የየካቲት 29 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ የካቲት 29 2013የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ውጤት ርቆት በደረጃ ሰንጠረዡ እያሽቆለቆለ ነው። ዶርትሙንድን በአንድ ወቅት ከፍ ከፍ አድርገውት የነበሩት ጀርመናዊ አሰልጣኝ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑልን ከገጠመው መከራ ሊታደጉት አልቻሉም። ሊቨርፑልም እንደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ወደ ታች እያሽቆለቆለ ነው። ሁለቱም ቡድኖች ግን በሻምፒዮንስ ሊጉ ፉክክር ከተጋጣሚ ዎቻቸው ብልጫ ዐሳይተዋል። ነገ እና ከነገ በስተያ የመልስ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። በስፔን ላሊጋ የሪያል ማድሪዱ ካሪም ቤንዜማ በስተመጨረሻ ያስቆጠራት ቡድኑን አቻ ያደረገችው ግብ የከተማው ተቀናቃኝ ቡድን አትሌቲኮ ማድሪ ከባርሴሎና ጋር የአምስት ነጥብ እንዳይኖረው ልዩነት ግን እንቅፋት ኹናለች። ላሊጋውን አትሌቲኮ ማድሪድ በ59 ነጥብ ሲመራ፤ ባርሴሎና በ56 እንዲሁም ሪያል ማድሪድ በ54 ነጥቦች ይከተላሉ።
ፕሬሚየር ሊግ
የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በደረጃ ሰንጠረዡ 18ኛ ላይ በሚገኘው ፉልሃም ቡድን ትናንት 1 ለ0 ተሸንፈው ነጥብ ማጣታቸው በዘመናቸው ከባዱ ሽንፈት መሆኑን ገለጡ። አሰልጣኙ ከሽንፈቱ በኋላ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፦ ባለፉት 20 ዓመታት የአሰልጣኝነት ዘመናቸው ካዩት «ደካማው ውጤት» መሆኑን መስክረዋል። ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በአንድ ሌሊት መቀረፍ መቻሉ አስቸጋሪ እንደሆነ ሳይሸሽጉ አላለፉም።
ጀርመናዊው አሰልጣኝ አንድ ቡድንን ለከፍተኛ ድል በተደጋጋሚ አብቅተው ቡድኑ ሲሽቆለቆልባቸው ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የ53 ዓመቱ አሰልጣኝ በ2010-11 እና 2011-12 የጨዋታ ዘመን ቦሩስያ ዶርትሙንድን በተደጋጋሚ በቡንደስሊጋው የዋንጫ አሸናፊ እንዲሆን አስችለውታል። በቀጣዩ የጨዋታ ዘመን በ2014-15 ግን ቡድናቸው ውጤቱ አሽቆልቁሎ በቡንደስሊጋው 7ኛ ደረጃ ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። በዚያም እሳቸው ቦሩስያ ዶርትሙንድን ተሰናብተዋል።
ቦሩስያ ዶርትሙንድን ጥለው ከወጡ በኋላም በ2015 የሊቨርፑል አሰልጣኝ ኹነው ተሹመዋል። ሊቨርፑልን በ3 ዓመት ቆይታቸው ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ አብቅተው ለጥቂት ዋንጫ ሳያገኙ ቀርተዋል። በሪያል ማድሪድ በፍጻሜው ያጡትን ዋንጫም በዓመቱ ቶትንሃም ሆትስፐርን ድል በማድረግ መቀዳጀት ችለዋል። በዚያው የ2019-20 ዓመት የውድድር ዘመን ሊቨርፑል ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳም አስችለዋል። ያም ብቻ አይደለም፤ የሊጉ ሰባት ጨዋታዎች እየቀሩት ዋንጫውን መውሰዳቸውን በማረጋገጥም ክብረ ወሰን መስበር ችለው ነበር። ጀመርናዊው አሰልጣኝን ዘንድሮ ግን ምን ነካቸው? በአሁኑ ወቅት ሊቨርፑል በሚገርም ሁኔታ ከ1953-54 የውድድር ዘመን ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለስድስት ተከታታይ ጊዜያት ሽንፈት አስተናግዷል። በደረጃ ሰንጠረዡም 43 ነጥብ ይዞ 8ኛ ላይ ይገኛል። ምናልባትም አስቶን ቪላ ከቀሪ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎቹ አንዱን ካሸነፈ በነጥብ ከሊቨርፑል ጋር ተስተካክሎ በግብ ክፍያ ይበልጠዋል ማለት ነው። ያኔም ሊቨርፑል ከስምንተኛ ወደ ዘጠነኛ ተንሸራቶ በተቀራራቢ የነጥብ ልዩነት ከስሩ አርሰናል ይከተለዋል። 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከሊቨርፑል የሚበለጠው በ5 ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው።
