1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ካቢኔ አዲስ የስደት ህግ አፀደቀ

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2015

የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት የገጠማት ጀርመን ችግሩን ለመፍታት ከውጭ ሀገራት ሰራተኞችን ለማመጣት በዚህ ሳምንት ረቡዕ አዲስ የስደት ረቂቅ ህግ አጽድቃለች።መመዘኛዎቹ የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታዎች፣የሥራ ልምድ፣ የዩንቨርሲቲ ዲግሪ ወይም ሙያ ብቃት ፣ከጀርመን ጋር ከዚህ ቀደም የነበሩ ትስስሮች ወይም ጀርመን የኖረ እና ከ35 ዕድሜ በታች ናቸው።

https://p.dw.com/p/4PYHf
Reisepass Symbolbild
ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

አዲሱ የጀርመን የስደት ህግ


ጀርመን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ችግርን ለመፍታት የስደት  ፖሊሲዎቿን በትኩረት እንድትመለከት አስገድዶታል። የጀርመን የሀገር ውስጥ እና የሰራተኛ ሚኒስቴሮች  በጋራ ያቀረቡት አዲስ የስደት  ረቂቅ ህግ ሰሞኑን በሀገሪቱ ካቢኔ ፀድቋል ።
በሀገሪቱ ምክር ቤቶች በኩል ማለፍ የሚጠበቅበት ይህ  ረቂቅ ህግ የሀገሪቱን የስደት ፣የነዋሪነት እና የዜግነት ህጎችን ያሻሽል ተብሏል።
 የሰሰለጠነ የሰው ሀይል ወደ ሀገሪቱ የማምጣት ሀሳብ መሰረቱ የተጣለው ቀደም ሲል በጎርጎሪያኑ መጋቢት 2020 ዓ/ም በቀድሞዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርከል በሚመራው የጥምር መንግስት ሲሆን፤ረቂቅ ህጉ የአውሮፓ ህብረት ካልሆኑ ሀገራት የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍልሰትን በዓመት ወደ 60,000 ሊጨምር እንደሚችል ይገምታል። ይህም በ2019 ከኮቪድ በፊት ከነበረው ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል።በጀርመን የኑረንበርግ የሰራተኛ ቅጥር ጥናት ተቋም ባልደረባ  የሆኑት ኢህሳን ቪልዜዴህ በርካታ የሰራተኛ ገበያ መኖሩን ያስረዳሉ። 
«ወጣቱ ትውልድ ጡረታ ሲወጣ የእኛ የስራ ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ጀርመን በዓመት 40,000 ያህል ስደተኞች ትፈልጋለች። እና ጀርመንን ይበልጥ ማራኪ ማድረግ አለብን። በተለይም ከፍተኛ ብቃት እና ችሎታ ላላቸው ሰራተኞች።»
ፖሊሲው በአምስት መመዘኛዎች ላይ  የተመሰረተ ሲሆን፤ እነዚህም የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታዎች፣ የሥራ ልምድ፣ የዩንቨርሲቲ ዲግሪ ወይም ሙያ ብቃት ፣ከጀርመን ጋር ከዚህ ቀደም የነበሩ ትስስሮች  ወይም ጀርመን የኖረ እና ከ35 ዕድሜ በታች ናቸው።
የሰራተኛ ሚኒስትር ሁበርተስ ሄይል በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ እንዳደረጉት ሰዎች ከእነዚህ መስፈርቶች ውስጥ ሶስት እና ከዚያ በላይ ያሟሉ  ብቁ ይሆናሉ ብለዋል ።
ይህም  በሀገሪቱ ያለውን ከፍተኛ  የሥራ ገበያ በስራተኛ ለመሙላት ይጠቅማል። በርሊን በ 2022 አራተኛው ሩብ ዓመት የነበራት  ክፍት የስራ ቦታዎች ቁጥር 1.98 ሚሊዮን ደርሷል ፣ ይህም እስካሁን ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው ተብሏል ።
በጀርመን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፣ በቅርብ በተደረገ ጥናት ከተሳተፉት ኩባንያዎች ውስጥ 90 በመቶ የሚጠጉ ኩባንያዎች የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት አለባቸው።በመሆኑም የተካኑ የውጭ ሀገር ሰራተኞችን  መምጣት ቀላል እንዲሆንላቸው ይሻሉ።
የጀርመን መንግሥት ይንንን የሚያቀል አዲስ የዕድል ካርድ /ሹዋንሰን ካርተ/ ማዘጋጄቱን ገልጿል። በርሊን የሚኖሩት ህንዳዊ የሶፍትዌር መሀንዲስ ማንጋት አይ ሙዲ ግን መመዘኛው ቀላል አይደለም ይላሉ። 
«ወደ ጀርመን መምጣት የሚፈልጉ ጓደኞች አሉኝ ።በእነዚህ መስፈርቶች ምክንያት ግን ሁሉም ወደ ዩስ አሜሪካ  ወይም ወደ ብሪታንያ ለመሄድ ወሰኑ።ምክንያቱም እነሱ ትግሉን  አይችሉትም ። ለምንስ መታገል ይፈልጋሉ? በሌሎች ሀገሮች ተጨማሪ ደሞዝ በተመሳሳይ መንገድ ካገኙ።ለዚያውም የቋንቋ እንቅፋት ሳይኖር።»
በመሆኑም  ሀገሪቱ የውጭ ሰራተኞችን ለመሳብ አስቸጋሪ  ያደረጉትን የተለያዩ የቢሮክራሲ መሰናክሎች መቀነስ እንዳለባት ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው።
ጀርመን ቢሮክራሲ የሚበዛባት ሀገር ከመሆኗ ባሻገር በቅርብ ጊዜ በወጣ መረጃ መሰረት  ቋንቋ ከመማር ፣የዲጂታል አገልግሎቶችን ከማግኘት እና ጓደኛ እና ወዳጅነትን ከመመስረት አንፃር  ለውጭ ሀገር ሰራተኞች ከማይመቹ ሀገራት አንዷ ነች ።በመሆኑም  መንግስት   የውጭ ሀገር ሰራተኞችን ለመሳብ እና  ለማቆየት እንደ የስራ ለውጥ ወይም ቤተሰብን ማምጣት ያሉ ጉዳዮች ላይ  ከባድ ቢሮክራሲዎች መስተካከል ይኖርበታል። ይላሉ የሰራተኞች ጥናት ባለሙያው ቪልዜዴህ።  
«እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተቻለ መጠን ለመቀነስ ማየት ይኖርብናል ።  ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎችንም ሆነ ለቪዛ ቀጠሮ ለመያዝ መሞከርን ወይም የትምህርት ደረጃን ዕውቅና ማግኘትን። ምክንያቱም ሰዎች ጀርመንን ከሌሎች መሰናክል ከሌላቸው ሀገሮች ጋር ያወዳድራሉ።»

Griechenland/Deutschland Proteste von Flüchtlingen vor dem deutschen Konsulat in Thessaloniki
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance
Deutschland | Bundespressekonferenz zum Regierungsentwurf für das neue Fachkräfteeinwanderungsgesetz
ምስል Jens Krick/Flashpic/picture alliance


ፀሀይ ጫኔ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር