1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 17 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 17 2012

ባየር ሙይንሽን ቦሩስያ ዶርትሙንድን አስከትሎ በመሪነቱ እንደቀጠለ ነው፤ ኹለቱ ነገ ማታ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ በተደረገ ምርመራ በኮሮና ተሐዋሲ የተጠቁ ተጨዋቾች ተገኝተዋል፤ ቀደም ሲል በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ የታደሙ 41 እግር ኳስ አፍቃሪያንም በኮሮና ታመው መሞታቸው ተዘግቧል።  

https://p.dw.com/p/3ck9c
Bundesliga - Hertha BSC v 1. FC Union Berlin
ምስል Getty Images/AFP/S. Franklin

የግንቦት 17 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ፍራንክፉርትን ባደባየበት ግጥሚያ በግብ የተንበሸበሸው ባየር ሙይንሽን መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። በአራት ነጥብ ከሚከተለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ነገ ማታ የሚያደርጉት ግጥሚያ በዓለም ዙሪያ በስፋት ይጠበቃል። ከኹለቱ ጨዋታ በኋላ በተመሳሳይ ሰአት የሚከናወኑት ሦስት የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎችም ወሳኝ ናቸው። የዶርትሙንድ የመሀል ተከላካይ ማትስ ሁመልስ ጨዋታዎን እንደሚያሸንፉ «99 በመቶ» እርግጠኛ መኾኑን ገልጧል። ከኹለት ወራት በፊት እንግሊዝ ውስጥ በተከናወነው የሊቨርፑል እና የአትሌቲኮ ማድሪድ ግጥሚያ ታዳሚ ከነበሩ የስፖርት አፍቃሪያን መካከል 41ዱ በኮሮና ተሐዋሲ ምክንያት መሞታቸውን አንድ ጥናት አመላከተ። የባየር ሌቨርኩሰኑ አማካይ ካይ ሐቬርትስን ጨምሮ አንዳንድ የቡንደስሊጋ ተጨዋቾች ወደ ሌሎች የአውሮጳ ቡድኖች ሊዛወሩ እንደኾነ እየተነገረ ነው።  

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ጨዋታዎች መሪው ባየር ሙይንሽን እና አር ቤ ላይፕትሲሽ በግብ ተንበሽብሸዋል። ከኹለቱም በድምሩ ዐሥር ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል። በተለይ የላይፕሲሹ አጥቂ ቲሞ ቬርነር ሔትሪክ በመሥራት በቡንደስሊጋው በርካታ ግብ በማስቆጠር አንደኛ ወደ ኾነው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ተጠግቷል። ቲሞ ቬርነር 24 ግቦች አሉት። በባየር ሙይንሽኑ አጥቂ የሚበለጠው በሦስት ግቦች ብቻ ነው።

Vorschau Borussia Dortmund-FC Bayern Muenchen am 26.05.2020.
ምስል picture- alliance/E. Kremser Hoermann

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከተከሰቱ ዐበይት የቡንደስሊጋ ክንውኖች መካከል፦ ከተቀያሪ ወንበር ያልተነሳው ማሪዮ ጎይትስ  ዕጣ ፈንታ የብዙዎች መነጋገሪያ ኾኗል።  የሻልከ ተደጋጋሚ ሽንፈት አሰልጣኝ ዴቪድ ቫግነር ላይ ጫናው እንዲበረታ አድርጓል። የጄደን ሳንቾ ተቀይሮ እንደገባ ግብ ማመቻቸቱ፤ እንዲሁም የኮሎኝ ቡድን ፎርቱና ዱይስልዶርፍን ባለቀ ሰአት ነጥብ የተጋራባት ብርቱ ፍልሚያ በቡንደስሊጋው ጎልተው የወጡ እና የሚጠቀሱ ናቸው። 