መሪው ማንቸስተር ሲቲ ትናንት በተከታዩ ማንቸስተር ዩናይትድ የ2 ለ0 ሽንፈት ቢገጥመውም በ65 ነጥብ የፕሬሚየር ሊግ ደረጃውን እየመራ ይገኛል። ማንቸስተር ዩናይትድ በ11 ነጥብ ልዩነት በሁለተኛነት ይከተላል። ብራይተንን ቅዳሜ ዕለት 2 ለ1 ድል ያሸነፈው ላይስተር ሲቲ በ53 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታውን ከኤቨርተን ጋር የሚያከናውነው ቸልሲ 47 ሰብስቦ የአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ተጋጣሚው ኤቨርተን በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ደረጃው አምስተኛ ነው። ቶትንሀም እና ዌስት ሐም ሊቨርፑልን ከስራቸው አድርገው በ45 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል።
ዌስት ሐም ምሽቱን ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ትናንት ሊቨርፑልን 1 ለ0 በማሸነፍ ታሪክ ያጻፈበት ፉልሃም በ26 ነጥብ 18ኛ፣ ዌስት ብሮሚች በ18 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገናኛሉ። ሼፊልድ ዩናይትድ 14 ነጥብ ይዞ የደረጃው ግርጌ ላይ ተዘርግቷል። ባለፈው ውድድር ይኸው ቡድን ሊቨርፑልን ማሸነፍ ችሎ ነበር።
ጀርመን ቡንደስሊጋ
ባየር ሙይንሽን ትናንት በቦሩስያ ዶርትሙንድ 2 ለ0 ሲመራ ይቶ 4 ለ2 አሸንፎታል። በደረጃ ሰንጠረዡም በ55 ነጥብ አንደኛ ነው። ተጋጣሚው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ39 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይፕትሲሽ በ53 2ኛ፤ ቮልፍስቡርግ በ45 3ኛ፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ43 አራተኛ፤ ባየር ሌቨርኩሰን ደግሞ በ40 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቀጣይ የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ተወዳዳሪ ለመሆን ቢያንስ አራተኛ ሆኖ መጨረስ ይጠበቅበታል።
የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ፦ የ32 ዓመቱ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ትናንት ዶርትሙንድ ላይ ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል። አንዱን በድንቅ ፍጹም ቅጣት ምት ሌሎቹን በጨዋታ። ሌዎን ጎሬትስካም 88ኛው ደቂቃ ላይ አንድ አስቆጥሯል። ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ 31 ግቦችን በማስቆጠር በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ነው። የጌርድ ሙይለር ክብረ ወሰን ላይ ለመድረስም 9 ግቦች ብቻ ይቀሩታል። ጌርድ ሙይለር በ1971-72 የውድድር ዘመን 40 ግቦችን በማግባት ክብረወሰን ይዟል።
ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ የቀድሞው ቡድኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድን እንዲህ ጉድ ከማድረጉ ቀደም ብሎ ግን ኖርዌያዊው አጥቂ ኧርሊን ኦላንድ ባየር ሙይንሽሽን አስደንግጦ ነበር። ጨዋታው በተጀመረ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ደቂቃዎች ቀዳሚዋን ግብ አስቆጥሮ ሁለተኛዋን ለመድገም ብዙም አልቆየም። በ9ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋን በፈጣን እንቅስቃሴ ከመረብ አሳርፏል። ኧርሊንግ ኦላንድ በተከላካዩ ጄሮም ቦአቴንግ ተረከዙ ላይ በገጠመው ግጭት ከበለዘ በኋላ ለመቀየር ባይገደድ እንደ ሮቤርት ሔትትሪክ ሊሠራ ይችልም ነበር።
ጉዳት ያደረሰበት ተከላካይ ቦአቴንግም በኋላ ላይ ጉዳት ደርሶበት ከሜዳ ወጥቷል። አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚች ግን ኧርሊንግ ኦላንድን የቀየሩት በመጎዳቱ ሳይኾን በርካታ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፉ ለጥንቃቄ ብለው እንደሆነ ከስካይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል። ሌሎች ተጨዋቾችም ዕድል ሊያገኙ ይገባቸዋል ሲሉም ተደምጠዋል።
የኧርሊንግ ኦላንድ በ60ኛው ደቂቃ ላይ መውጣቱ የጨዋታውን ፍጥነት እና ስልት በሚታይ መልኩ ቀይሮታል። ኧርሊንግ ኦላንድ ፈጣን እና የጨዋታ ቦታ መፍጠር የመቻል አቅሙ ከፍ ያለ ነው። እሱ ሲወጣ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ፍጥነቱ እና ንቃቱ ፈዟል።
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ኤዱና ፓርክ ሜዳው ውስጥ ሦስት ዐበይት ችግሮች ውጤቱ እንዲያሽቆለቊል አድርገዋል። 1ኛ፦የአሰልጣኝ ለውጥ ሲደረግ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች አለመቅረባቸው እንደችግር ሊታይ ይችላል። ስዊዘርላንዳዊው አሰልኝ ሉቺያን ፋቭሬ ከተደጋጋሚ ሽንፈት በኋላ በተለይ በሜዳቸው በሽቱትጋርት የ5 ለ1 ብርቱ ቅጣት ከደረሰባቸው በኋላ ነበር የተሰናበቱት። ወዲያው ታዲያ ምርጥ ተጨዋቾች ወደ ቡድኑ ሳይመጡ ኤዲን ቴርዚች በተጠባባቂ አሰልጣንነት መቀጠራቸው ሌላ ችግር ፈጥሯል።
2ኛ፦የቡድኑ ወጥ ያልሆነ አጨዋወትም ለቡድኑ ማሽቆልቆል እንደምክንያትነት ማንሳት ይቻላል። አሸነፈ ሲባል በቀጣይ ጨዋታ ነጥብ እየጣለ እና እየተሸነፈ በጥቅሉ ወጥ የሆነ የአጨዋወት ስልት ዐልታየበትም። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ ወረደ ሲባል እየተነሳ፤ ከፍ አለ ሲባል በመውደቅ ግራ ተጋብቷል።
ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ተደጋጋሚ ሽንፈት በ3ኛነት እንደምክንያትነት ሊነሳ የሚችለው የተጨዋቾች በተለይም የአጥቂው ኧርሊንግ ኦላንድ በተደጋጋሚ መጎዳት ናቸው። የግራ ክንፍ ተከላካይ ማርሴል ሽሜልትሰር በጉልበት ቀዶ ጥገና፤ አማካይ ተከላካይ አክሰል ቪትሰል በቁርጭምጭሚት ጉዳት፣ የግራ ክንፍ ተከላካዩ ራፋኤል ጉዌሬሮ በጡንቻ ችግር፤ እንዲሁም ጄደን ሳንቾ በጡንቻ መሰንጠቅ አይሰለፉም።
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ምናልባት በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫ የማግኘት ተስፋ ግን ሳይኖረው አይቀርም። በግምሽ ፍጻሜው የሚጫወተው ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ቡድኑ ኪዬል ጋር ነው።
ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ነገ ከሴቪያ ጋር ይጋጠማል። በመጀመሪው ግጥሚያ ሴቪያን 3 ለ2 አሸንፎታል። ማክሰኞ ጁቬንቱስ ከፖርቶ ጋር በተመሳሳይ ሰአት የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል። በመጀመሪያው ግጥሚያ ጁቬንቱስ 2 ለ1 ተሸንፏል። ረቡዕ ዕለት በሚኖሩት የመልስ ግጥሚያዎች፦ ሊቨርፑል ከላይፕትሲሽ ጋር የሚያደርጉትም ይጠበቃል። ላይፕትሲሽ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ሊቨርፑልን ከ2 ግብ በላይ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በተመሳሳይ ሰአት ፓሪ ሳንጃርሞ ከባርሴሎና ጋር ይጋጠማሉ። ላይፕትሲሽ የመልሱን ጨዋታ በኮሮና ምክንያት ወደ ቡዳፔስት በማዛወሩ ምክንያት ለሊቨርፑል የ1 ሚሊዮን ዩሮ ካሣ እንደሚከፍል ቢልድ የተሰኘው በጀርመን በተነባቢ ብዛት ከፍተኛ የሆነው ጋዜጣ ዘግቧል።
አትሌቲክስ
የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (Caf) ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የፊታችን ዐርብ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል። ከወዲሁ ግን ባለፈው ዐርብ ሁለት ዕጩዎች ከውድድሩ መውጣታቸውን ዐሳውቀዋል። ተፎካካሪዎቹ የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት አውጉስቲን ሴንጎር እና ዣክ አኖማ የምክትል ፕሬዚደንት ቦታዎችን በመውሰድ ማማከሩ ላይም ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጠዋል። የፊፋ ፕሬዚደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ባሉበት የሞሪታንያ መዲና ኖዋኮት ውስጥ ስምምንት ተፈራርመዋል። ደቡብ አፍሪቃዊው ቢሊዮኔር ፓትሪስ ሞትሴፔ ቀጣዩ የካፍ ፕሬዚደንት ይሆናሉ ተብሏል። በአስተዳደር ችግር ለ5 ዓመታት የታገዱት አህመድ አህመድንም ይተካሉ።
የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8)ን ምክንያት በማድረግ ከ50 ሺህ በላይ ሴቶች ተሳታፊ የሆኑበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ተከናውኗል። በኅብረት እንቅስቃሴው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ሌሎች ሴት የመንግስት አመራር፣ አንጋፋ ሴት አትሌቶች እና አርቲስቶች ተሳታፊ ነበሩ። በኅብረት እንቅስቃሴው ላይ የታደሙ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች እና አዋቂዎች እጅግ ተጠጋግተው ገሚሱ የአፍና የአፍንጫ መከለያ ጭምብል አድርጎ ቀሪው ደግሞ ምንም ሳያደርግ ሲንቀሳቀስ እና ሲዘፍንም ነበር።
ሞ ፋራህ የኦሎምፒክ ወቅትን ጅቡቲ ውስጥ የግማሽ ማራሮን ውድድር ላይ በማሸነፍ ጀምሯል። የአራት ጊዜያት የኦሎምፒክ ባለድሉ ሞ ፋራህ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ ልምምድ እና ውድድሮችን እያከናወነ ነው። በስድስት ወራት ውስጥ የመጀመሪያው ድሉን ባለፈው ዐርብ የጅቡቲ የግማሽ ማራቶን ፉክክር ላይ አስመዝግቧል። ከአሰልጣኙ ባሽር አብዲ በአራት ሰከንዶች ቀድም ብሎ አንድ ሰአት ከ3 ደቂቃ 7 ከ3 ሰከንዶች በመሮጥ አጠናቋል። የ37 ዓመቱ ትውልደ ሶማሊያ ብሪታኒያዊ ሯጭ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላለፉት 9 ዓመታት ይዞ የቆየውን የዐሥር ሺህ ሜትር ሩጫ ክብረ ወሰን ለማስጠበቅ ምኞት እንዳለውም ገልጧል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