የዩናይትድ ስቴትስና የቻይና መበቃቀል
ሰኞ፣ ሐምሌ 20 2012የካቲት 21፣ 1972 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን ቤዢንግ-ቻይና አዉሮፕላን ማረፊያ ደረሱ።ካዉሮፕላን እንደወረዱ ሊቀበሏቸዉ የሚጠብቋቸዉን ጠቅላይ ሚንስትር ዡ ኢንላይን ተንደርድረዉ ጨበጧቸዉ።«እጆቻችን ሲገናኙ» አሉ ኒክሰን ኋላ በፃፉት ማስታወሻ «አንዱ ዘመን አብቅቶ ሌለኛዉ ተጀመረ።» በርግጥም የኮሚንስት ቻይና እና የኢምፔሪያሊስት ዩናይትድ ስቴትስ የጠብ፣ሽኩቻ፣የእጅ አዙር ጦርነት፣ ቁርቁስ ዘመን አብቅቶ-የዲፕሎማሲ፣ የንግድ ልዉዉጥ፣የድርድር ዉይይት ዘመን በረቀ።ሁለቱ የዓለም ኃያል-ሐብታሞች ዘንድሮ የገጠመት መጎሻሻም ግን ኒክሰን እና ማኦ የጀመሩት ዘመን ፍፃሜ እንዳይሆን ያጠያይቅ ይዟል።ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
በ1990 ዎቹ የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ቻይና ላይ ጠንካራ ምጣኔ ሐብታዊ እርምጃ ለመዉሰድ አንድ ሁለት ማለት ጀምረዉ ነበር።ክሊንተን በዝርዝር ባያሳዉቁም መንግስታቸዉ የንግድ ከፊል ማዕቀብ ለማድረግ ዳርዳር ያሉት ቤጂንግ የአሜሪካዋ የቅርብ ወዳጅ ታይዋንን ትወርራለች በሚል ሥጋት ነበር።
የኤዢያ ጉዳይ አጥኚዉ ኪሾር ማሕቡባኒ እንደሚያስታዉሱት ክሊንተን እርምጃዉን ለመዉሰድ ሲያዉጠነጥኑ «አይሆን፣አቁም፣ አቁም እባክሕ እርምጃዉን እንዳትወስድ---ቻይና ትልቅ ገበያ ናት» እያሉ የተማፀኑት የአሜሪካ ነጋዴዎች ነበሩ።እርምጃዉ ቆመ ወይም በዛቻ ቀረ።
ኒክሰን፣ በ1952 ዩያትድ ስቴትስ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ የፕሬዝደንት ድዌይት ዴቪድ አይዘናወር ምክትል ሆነዉ የተመረጡት ኮሚንስትቶችን አጥብቀዉ የሚጠሉ ፖለቲከኛ በመሆናቸዉ ነበር።በ20ኛዉ ዓመት ነባር አቋማቸዉን አለዝበዉ፣ የቀድሞ መሪዎችን መርሕ ሽረዉ፣ ኢፔሪያሊዝምን «የወረቀት ላይ ነብር» እያሉ ከሚያወግዙ ኮሚንስቶች ጋር ለመነጋገር ቤጂንግ ድረስ የተጓዙት ኮሚንስትን ስለወደዱ አልነበረም።
ፖለቲካዊ ምክንያታቸዉ ብዙ ተንታኞች እንደሚሉት ሶቭየት ሕብረትን ከቻይና ለመነጠል፣ ታይዋን፣ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ የአሜሪካ ወዳጆችን ደሕንነት ለማስከበር ወይም ሌላ ብዙ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል።ሳይጠቀስ የማይታለፈዉ ግን እኒያ የሚጠሏቸዉ ኮሚንስቶች የሚመሩት ታላቅ ሐገርና ሕዝብ ለአሜሪካ የሚሰጠዉን ጥቅም አሻግረዉ በማየታቸዉ ነበር።
«የቻይና ሕዝብ ትልቅ ሕዝብ ነዉ።የአሜሪካ ሕዝብ ትልቅ ሕዝብ ነዉ።ባለፉት ዘመናት ጠላቶች የነበርንባቸዉ ጊዚያት ነበሩ።ዛሬም ትልቅ ልዩነት አለን።እንድንቀራረብ የሚያደርጉን እነዚያ ልዩነቶቻችንን የሚልፉ የጋራ ጥቅሞች አሉን።»
ኒክሰን እና ማኦ ከ48 ዓመታት በፊት የጀመሩት የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት በርግጥ ከመሻኮት፣ መሳለል፣ መወቃቀስ ፀድቶ አያዉቅም።ይሁንና ኒክሰን እንዳሉት የጋራዉ ጥቅም አይሎ የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት በተለይም የንግድ ልዉዉጡን አንቻርሮታል።ኒክሰን ቤጂንግን በጎበኙበት በ1972 የሁለቱ ሐገራት የንግድ ልዉዉጥ 4.7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነበር።
አሁን ዩናይትድ ስቴትስ ቻይና ዉስጥ ከዉበት ሳሎን እስከ ግዙፍ የመኪና ፋብሪካ ወደ 34 ሚሊዮን ኩባንዮች አሏት።ቻይና ባንፃሩ ከ160 በላይ ኩባንዮቿ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ይሰራሉ።
በ2018 በሁለቱ ሐገራት መካከል የተደረገዉ የሸቀጥና የአገልግሎት ንግድ ልዉዉጥ 731.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር።ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ቻይና የላከችዉ ሸቀጥና አገልግሎት 180 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ቻይና ለዩናይትድ ስቴትስ የሸጠችዉ ሸቀጥና አገልግሎት ደግሞ ከ558 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነዉ።ይሕ የንግድ ተባለጥ ከማንም በላይ ኋላ ድንገት ፖለቲከኛ ፕሬዝደንትም ለሆኑት ለነጋዴዉ ዶናልድ ትራምፕ ግልፅ ነበር።«መቀልበስ አለበት።»
ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ እንደዛቱት አሜሪካንን ያከስራል ያሉትን የንግድ ተባለጥ ለማስወገድ የአስተዳደራቸዉ ባለስልጣናት ከቻይና አቻቸዉ ጋር በተከታታይ መደራደር ጀምረዉ፣ የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ተስማምተዉም ነበር።የመጀመሪያዉ ዙር ስምምነት ከተፈረመ ከጥቂት ወራት በኋላ ግን የንግድ ጦርነቱ ተካርሮ ቀጠለ።አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ሐገራት በሚያስገቧቸዉ ሸቀጦች ላይ ቀረጥ በመጨመር ወይም ማዕቀብ በመጣል የተጀመረዉ ጠብ፣ በኮሪያ ልሳነ-ምድር ፍጥጫ፣ በምስራቅ ቻይና ደሴቶች ዉዝግብ፣ በኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት ሰበብ ይንር ያዘ።
«የቻይና ተሕዋሲን በመዋጋቱ ሒደት የታዩ ለዉጦችን እንቃኛለን።አስፈላጊ ከሆነ የመከላከያ ምርት ደንብን ሥራ ላይ ልናዉል እንችላለን።»
የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ለተሕሲዉ ዓለም የተስማበትን መጠሪያ ትተዉ «የቻይና ተሕዋሲ ማለታቸዉ ለብዙዎች ከዘረኝነት የመነጨ ንቀት፣ ላንዳዶች ስድብ ነዉ የሆነዉ።ለቻይኖች ደግሞ አናዳኝ።እንደዘበት የተጀመረዉ ዉዝግብ ሁለቱ ኃያላን ለጋራ ጥቅም ሲሉ ለዓመታት ችላ ያሏቸዉን ልዩነቶች እያጎሉ እንደቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን በጦር ዲፕሎማሲ ጡንቻ ይፈታተሹ ይዘዋል።
ኃምሌ መጀመሪያ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ደቡባዊ ቻይና ባሕር ላይ አምስት ቀን የቆየ የዉጊያ ልምምድ አድርጓል።ቻይና እንደ ግማደ ግዛትዋ ከምትቆጥረዉ አካባቢ የአሜሪካ ጦር የዉጊያ ልምምድ ማድረጉን አጥብቃ አዉግዛዋለች።የዉጊያ ልምምድ-ዉግዘቱ በዉል ተተንትኖ ሳያበቃ ዩናይትድ ስቴትስ ሁዩስተን ቴክሳስ የሚገኘዉ የቻይና ቆስላ በ72 ሰዓትት ዉስጥ እንዲዘጋ ባለፈዉ ሳምንት አዘዘች።ምክንያቱ ቆስላዉ «የስለላና የሌብነት ማዕከል» ሆኗል የሚል ነበር።ቻይናም ላፀፋዉ አልሰነፈችም።አላመነታችምም። ቼንግዱ የሚገኘዉ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲዘጋ ባለፈዉ አርብ አዘዘች።የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን እንዳሉት ቆንስላዉ ዛሬ ተዘጋ።
«ቻይና ባዘዘችዉ መሠረት ቼንግዱ በሚገኘዉ የአሜሪካ ቆስላ ፅሕፈት ቤት ባልደረቦች ዛሬ ጠዋት ሕንፃዉን ለቅቀዉ ሄደዋል።ቆንስላዉም ተዘግቷል።የቻይና ባለስልጣናት በፊለፊቱ በር ገብተዉ ሕንፃዉን ተረክበዋል።»