ከኮሮና ወረርሺኝ በኋላ ዳግም በተካሄደው ኹለተኛ ሳምንት የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ ለኮሮና ወረርሽኝ ጥንቃቄ በማድረጉ ረገድ እመርታ መመዝገቡ ተገልጧል። የጀርመን እግር ኳስ ሊግ (DFL) ኃላፊ ክሪስቲያን ዛይፈርት እና የሊጉ የእግር ኳስ ጉዳዮች እና የደጋፊዎች ዳይሬክተር አንስጋር ሽቬንከን ለተመዘገበው እመርታ ኹሉንም ተጨዋቾች በደብዳቤ አወድሰዋል። ተጨዋቾች በሊጉ የታሰበውን ጥንቃቄ በመፈጸማቸውም «እጅግ አድናቆት እና ከልብ የኾነ ምስጋና» እንዲደርሳቸው አድርገዋል። በእርግጥም ተጨዋቾች በተለይ ግብ ሲያስቆጥሩ በመጀመሪያው ሳምንት ደስታቸውን የገለጡበት መንገድ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተሻሽሏል። ቀደም ሲል ተጨዋቾች ክልከላ ቢኖርም ግብ ካስቆጠሩ በኋላ መተቃቀፋቸው እና መጨባበጣቸው አነጋጋሪ ኾኖ ነበር።

ቅዳሜ ዕለት ከተደረጉ አምስት ጨዋታዎች መካከል ከባየር ሙይንሽን እና ፍራንክፉርት ግጥሚያ በተቀር ሌሎቹ በተመሳሳይ ሰአት መከናወናቸው የእግር ኳስ አፍቃሪያንን ለምርጫ እንዲቸገሩ አድርጓል። ወደ ሽቫርትስቫልድ ስታዲየም ያቀናው ብሬመን ፍራይቡርግን በሜዳው 1 ለ0፤  ሲያሸንፍ፤ ፓዴርቦርን  በሜዳው ቤንቴለር አሬና ስታዲየም ሆፈንሃይምን ገጥሞ አንድ እኩል ተለያይቷል። ባየር ሌቨርኩሰን ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅን በሜዳው ቦሩስያ ፓርክ 3 ለ1 አሸንፏል።

ራፋኤል ጉዌሬሮ በ32ኛው ደቂቃ ላይ፤ አሽራፍ ሐኪሚ 78ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሩት ኹለት ግቦች ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቅዳሜ ዕለት ቮልፍስቡርግን በሜዳው ፎልክስቫገን አሬና ስታዲየም አሸንፏል። 

Bundesliga VfL Wolfsburg - Borussia Dortmund Dortmunds Trainer Lucien Favre
ምስል picture-alliance/dpa/M. Sohn

አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬ ባለፈው ደርቢ ሻልከን 4 ለ0 ሲያሸንፉ የነበሩትን ተጨዋቾች በአጠቃላይ አሰልፈው ነው ወደ ሜዳ የገቡት። በጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኹለቱም ቡድኖች በጣም ጥንቃቄ አድርገው በመከላከል ስልት ነበር የተጫወቱት።  

የዶርትሙንዱ የመኻል ተከላካይ  ማትስ ሁመልስ 46ኛው ደቂቃ ላይ በኤምሬ ቻን  ተቀይሯል። ከግራ ማኑዌል አካንጂ፤ ከቀኝ ደግሞ ሉቃስ ፒስቼክ የተከላካይ ክፍሉን በደንብ አጠናክረው ቆይተዋል። 

የ19 ዓመቱ ኖርዌጂያዊ አጥቂን  ከፊት ያሰለፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ኹለቱን ግቦች ያስቆጠረው በአማካዮች ነበር። አማካዮች በአሰላለፍ ከግራ ወደቀኝ ራፋኤል ጉዌሬሮ፤ ቶማስ ዴላኒ፤ ማህሙድ ዳውድ፤ አሽራፍ ሐኪሚ ነበሩ።  ዩሊያን ብራንድት በስተግራ ተመላላሽ አማካይ፤ ቶርጋን ሃዛርድ  በስተቀኝ ተመላላሽ አማካይ ተሰልፈው በተገቢ ኹኔታ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል። 

32ኛው ደቂቃ ላይ ኧርሊንግ ሃላንድ የሳተውን ጉዌሬሮ ከመረብ አሳርፏል። ሃላንድ እየተጋጨ ጥፋት ሲሠራ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ሃላንድ እምብዛም ነበር ማለት ይቻላል። ግጥሚያው ሲከናወን አየሩ ቀዝቃዛና ነፋሻማ  ብሎም ካፊያማ ነበር።  ማርኮ ሮይስ፦ በደረሰበት ጉዳት ምናልባትም እስከመጨረሻው የጨዋታ ዘመን ላይሰለፍ ይችላል እየተባለ ነው። ማትስ ሁመል ከመጀመሪያው አጋማሽ በኋላ ትንሽ ጉዳት ስለደረሰበት በኤምሬ ቻን ተቀይሯል፤ ጉዳቱ ግን የከፋ አይደለም። 

