1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየካቲት 27 ቀን 2015 ስፖርት

ሰኞ፣ የካቲት 27 2015

በቶኪዮ በተደረገው የ 2023 የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ዴሶ ገልሚሳ እና ኬንያዊትዋ ሮዝመሪ ዋንጂሩ አሽናፊ ሆነው አጠናቀዋል። ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ዳኞች የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ይመራሉ

https://p.dw.com/p/4OK6C
Bundesliga  VfB Stuttgart - FC Bayern München | Eric Maxim Choupo-Moting
ምስል Bernd Feil/MIS/IMAGO

የየካቲት 27 ቀን 2015 ስፖርት

 

በቶኪዮ በተደረገው የ 2023 የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ዴሶ ገልሚሳ እና ኬንያዊትዋ ሮዝመሪ ዋንጂሩ  አሽናፊ ሆነው አጠናቀዋል። የካቲት 26 ቶኪዮ ጃፓን በተካሄደው የ16ኛው የቶኪዮ ማራቶን በወንዶች በተደረገው ውድድር  2  ሰዓት ከዜሮ አምስት ደቂቃ ከ22 ሰከንድ በመግባት ቀዳሚ ሆኖ ድል የተጎናጸፈው አትሌት ዴሶ ገልሚሶ ነው። በተመሳሳይ ሰአት አትሌት ዴሶን ተከትሎ  ሁለተኛ የወጣው መሀመድ ኢሳ  ሲሆን በሦስት ሰከንድ ልዩነት  ተበልጦ አትሌት ፀጋዬ ከበደ  ሦስተኛ በመውጣት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ከአራት ዓመታት በኋላ ከፍተኛ የተሳታፊ ቁጥር የታደመበትን የፓፓን ማራቶን ውድድር ተጨማሪ ውበት ሰጥተውታል።
38 ሺህ ጃፓናውያን እና ዓለም አቀፍ ሯጮች የተካፈሉት ይሕ ውድድር በሴቶች የማራቶን ፉክክርም እንደ ወንዶቹ ሁሉ አፍሪቃውያን አትሌቶች በበላይነት ያጠናቀቁበት ነበር። 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ፣ከ28 ሰከንድ በመግባት ኬንያዊቷ አትሌት ሮዝመሪ ዋንጅሩ አንደኛ በመሆን ስታጠናቅቅ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፀሐይ ገመቹ 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ  ሆናለች።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው  አሸቴ በከሬ፣ 2 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመግባት በዘንድሮ ማራቶን ሦስተኛ በመሆን አጠናቃለች። 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ13 ሰከንድ የገባችው ወርቅነሽ  ኢዶሳ ደግሞ አራተኛ በመውጣት  ውድድሩን ጨርሳለች።

ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ
 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ  ጨዋታዎች የጨዋታ መረሐግብር ማስተካከያ ተደረገባቸው። በድሬደዋ  ከተማ እየተካሄደ ያለው ጨዋታ የውድድሩ መረሐግብር በ15ኛው ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታ ላይ   ባጋጠመ  ከፍተኛ ዝናብ  የመብራት ኃይል እና ሲዳማ ቡና እንደዚሁም ፋሲል ከነማ ከቡና ጋር ያደርጉት የነበረው ጨዋታ እንዲቋረጥ መደረጉን ተከትሎ 16ኛው እና 17ናው ጨዋታ በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ማስገደዱን የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር    አስታውቋል። በመሆኑም ፕሪምየር ሊጉ ነገ ሲዳማ ቡና ከድሬደዋ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመድህን፤ ውድድራቸውን በተያዘላቸው መረሐግብር  መሠረት  ያደርጋሉ።

Deutschland Bundesliga Julian Brandt Dortmund gegen Leipzig
ምስል Ina Fassbender/AFP/Getty Images

ሴቶች ፕሪምየር ሊግ

በ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር 14ኛ ሳምንት ጨዋታ በ በኅዳር ከትናንት በስተያ  የተጀመረ ሲሆን ትናንት 3 ጨዋታዎች ተስተናግደዋል  በተደረገው ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ   አዳማ   ከተማን አንድ ለባዶ ሲረታ፤ ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አንድ እኩል ተለያይተዋል።  የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ በአዋሳ ከተማ እና በ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  መካከል የተደረገ ሲሆን ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋ። በዚህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን  ይዟል።

ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ዳኞች የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ ይመራሉ  

 የ2022/23 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ የማጣሪያ የአራተኛ ዙር የምድብ ጨዋታዎች ተጀመረ።  በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሁለት ክለቦችን በያዘው ምድብ ሦስት ስር ተደልድለው   የሚገኙትን የዩጋንዳው ቫይፐርስ እና የታንዛኒያው ሲምባ ክለብ የፊታችን ማክሰኞ በቤንጃሚን ሞካፖ ስታዲየም  የሚያደርጉትን ጨዋታ አራት ኢትዮጵያዊያን ዓለም አቀፍ ዳኞች እንዲመሩት በካፍ ተመርጠዋል። በአምላክ ተሰማ በመሀል ዳኝነት ፣ ትግል ግዛው እና ተመስገን ሳሙኤል በረዳት ዳኝነት ይኽን ጨዋታ እንዲመሩ ሲመረጡ  በላይ ታደሰ አራተኛ ዳኛ በመሆን ለጨዋታው ተመድበዋል።

Bundesliga VfL Wolfsburg vs Eintracht Frankfurt | Tor Yannick Gerhardt
ምስል Ronny Hartmann/AFP/Getty Images

እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ

በሳምንቱ መጨረሻ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውድድሮች መካከል በአንፊልድ የተስተናገደው ጨዋታ   በፕሪምየር ሊጉ  አዲስ ታሪክ ያስመዘገብ ሆንዋል።  ሊቨርፑል ማንችስተርን  ሰባት ለ ምንም በማሽነፍ የፈረንጆቹ ሚልንየም ከባተ በኋላ እንዲህ የጎል ናዳ ወርዶበት የማያውቀው ማንችስተር ዩናይትድ ከእረፍት በፊት የተሻለ ተንቀቅሶ የቆየ ቢሆንም ከወረደበት መአት ሊታደገው 

የሚችል ሀይል  አልነበረውም።  ትናንት በቁማቸው የተበሉት ማንችስተሮች ጎል ማስተናገድ የጀመሩት የመጀመሪያው  ግማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ነበር። በ 43ኛው ደቂቃ  በአንፊልድ የተካሄደው ይህ ጨዋታ የመጀመሪያው ግማሽ በሊቨርፑል 1 ለ0 መሪነት ሲጠናቀቅ  የቀያይ ሰይጣኖች መጨረሻቸው እንዲህ ይሆናል ብሎ  የጠበቅ አልነበረም ። ሊቨርፑል ለተቀናቃኙ ሀፍረት ያሸከመበት በተመሳሳይ ለአንፊልድ ታዳሚዎች የተዋበ ድል ያከናነበበት የትናንቱ ጨዋታ 7 ለ0 ሲጠናቀቅ የርገን ክሎፕ ቡድናቸው አራተኛ ሆኖ እንዲጨርስ ያላቸውን ምኞት አለምልሞታል።

የጀርመን ቡንድስ ሊጋ

23ኛ የጨዋታ ሳምንቱን በያዘው የጀርመን ቡንዲስ ሊጋ ስቱትጋርትን 2ለ1 የረታው ባየር ሙኒክ   አሁንም የቡንደስ ሊጋውን የደረጃ ሰንጠረዥ በበላይነት እየመራ ነው። ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው ጨዋታ አሽናፊ የሆነው ባየር ሙኒክ በተጋጣሚው ላይ ያገኘው የነጥብ ብልጫ  ቡንደስ ሊጋውን  ከ ቦሪስያ   ዶርትሙንድ መሪነት  ተቀብሎ በጎል ክፍያ ብቻ በልጦ ከላይ እንዲቀመጥ አስችሎታል ።

በሳምንቱ መጨረሻ በነበረ  ጨዋታ ባየርን ሊቨርኩዘን ሀርታ በርሊንን  4 ለ 1 ሲረታ ቮልፍስ በርግ  እና ፍራክፈርት 2ለ 2ዑኒዮን ቤርሊን ከ ኮለን 0 ለ 0  ተለያይተው ነጥብ ተጋርተው ወጥዋል።    ቦሩስያ ዶርትሙንድ   ላይፕዚንግ  2ለ1 አሽንፏል። አሁን የቡንደስ ሊጋውን የደረጃ  ሰንጠረዥ በተመሳሳይ 49 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ በልጦ ባየር ሙኒክ ሲመራው ዶርትሙንድ በግብ ክፍያ ተበልጦ በዕኩል 49 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Symbolbild | Depression im Spitzensport
ምስል JB Autissier/PanoramiC/IMAGO

የሚዳ ቴንስ

የዓለማችን ቁጥር አንድ የሜዳቴንስ ንጉሥ ኖቫክ ጃኮቪች በዚህ ሳምንት ከሚጀመረው የአሜሪካው ኢንዲያና  የሜዳ ቴንስ ውድድር መውጣቱን አስታወቀ።  

የ 22 ጊዜ  ግራንድ ስላም ሜዳቴንስ አሽነፊ ሰርቢያዊው  ጃኮቪች የ ኮቪድ 19 ክትባት ባለመውሰዱ  ከውድድሩ ውጭ መሆኑ ተነግሯል። ማንኛውም አሜሪካዊ ያልሆነ ዜጋ ወደግዛትዋ ሲገባ የኮቪድ 19 ክትባት መውሰድን አስገዳጅ በማድረግዋ የዓለም ቀጥር አንዱ የሜዳቴንስ ተጫዋች ከኢንዲያናው የሜዳቴንስ ውድድር ለሁለተኛ ግዜ ራሱን ለማግለል ተገዷል። የ35 ዓመቱ የሜዳቴንስ ተጫዋች የኮቪድ 19 ክትባትን በተመለከተ በያዘው አቋም ከትላልቅ ውድድሮች ውጭ ሲሆን ይህ ለ4ኛ ግዜ ነው።

Bahrain F1 GP Auto Racing
ምስል Frank Augstein/AP/picture alliance

በፎርሙላ 1 የመኪና ውድድር

በሳምንቱ መጨረሻ በባህሪን በተደረገው የ ፎሩላ 1 የመኪና ሽቅድድም ሬድ ቡል የበላይነት አግኝቷል። ማክስ ቫስቲፈንና ሰርጊዮ ፒሪዝ ከሬድ ቡል አንደኛ እና ሁለተኛ ሲሆኑ ፈርናንዶ አሎኒዞ ከ አስቶን ማርቲን ሦስተኛ በመሆን የባህሪን ግራንድ ፕሪል የፎርሙላ 1 ውድድርን ጨርሷል። በዚህ ውድድር እንግሊዛዊው ሉዊስ ሀሚልተን  ከማርቸዲስ 5 ኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል። ቀጣዩ የሳውድ አረቢያው ግራን ብሪይ የፎርሙላ 1 የመኪና ውድድር ከ 10 ቀን በሁዋላ የሚካሄድ ይሆናል።

ሃና ደምሴ

ሸዋዬ ለገሠ