1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ም/ቤት የኢትዮጵያና የኤርትራን ሰላም ደገፈ

ሰኞ፣ ጥር 13 2011

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ግንኙነቱ መሻሻል የጀመረው ከስድስት ወር በፊት ነበር። የጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ ቡንድስታግ ይህንኑ ግንኙነታቸውን ለብዙ ዓመታት አቋርጠው የነበሩትን  የሁለቱን ምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት መቀራረብ  አሞግሷል።

https://p.dw.com/p/3Bu09
Deutschland Bundestag in Berlin | Olaf Scholz (SPD), Bundesfinanzminister
ምስል picture-alliance/dpa/B.v. Jutrczenka

የጀርመን ፌዴራዊ ም/ቤት የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ሰላም መደገፉ

የጀርመን የሕዝብ እንደራሴ ምክርቤት «ቡንደስታግ» ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ አቀረበ :: ምክር ቤቱ ባለፈው ሃሙስ አመሻሽ ላይ ባካሄደው ውይይት ሁለቱ አገራት ዳግም የተሟላ ግንኙነትን በመመሥረት ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ አለመግባባት በመቋጨት አዲስ የሰላም ምዕራፍ መጀመራቸውን ከመንፈቅ በኋላ አወድሶታል:: በኢትዮጵያ ለሚካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ አድናቆታቸውን የቸሩት የጀርመን ፓርላማ እንደራሴዎች አሁን በአገራቱ መካከል የተጀመረውን የሰላም ጥረት ከማገዙ ጎን ለጎን በአፍሪቃ ግንባር ቀደም አምባገነን እና ጨቋን ነው ያሉትን የኤርትራ መንግስት በአገር ውስጥ ስር ነቀል የዲሞክራሲያዊ እና የተሃድሶ ለውጥ እንዲያመጣም ጠይቀዋል:: የስብሰባውን ሂደት የ DW የአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ፕሮግራም ክፍል አስተባባሪ ኤዲተር /አርታዒ/ ዳንኤል ፔልዝ ተከታትሎታል እንዳልካቸው ፈቃደ እንደሚከተለው ተርጉሞታል።
የጀርመን የሕዝብ እንደራሴ ምክርቤት ቡንደስታግ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ጥረት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ባለፈው ሳምንት ሃሙስ አመሻሽ ጥልቅ ውይይት እና ክርክር አካሂዷል:: ውይይቱ የጀርመኑ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ከአንድ ሳምንት በኋላ ለአራት ቀናት በኢትዮጵያ ኦፊሴልያዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ከተገለጸ በኋላ መሆኑ ጀርመን በአጠቃላይ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና ብልጽግና ለማስፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ያላትን ቁርጠኝነት አመላካች ነው የሚል ዕምነት አሳድሯል :: የ DW ጋዜጠኛ ዳንኤል ፔልዝ የውይይቱን ሂደት ተከታትሎ እንደዘገበው ክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በምህጻሩ ሲ ኤስ ዩ እና እህት ፓርቲው ክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ ሲ ዲ ዩ  እንዲሁም የጥምሩ መንግሥት አካል የሆነው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ኤስ ፒ ዲ ለውይይት በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ከተካሄደ በኋላ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰው ታሪካዊ የሰላም ስምምነት አበረታች እና የሚደነቅ ነው ሲሉ ከመንፈቅ በኋላ ዳግም አወድሰውታል ::
የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP የልማት ጉዳዮች እንደራሴ ኦላፍ ቤክ በበኩላቸው የኢትዮ-ኤርትራን የሰላም ስምምነት እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር በ 1963 ዓ.ም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን እና ፈረንሳይ አገራት መካከል የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ግጭት ለማብቃት በአገራቱ መካከል ከተደረገው የፓሪሱ የሁለትዮሽ የእርቅ  የፖለቲካ የምጣኔ ሃብት እና የባህል ትብብር ማለትም " የኤሊዜ ትሪቲ " ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይገባዋል ሲሉ መክረዋል::
