበለጥ በነጥብ ተስተካክሎ እዛው 7ኛ ደረጃው ላይ ነው የሚቆየው። በሚቀጥለው ሌላ ተስተካካይ ጨዋታው ግን 14ኛ ደረጃ ላይ ያለው ሳውዝሀምፕተንን አሸንፎ የሊቨርፑልን ቦታ የመረከብ ዕድል አለው። ሊቨርፑል በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሼፊልድ ዩናይትድን 2 ለ0 ድል አድርጓል። የሊቨርፑሉ አማካይ ኩርቲስ ጆንስ ትናንት ያስቆጠረው ግብ ለግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር አባት መታሰቢያ ነው ብሏል። ባለፉት ግጥሚያዎች ያልተጠበቊ ድክመቶችን በማሳየት ለሊቨርፑል ሽንፈቶች ሰበብ የነበረው ግብ ጠባቂ አባት የ57 ዓመቱ ሆዜ ቤከር ደቡብ ብራዚል ውስጥ ከሚገኘው የረፍት ጊዜ ቤት አቅራቢያ በጎርፍ ተወስደው ሕይወታቸው አልፏል።

Britain Soccer Premier League Fußball Crystal Palace vs Leicester City
ምስል Marc Atkins/AP/picture alliance

የሊቨርፑል አሰልጣኝ ከአራት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ባገኙት የትናንትና ድል የቡድናቸው ሞራል እንደሚነቃቃ ተናግረዋል። 43 ነጥብ ይዘው አሁን ያሉበት የ6ኛ ደረጃም ለክፉ የሚሰጥ አለመሆኑን ገልጠዋል። የአውሮጳ ሊግ ቦታን አምስተኛ ደረጃ ላይ ኾኖ የያዘው ቸልሲ ሊቨርፑልን የሚበልጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። በተለይ ሊቨርፑል እና ቸልሲ የፊታችን ሐሙስ የሚያደርጉት ግጥሚያ በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። ቸልሲ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ትናንት ባደረጉት ውድድር ያለምንም ግብ መለያየቱ ጎድቶታል። በሁለቱም በኩል ለማሸነፍ ጥረት የታየበት ፈጣን ጨዋታ ነበር።

ለሻምፒዮንስ ሊግ ወደፊት ለመግባት በፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ካሉት ቡድኖች አራተኛውን የያዘው ዌስት ሐም ዩናይትድም ነጥቡ 45 በመሆኑ ከቸልሲ፣ ሊቨርፑል እና ኤቨርተን ብርቱ ፉክክር ይጠበቃል። ቶትንሃም እና አስቶን ቪላ ከሊቨርፑል በአንድ ነጥብ ብቻ አንሰው ደረጃቸው 9 እና 10 ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ 50 ነጥብ ይዞ በኹለተኛ ደረጃ ላይ ሲሰፍር መሪው ማንቸስተር ሲቲ በ62 ነጥብ ርቆ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ ዌስት ሐምን 2 ለ1 አሸንፏል። ላይስተር ሲቲ በ49 ነጥብ ደረጃው ሦስተኛ ነው። አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን 3 ለ1 አሸንፏል። በርንሌይ በቶትንሃም የ4 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየር ሙይንሽን በ52 ነጥብ ይመራል። ላይፕትሲሽ በ50 ይከተለዋል። ባየር ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ኮሎኝን 5 ለ1 ነበር ያንኮታኮተው። ላይፕትሲሽ በበኩሉ ከቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር ተጋጥሞ 3 ለ2 በሆነ ጠባብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል።

Fußball Bundesliga 23. Spieltag | Borussia Dortmund vs. Arminia Bielefeld | Jubel Dortmund
ምስል Ina Fassbender/REUTERS

ባየር ሙይንሽን የናፖሊስ እና የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን የመሀል ተከላካይ ካሊዱ ኩላባሊን ለማስመጣት 45 ሚሊዮን ዩሮ ማውጣቱን ካውትኦፍሳይድ የተሰኘው የስፖርት ድረ ገጽ ዘግቧል። በተከላካይ እጦት የሚንገላታው ሊቨርፑል ይኽንኑ ተከላካይ ለማስመጣት ፈልጎ ናፖሊ 100 ሚሊዮን ዩሮ እንዲከፍል ጠይቆት እንደነበረም ዴይሊ ሚረር ዘግቧል።

ቮልፍስቡርግ በ45 ነጥቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሔርታ ቤርሊንን ቅዳሜ ዕለት  2 ለ0 ማሸነፉ በጅቶታል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት 42 ነጥብ ይዞ 4ና ደረጃ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ39 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ዶርትሙንድ ከትናንት በስትያ አርሜኒያ ቢሌፌልድን 3 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። ትናንት ሌቨርኩሰን ከፍራይቡርግ ጋር ተጋጥሞ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል።