62ኛው ደቂቃ ላይ ሮናቶ ሽቴፋን አየር ላይ እንዳለች አጥብቆ ወደ ግብ የመታት እና ሮማን ቡርኪ የመለሳት ኳስ ግብ ጠባቂው ብቃቱን ያሳየበት፤ ለቮልፍስቡርግ ደግሞ የግብ እድል ልትኾን ትችል የነበረች አጋጣሚ ናት። 65ኛው ደቂቃ ላይ  ጄደን ሳንቾ በዩሊያን ብራንድት ተቀይሮ ገባ። ሳንቾ እንደገባ ጆን አንቶኒ ብሩክስ ጉዳት ስላደረሰበት ቢጫ አይቷል። 

Fußball Bundesliga Borussia Dortmund Michael Zorc und Mario Götze
ምስል Imago Images/Team 2

ዶርትሙንድ በኹለተኛው አጋማሽ ወደ መከላከሉ አዘንብሏል። 70ኛው ደቂቃ ላይ ግን በመልሶ ማጥቃት የግብ ሙከራ አድርገው የማዕዘን ምት አግኝተዋል። የጄደን ሳንቾ መግባት ጨዋታውን ቀይሮት፤ 72ኛው ደቂቃ ላይም ዶርትሙንድ የማዕዘን ምት አግኝቷል። 74ኛው ደቂቃ ላይ ቶርጋን ሐዛርድ ቢጫ ዐየ፤ ባቡን ከማሳለፍ ግን ጠልፎ ማጨናገፉ ይሻለዋል። 78ኛው ደቂቃ ላይ በድንቅ የመልሶ ማጥቃት ሐኪሚ በቀኝ በኩል ምርጥ ግብ አስቆጥሯል። ጄደን ሳንቾ ፍጥነት እና ቅልጥፍና በተሞላበት ኹኔታ ወደፊት በመግፋት ኳሷን ለሐኪሚ አመቻችቶ አቅርቧል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ፌሊክስ ክላውስ ማኑዌል አካንጂን ባቱ ላይ ኾን ብሎ ስለረገጠው በቀይ ተሰናብቷል። የመጨረሻውን 10 ደቂቃም ቮልፍስቡርግ በ10 ተጨዋቾች ብቻ ተወስኗል። 

በእለቱ ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ በሜዳው ቦሩስያ ፓርክ ስታዲየም  በባየር ሌቨርኩሰን 3 ለ1 መሸነፉ ለላይፕሲሽ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ እንዲል አስችሎታል። ላባየር ሌቨርኩሰን በ7ኛው እና 58ኛው ደቂቃ ላይ ኹለት ግቦችን ያስቆጠረው አማካዩ ካይ ሐቬርትስ ነው። የማሳረጊያዋን ግብ ተከላካዩ ስቬን ቤንደር በ81ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፏል።  ካይ ሐቬርትስ በ100 ሚሊዮን ዩሮ ሊዘዋወር መኾኑ እየተነገረ ነው። ማድሪድ፣ ባርሴሎና፣ ሊቨርፑል፤ ጁቬንቱስ እና ባየር ሙይንሽን አማካኙን ወደ ቡድናቸው ለማስመጣት እየተረባረቡ ነው።

ለቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ብቸኛዋን ግብ 52ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው አጥቂው ማርኩስ ቱራም ነው። የባየር ሌቨርኩሰኑ አሰልጣኝ ፔተር ቦስዝ ብሬመን ውስጥ ባለፈው ሰኞ 4 ለ1 ያሸነፉበት ቡድናቸው ላይ የተከላካይ እና አጥቂ ኹለት ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል። አሌክሳንደር ድራጎቪች እና ካሪም ቤላራቢ በአማካዩ ናዲም አሚሪ እና ፍሎሪያን ቪርትትስ ምትክ ቀዳሚ ተሰላፊ ኾነዋል። ባየር ሌቨርኩሰን ጥር ወር ውስጥ በሆፈንሃይም 2 ለ 1 ከተሸነፈ በኋላ ሽንፈት ገጥሞት አያውቅም።

Bundesliga | Borussia Mönchengladbach v Bayer Leverkusen - Kai Havertz
ምስል Reuters/I. Fassbender

ቅዳሜ ዕለት ከተከናወኑ አምስት የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ከፍተኛ ግብ የተቆጠረው በባየር ሙይንሽን እና ፍራንክፉርት ግጥሚያ ነበር። ባየር 5 ለ2 ያሸነፈበት ግጥሚያ። የደረጃ ሰንጠረዡን በ61 ነጥብ ይመራል። በአራት ነጥብ ከሚበልጠው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ማክሰኞ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። 

ሻልከ በሜዳው በአውግስቡርግ 3 ለ0 መሸነፉ አሰልጣኙ ላይ ጫና ፈጥሯል። የትናንቱ ሽንፈት በአምስት ጨዋታዎች አራተኛው ነበር። ባለፉት 9 ግጥሚያዎች ኹለት ግቦችን ብቻ ቡድናቸው ማስቆጠሩ ለአሰልጣኝ ዴቪድ ቫግነር ብርቱ ጫና አሳድሮባቸዋል። ሻልከ በ37 ነጥብ እዛው 8ኛ ደረጃው ላይ ተወስኗል። አውግስቡርግ አራት ጨዋታዎችን በተደጋጋሚ ከተሸነፈ በኋላ ማሸነፉ ነጥቡን ወደ 30 ከፍ አድርጎለት ከወራጅ ቃጣና ጠርዝ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ እንዲል አስችሎታል። 

የአውግስቡርጉ አሰልጣኝ ሐይኮ ሄርሊሽ ባለፈው ሳምንት የለይቶ ማቆያ ደንብን በመጣሳቸው ከስታዲየም ታግደው ነበር። በወቅቱም በቮልፍስቡርግ 2 ለ1 ተሸንፈው ነበር። ሻልከን ባሻነፉበት ግጥሚያ ግን ሑለት ጊዜ የኮሮና መለያ ምርመራ ተደርጎላቸው ነጻ በመኾናቸው ስታዲየም መግባት ተፈቅዶላቸዋል።  

ላይፕሲሽ ቲሞ ቬርነር ሔትትሪክ በሠራበት ግጥሚያ ማይንትስን በሜዳው 5 ለ0 አንኮታኩቷል። የጁሊያን ናግልስማን ቡድን ከመሪው ባየር ሙይንሽን በ7 ነጥብ ተበልጦ ዋንጫ የማግኘት ተስፋውን አለምልሟል። ባለፈው ሳምንት ከፍራይቡርግ ጋር አንድ እኩል ለተለያየው ኤር ቤ ላይፕትሲሽ የትናንቱ ድል ልዩ ነበር። በርካታ የአውሮጳ ቡድኖች ወደ ቡድናቸው ለማምጣት ያነጋገሩት የ24 ዓመቱ አጥቂ እስካሁን 24 ግቦችን ከመረብ አሳርፎ የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ ጋር ተጠግቷል። ሌቫንዶቭስኪ 27ኛ ግቡን ቅዳሜ ዕለት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 5 ለ2 ባሸነፉበት ግጥሚያ ነው ከመረብ ያሳረፈው። 

Red Bull Arena in Leipzig
ምስል picture-alliance/ZB/P. Endig

ሬድ ቡል ኃይል ሰጪ መጠጥን ለሚያመርተው ቡድን በባዶ ስታዲየም መጋጠሙ መልካም አጋጣሚ ነበር። የቡድኑ ደጋፊ ባለሐብትን በመቃወም የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊዎች በየጊዜው የተቃውሞ ድምፆችን ያሰሙ መስመር የለቀቊ መፈክሮችንም በሰፋፊ ጨርቆች ላይ ያሳዩ ነበር። ኤር ቤ ላይፕትሲሽ በደጋፊው ፊት በዚህ የጨዋታ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ኅዳር 1 ቀን ማይንትስን 8 ለ0 ድባቅ በመምታት ባሳፈረበት ግጥሚያ ቲሞ ቬርነር ሔትትሪክ ሠርቶ ሦስት ግብ የኾኑ ኳሶችንም ማመቻቸቱ  አይረሳም።  

