የደቡብ ፖሊስ አግር ኳስ ቡድንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውዝግብ
ሐሙስ፣ መስከረም 22 2012የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2012 ዓም የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ዙሪያ ያሳለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበለው የደቡብ ፖሊስ አግር ኳስ ክለብ አስታወቀ። ክለቡ ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው ቅሬታ ምላሽ ካላገኘም ጉዳዩን ወደ አፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) በመውሰድ አቤቱታውን ለማሰማት መዘጋጀቱን የክለቡ አመራሮች ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ በነገው እለት በጉዳዩ ላይ ለምመከር ክለቦችን ስብሰባ መጥራቱን አስታውቋል።
የደቡብ ፖሊስ አግር ኳስ ክለብ አመራሮች ዛሬ በሀዋሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጲያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2012 ዓም የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ ክለባቸው እንደማይቀበለው አስታውቀዋል። የክለብ ጸሐፊ ኢንስፔክተር እታገኘው ዜና እንዳሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2012 ዓም የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ወደ ሃያ አራት ከፍ በመደረጉ ምክንያት ክለባቸው በዓመታዊው የሊጉ ውድድር ተሳታፊ መሆኑን ከወራት በፊት ለክለቡ በላከው ድብዳቤ አንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ክለቡ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅቱን እንዲያደርግ በሚል ከፌዴሬሽኑ በደረሰው ማሳሰቢያ መሰረት የፕሪሚየር ሊግ ውድድሩን በሚመጥን ደረጃ የአሰልጣኞች ቅጥርና የተጫዋቾች ግዢን ጨምሮ ለውድድሩ የሚያስፈልገውን መሰናዶ ማጠናቀቃቸውን ኢንስፔክተር እታገኘው አብራርተዋል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የ2012 ዓም የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ሃያ አራት መሆናቸው ሲገልፅ የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን «ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር አስራ ስድስት ብቻ መሆኑን በማስታወቅ ከሊጉ ውድድር ውጪ ያደርገን በመሆኑ ውሳኔውን እንቃወማለን» ብለዋል። የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በተከተለው አካሄድ ክለባችንን ለገንዘብ ኪሳራ ፣ ተጫዋቾቻችንንና ደጋፊዎቻችንን ደግሞ ለስነ ልቦናዊ ጉዳት ዳርጎብናል ያሉት የክለቡ አመራሮች ውሳኔን ዳግም እንዲመረምር በድብዳቤ መጠየቃቸውንም ገልጸዋል። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር ግርማ ዳባ በበኩላቸው «ፌዴሬሽኑ አስቀድሞ እራሱ የተስማማበትን ውሳኔ መልሶ አራሱ መጣሱን በመጠቆም በሕግ አግባብ ላቀረበነው ቅሬታ በጎ ምላሽ እናገኛለን የሚል አምነት አለን።» ብለዋል። ክለቡ ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው ቅሬታ ምላሽ ካላገኘም ጉዳዩን ወደ አፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ( ካፍ ) በመውሰድ አቤቱታውን ለማሰማት መዘጋጀቱን የክለቡ አመራሮች ገልጸዋል።
ዶቼ ቨለ (DW) ያነጋገራቸው የኢትዮጲያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሚኒኬሽን ዳይሬከተር አቶ ባሕሩ ጥላሁን የደቡብ ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች ክለቦችም ጨምሮ ባቀረበው ቅሬታ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በፌዴሬሽኑ ሥራአስፈፃሚ እንደገና እንዲታይ መጠየቃቸውን ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ በነገው እለት በጉዳዩ ላይ ለምመከር ከለቦችን ስብሰባ መጥራቱን የጠቆሙት የኮሚኒኬሽን ዳይሬከተሩ በ2012 የ2012 ዓም የፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦችን ቁጥርም ከክለቦቹ ጋር በመወያየት የጋር ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናገረዋል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