"ቀድሞ በጠላትነት ይተያዩ የነበሩት ጀርመን እና ፈረንሳይ ዛሬ በመላው አውሮጳም ይሁን በአውሮጳ ሕብረት ድርጅቱ ውስጥ ትልቅ የጋራ አመራር ሚና ሊኖራቸው የቻለው በኤሊዜው ስምምነት መሰረት አስተማማኝ የጠበቀ እና በዕምነት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ወዳጅነትን በመሃላቸው በመመስረታቸው ነው ።
ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ አወዛጋቢ ሆኖ በሰላም የተቋጨውን የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነትም ዘላቂነት እንዲኖረው በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ "የአፍሪቃ የኤሊዜ ትሪቲ" እንዲሆን የጋራ ራዕያችን እና ግባችን ሊሆን ይገባል። “
የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረዉን የለዉጥ ተሃድሶ ጅማሮ በማመስገን አሁን የሚካሄደውን የሰላም እና የዲሞክራሲ ጉዞ እንዲቀጥልበት ያበረታታው የጀርመን ምክርቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአገሪቱ የአንድ ፓርቲ አምባገነን ሥርዓት እንዲያበቃ የተቃውሞ የፖለቲካ አራማጅ የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱ በአገሪቱ ብሔራዊ የምርቻ ቦርድ ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲ አባል የነበሩ በአመራርነት እንዲሾሙ ማድረጋቸው እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ 2020 ዓ.ም ነጻ አገራቀፍ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲካሄድ መወሰናቸው በአገሪቱ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያላቸውን ቁርጠኝ ነት አመላካች መሆኑን ነው የገለጸው:: የጀርመኑ ክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት ፓርቲ CDU ምክትል ሊቀመንበር ጊሴላ ማንዴርላ እንደሚሉት ኢትዮጵያ አሁን ወደተሻለ የዲሞክራሲ ጎዳና እያቀናች ነው ::
"በኢትዮጵያ የታየው ፖለቲካዊ ለውጥ ከአመታት በፊት ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችል ነበር:: እናም በጥቂት ወራት ውስጥ የተገኘው ፖለቲካዊ ስኬት በግልጽ ዕውቅና ሊቸረው ይገባል:: የተሃድሶ ለውጡን ለማስቀጠል
እና በቀጣናው የተሻለ ሰላምን ለማስፈን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ መንግሥት በኩል እየተደረገ ያለውም ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ሊመሰገን የሚገባው ነው:: " የጀርመን የሕዝብ እንደራሴ ምክርቤት ቡንደስታግ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ ባቀረበበት ውይይት በአፍሪቃ ግንባር ቀደም አምባገነን እና ጨቋን ነው ያሉትን የኤርትራ መንግስት በአገር ውስጥ ስር ነቀል የዲሞክራሲያዊ እና የተሃድሶ ለውጥ እንዲያመጣም ጠይቀዋል :: በአገሪቱ ሁሉም ዜጎች ላይ ግዳጅ ተጥሎ የነበረው የብሄራዊ ውትድርና እና በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያለክፍያ ለዓመታት ነጻ አገልግሎት ማበርከት የጊዜ ገደብ እንዲኖረው እና የአገልግሎት ግዳጃቸውን ለሚፈጽሙ ምልምሎችም አዲስ የማበረታቻ የክፍያ አሰራር እንዲዘረጋ ሃሳብ ቀርቧል:: ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ነጻ የሚድያ ተቋማትም የሃሳብ ነጻነት መብታቸው እንዲጠበቅ ግፊት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም አጽንዖት ተሰቶበታል።
ኤርትራ ነጻነቷን ካገኘችበት እንደ ጎርጎራውያኑ 1993 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቱ ነጻ ምርጫ አለመካሄዱም ተወስቷል:: የተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች መርጃ ድርጅትን ዋቢ ያደረጉት የጀርመን የሕዝብ እንደራሴ አባላት በድህነት ተስፋ በማጣት እና ቀደም ሲል በዜጎች ላይ ተጥሎ የቆየውን የብሄራዊ አገልግሎት ምክንያት አድርገው እስከ ቀርብ ዓመታት ድረስ በየወሩ ከ 4-5 ሺህ የሚገመቱ ኤርትራውያን አገሪቱን ጥለው እንደተሰደዱ በመግለጽም የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት ዘርዝረዋል:: የኢትዮ-ኤርትራን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኤርትራ ጥቂት ለውጦች እየታዩ ነው ያሉት የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሃላፊ ክሪስቶፍ ማትቺ በበኩላቸው በአገሪቱ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በግልጽ ሊነገራቸው ይገባል ነው ያሉት::