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ዮኣኺም ሎይቭ፦ የዓለም ዋንጫ ድል ተቋዳሽ የነበሩ ሦስት ተጨዋቾች ዳግም ወደ ቡድኑ የመመለሳቸው ጉዳይ የተዘጋ አለመሆኑን ዐስታወቊ። የጀርመን ቡድን በኔሽን ሊግ ግጥሚያ በስፔን ቡድን የ6 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ ዋና አሰልጣኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፦ ቶማስ ሙይለር፣ ማትስ ሁመልስ እና ጄሮም ቦኣቴንግ ወደ ቡድኑ ሊመለሱ እንደሚችሉ ጥቁምታ ሰጥተዋል። የባየር ሙይንሽን እና የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተከላካዮች የሆኑት ጄሮም ቦኣቴንግ እና ማትስ ሁመልስ ወቅታዊ ብቃትን አወድሰዋል። አኤርዴ ከተሰኘው የማሠራጫ ጣቢያ እና ከኪከር መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ከብሔራዊ ቡድኑ የተቀነሱት የ32 ዓመት ተጨዋቾች ወደ ቡድኑ ቢመለሱ እንደ ሌዎን ጎሬትስካ እና ዮሹዋ ኪሚሽ ባሉ ወጣቶች ላይ የተፈራው ተጽእኖ አይፈጠርም ብለዋል። እንደውም አጥቂው ቶማስ ሙይለር ኪሚሽ የቡድኑ ሞተር ነው እያለ የሚያደንቅ ነው ብለዋል። ጀርመን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በምታደርጋቸው ሦስት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች እና የአውሮጳ ሻምፒዮንሺፕ ፉክክሮች በቡድኑ የቆየ ልምድ ያካበቱ የቀድሞ ተጨዋቾች ሳያስፈልጓቸው እንዳልቀሩ በዘወርዋራ ፍላጎታቸውን ዐሳይተዋል። ምናልባትም ሩስያ ውስጥ በተከናወነው የ2018 የዓለም ዋንጫ ደካማ ውጤት ያስመዘገበው ቡድናቸው ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንጋፋ ተጨዋቾችን በቀጣይ ግጥሚያዎች ውስጥ እንመለከት ይኾናል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

አትሌቲክስ

ታላቊ ሩጫ በኢትዮጵያ፦ «ቅድሚያ ለሴቶች» የተሰኘ የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ለ18ኛ ጊዜ ለማከናወን ምዝገባ ዛሬ መጀመሩን ዐስታወቀ። በዘንድሮው ውድድር በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ተሳታፊ የሚሆኑት 2000 ሯጮች እና 150 አትሌቶች ብቻ መሆናቸው ተገልጧል። ቀደም ሲል ታቅዶ የነበረው 15000 ሯጮችን ለማሳተፍ ነበር። ከታቀደው ተሳታፊ 13 በመቶው ብቻ ይገኝበታል በተባለው በዘንድሮው  ውድድር  ከምሥራቅ አፍሪቃም ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሏል። የኮቪድ ወረርሺኝን ከግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ ጥንቃቄ መደረጉም ተገልጧል። ለተሳታፊዎች መነሻና መድረሻ ላይ የሚደረጉ የፊት ጭምብሎች፣ የሰውነት ሙቀት መለኪያ እና ጸረ ተሐዋሲ የእጅ ፈሳሾች ይኖራሉ ተብሏል። ውድድሩ ርቀትን በጠበቀ መልኩ እንደሚከናወንም አዘጋጆቹ በላኩልን የኢሜል መልእክት ተጠቅሷል። ተሳታፊዎች በውድድሩ ላይ በተሻለ የአካል ብቃት እንዲገኙ ለማበረታታት በሚል የታላቊ ሩጫ ውድድር አዘጋጆች የአራት ተከታታይ ቀናት የልምምድ መርሀ ግብር ማሰናዳታቸውንም ገልጠዋል። በሳምንታዊ ልምምዱ ቀድመው የተመዘገቡ 50 ሴቶች እንደሚሳተፉም አዘጋጆቹ ዐስታውቀዋል። «ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር» ሩጫ እሁድ መጋቢት 19 ቀን፣ 2013 ዓ.ም መነሻ እና መድረሻውን አትላስ ሆቴል አካባቢ አድርጎ እንደሚከናወን ተገልጧል።

የአሜሪካው ኢንተር ሚያሚ እግር ኳስ ቡድን ባለድርሻ የቀድሞው የእንግሊዚል ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ዴቪድ ቤክሃም የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን እና የባርሴሎና አጥቂ የሆነው ሊዮኔል ሜሲን ወደ ቡድኑ ለማስመጣት ፍላጎት እንዳለው ዐሳውቋል። ሚረር የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ፦ ቤክሃም ከሊዮኔል ሜሲ በተጨማሪ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን እና የጁቬንቱስ አጥቂው ክርስቲያኖ ሮናልዶንም ወደ ኢንተር ሚያሚ ቡድን የማስመጣት ሕልም አለው። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 36 ዓመት ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ የ33 ዓመቱ ነው።

USA I Tiger Woods I Unfall
ምስል KNBC/REUTERS

ጎልፍ

ሰሞኑን የተሽከርካሪ አደጋ የደረሰበት የ45 ዓመቱ የጎልፍ ስፖርት ዝነኛ ታይገር ውድ ለማገገም ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅበት ተገለጠ። በጎልፍ ስፖርት ለ15 ጊዜያት ለድል በመብቃት ዝናን ያተረፈው የጥቁር ዝርያ ያለበት ታይገር ለሕክምና ሎስአንጀለስ ወደሚገኝ ሐኪም ቤት ከተወሰደ በኋላ «በጥሩ መንፈስ ላይ እንደሚገኝም» ተዘግቧል። ታይገር ውድ ባለፈው ማክሰኞ ሲያሽከረክራት በነበረችው ተሽከርካሪ ላይ በደረሰበት አደጋ በሕክምና ላይ ሲገኝ፤ የእግሮቹ ጉዳቶች እያገገሙ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