ፕሬዝደንት ኒክሰን ቻይናን በጎበኙ ማግስት የተጀመረዉ የሁለቱ ሐገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ አንዳቸዉ በሌላቸዉ ሐገር በርካታ ቆስላዎችን ከፍተዋል።ዩናይትድ ስቴትስ ቤጂንግ ዉስጥ ከከፈተችዉ ኤምባሲ በተጨማሪ በስድት የቻይና ክፍለ-ግዛቶች ቆስላ ፅሕፈት ቤቶች ከፍታለች።ቻይና ባንፃሩ ዋሽግተን ከሚገኘዉ ኤምባሲዋ ሌላ በአምስት የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ቆስላ ፅሕፈት ቤቶች ክፍታለች።አሁን ሁለቱም አንዳድ ዘጉ።
የኤዢያ ማሕበረሰብ የተሰኘዉ የዩናይትድ ስቴትስ አጥኚ ተቋም ባልደረባ ኦሪቨል ሺል እንደሚሉት በንግድ፣ በግዛት፣በኮሮና ተሕዋሲ ሰበብ የናረዉ ጠብ፣ ቆንስላ ከማዘጋጋቱ ደረጃ መድረሱ በርግጥ ያሳስባል።የሚያስፈራዉ ግን ተንታኙ እንደሚሉት ጦር እንዳያማዝዝ ነዉ።
«እኔ የምፈራዉ ምናልባት ይበልጥ የሚያወድም ችግር ማለትም በደቡባዉ ቻይና፣ በምስራቃዊ ቻይና ባሕር ምናልባትም በታይዋን ምክንያትና አካባቢ የሆነ ወታደራዊ ግጭት እንዳይቀሰቀስ ነዉ።ይሕ ከሆነ ምናልባት ለብዙ አስርተ-ዓመታት የቆየዉ የዚሕ ዘመኑ ግንኙነት ፍፃሜ ሊሆን ይችላል።ይሕ የሁለቱ ሐገራት ጠላትነት ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን አመልካች ነዉ።»
የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖፕዮ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት አስፈሪዉ እርምጃ የሚቀር አይመስልም።ፖፕዮ የመርሕ በመሰለ ንንግራቸዉ እንዳስታወቁት ፕሬዝደንት ኒክሰን የዛሬ 48 ዓመት ከቻይና ጋር ግንኙነት የመሰረቱት ኒክሰን ራሳቸዉ ያኔ እንዳሉት ሁለቱን ታላላቅ ሐገራት ለጋራ ጥቅም ለማቀራረብ አልነበረም።ይልቅዬ የአሜሪካዉ የወቅቱ ትልቅ ዲፕሎማት እንዳሉት ኒክሰን ከቻይና ጋር ግንኙነት የጀመሩት ኮሚንስታዊን ሥርዓት ከዉስጥ ለመለወጥ ነበር።ይሁንና የኒክሰን መርሕ አልሰራም እንደ ፖምፒዮ።
«ኮሚንስት ቻይናን በትክክል መለወጥ የሚቻለዉ የቻይና መሪዎች በሚሉት ሳይሆን በሚያደርጉት ላይ ተመስርቶ እርምጃ በመዉሰድ ነዉ።የአሜሪካ መርሕ ለዚሕ ማጠቃላያ ምላሽ ሲሰጥ ማየት እንችላለን።ፕሬዝደንት ሬገን ከሶቭየት ሕብረት ጋር የነበራቸዉ ግንኙነት በመተማመን ግን በተረጋገጠ እርምጃ ላይ የተመሰረተ ነዉ ብለዉ ነበር።ከቻይና ከሚኒስት ፓርቲ ጋር ሲሆን ግን በመጠራጠር ግን በተረጋገጠ እርምጃ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት እላለሁ።»
ፖፒዮ እንንደሚሉት መንግስታቸዉ የቻይና ኮሚንስታዊ ስርዓትን ለመለወጥ ወይም ለማፍረስ ለሚወስደዉ እርምጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን የቡድን 7 እና የቡድን 20 ስብስብን ከጎኑ ያሰልፋል።ቻይና ለአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዛቻ አፀፋ፣ ቃል አቀባይ እንጂ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯን አላሰለፈችም።ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ግን የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርን ዛቻ «የቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን ቀረርቶ» ብሎዉታል።ያዉም የተሳሳተ።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