" በኤርትራ የፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች እየተከበሩ አይደሉም:: በአገሪቱ እስከዛሬ ነጻ የፓርላማ ሥርዓት እና ምርጫ የሚባል ነገር የለም:: ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እና የግል ፕሬስም እንዲሁ :: ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴም የታገደ ነው:: ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በግልጽ ሊነገራቸው ይገባል:: በኤርትራ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የተሃድሶ ለውጥ እንዲካሄድ እና ነጻነት እንዲያብብ እንጠብቃለን:: "
የኤርትራ መንግሥት ለለውጥ ዝግጁ ከሆነ ተቋርጦ የቆየው የልማት ተራድዖ ትብብር ስምምነቱ እንደሚቀጥልም ነው በምክርቤቱ የተገለጸው:: ጀርመን እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ አምባገነን ነው ካለችው የኤርትራ መንግስት ጋር የነበራትን የልማት ትብብር አቋርታ ቆይታለች:: በቅርቡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከጀርመኑ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ጌርድ ሙለር ጋር በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነትና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮች ዙሪያ አስመራ ውስጥ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ኤርትራ ከጀርመን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት መንግሥት አገራዊ የተሃድሶ ለውጥ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት ሲሉ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው ይታወሳል::ምንም እንኳን ጀርመን ጨቋኝ ሥርዓት ከምትለው የኤርትራ መንግሥት ጋር የልማት ተራድዖ ትብብሯን ለረጅም ጊዜያት አቋርጣ ብትቆይም አሁንም ከአውሮፓ ሕብረት በሚሰጥ የገንዘብ ድጎማ በስደተኞች ዙሪያ በተዘዋዋሪ መንገድ ከአገሪቱ ጋር እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች በምክርቤቱ አባላት ዘንድ ሌላው ከፍተኛ ክርክርን የፈጠረ አጀንዳ ነበር :: ለአብነትም የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ለሰዎች ፍልሰት መንስኤ ናቸው ካላቸው የአፍሪቃ አምባገነን መሪዎች ጋር የሚደረግን ስምምነት አጥብቆ ኮንኗል::የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ህብረት ምክትል ሃላፊ አግነይሽካ ብሩገርም ይህን ጉዳይ አጽንዖት ሰተውበታል::
"  እንደ ኤርትራ ካሉ አምባገነን የአፍሪቃ መንግሥታት ጋር ዓለማቀፉ የጀርመን የልማት ተራድዖ ድርጅትን የመሳሰሉ ግብረሰናይ ተቋማት ከአውሮፓ ሕብረት በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ ስደተኞችን በመርዳት እና መልሶ በማቋቋም እንዲሁም በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ላይ የሚያከናውኑት እንቅስቃሴ በውል ሊጤን ይገባል:: ከጨቋኝ መንግስታቱ ጋር በትብብር ሲሰሩ ገንዘቡ ለተፈለገው ዓላማ ሰላምን እና የወደፊት ብሩህ ተስፋን ሊያመጡ በሚችሉ ራዕዮች እና ዕቅዶች ላይ መዋሉን መቆጣጠር አለባቸው እንጂ የደህንነት ስጋትን እና አደጋን ሊደቅኑ አይገባም::“
ያም ቢሆን የጀርመን ምክር ቤት የኢትዮ-ኤርትራ ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ይበልጥ እንዲጠናከር ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡ አገራቱ በቀጣናው ለጀመሩት የለውጥ ምዕራፍ አጋዥ እንደሚሆን ታምኖበታል:: በቅርቡም በትጥቅ ትግል ላይ ቆይተው በመንግስት ጥሪ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስነው ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ ታጣቂዎችን ለማቋቋም የጀርመን መንግስት የልማትና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱ ይታወሳል:: የጀርመኑ ርዕሰ ብሔር ዶክተር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ከአንድ ሳምንት በኋላ ከጃንዋሪ 27 እስከ 30,2019 ዓ.ም ለአራት ቀናት በኢትዮጵያ ኦፊሴልያዊ የሥራ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን በዓለማቀፉ የጀርመን የልማት ተራድዖ ድርጅት አማካኝነት ብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዳንየል ፔልስ/እንዳልካቸው ፈቃደ

እሸቴ በቀለ