እሁድ እለት ከነበሩ ሦስት ጨዋታዎች ኮሎኝ ከዱይስልዶርፍ ጋር ያደረገው የትናንቱ የራይን ደርቢ ግጥሚያ እጅግ አዝናኝ  ነበር። እስከመጨረሻዋ ሰአት ድረስ ተስፋ ያልቆረጡት ኮለኖች ከ2 ለ0 ተነስተው በጭማሪ ሰአት አቻ የምታደርጋቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ኮሎኝ በ34 ነጥብ 10ኛ ፎርቱና ዱይስልዶርፍ በ24 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ፎርቱና ዱይስልዶርፍ በትናንቱ ግጥሚያ ከወራጅ ቃጣና ጠርዝ ለመውጣት የነበረውን ዕድል ነበር ያመከነው።

በሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች ውጤት መሠረትም፦ ባየር ሌቨርኩሰን ከ5ኛ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከነበረበት 3ኛ ደረጃ ወደ 5ኛ አሽቆልቁሏል። ላይፕሲሽ ከ4ኛ ደረጃ ወደ 3ኛ ከፍ በማለት ዶርትሙንድን  በሦስት ነጥብ ልዩነት ይከተላል። 57 ነጥብ ያለው ዶርትሙንድ ከመሪው ባየር ሙይንሽን የሚበለጠው በአራት ነጥብ ብቻ ነው። ኹለቱ የጀርመን ኃያላን ቡድኖች ነገ በሚያደርጉት ልዩ ግጥሚያ በጀርመንኛው «ዴር ክላሲከር» አሸናፊ የሚኾነው የዋንጫው ባለቤት ለመኾን በሚደረገው ፍልሚያ ወሳኝ ምዕራፍ ያስመዘግባል። ስድስት ጊዜያት በተከታታይ ላሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነገ ባየር ሙይንሽንን መግጠም ብዙም ስጋት ውስጥ የሚጥለው አይመስልም። ለዚያም ይመስላል የቡድኑ የስፖርት ኃላፊ ሚሻኤል ዞርክ፦ «ይኽን ጨዋታ ማሸነፍ ይገባናል» ያሉት። እንደ አሰልጣኝ ሉዚያን ፋቭሬ ከኾነ ደግሞ፦ የመሀል ተከላካዩ ማትስ ሑመልስ  ለማሸነፉ «99 በመቶ» ዝግጁ ነው።

Großbritannien Fußball | Premier League | Watford v FC Liverpool
ምስል Reuters/Action Images

እንግሊዝ ውስጥ የፕሬሚየር ሊግ ተጨዋቾች  ላይ በተደረገ የኮሮና ተሐዋሲ መለያ አንዳንድ ተጨዋቾች ላይ ተሐዋሲው መገኘቱ ተገልጧል። ብዙዎችን ያስደመመው ግን በሻምፒዮንስ ሊግ ሊቨርፑል አትሌቲኮ ማድሪድን በጋበዘበት ግጥሚያ ታዳሚ የነበሩ 41 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተው መሞታቸውን አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል። በያኔው ግጥሚያ ከ52 ሺህ በላይ ታዳሚዎች ስታዲየም ተገኝተው ነበር። እናም እንደጥናቱ ከኾነ፦ በዕለቱ ግጥሚያ 3,000 ያኽል የአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች ወደ እንግሊዝ አቅንተው ስታዲየም ውስጥ ጨዋታውን ተመልክተዋል። ስፔን የኮሮና ተሐዋሲ ብሪታንያ ውስጥ እጅግ ከመስፋፋቱ ቀደም ብሎ በብርቱ ከተጠቊ ሀገራት መካከል  ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች።  የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዳግም ሊጀመር ዳር ዳር ባለበት በዚህ ወቅት ይኽ ዘገባ መውጣቱ ብዙዎችን አስደንግጧል። 

ከሰሞኑ እንደሚጀምር ለተነገረለት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በ25 ነጥብ ልዩነት እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑልን ጨምሮ 20ዎቹም ቡድኖች ከዛሬ ጀምሮ ልምምድ መሥራት እንዲጀምሩ ተፈቅዶላቸዋል። ተጨዋቾቹ ልምምዱን ታዲያ ማድረግ የሚችሉት ከቡድናቸው አባላት ውስጥ ለኹለት በመጣመር ወይንም ለሦስት በመቀናጀት ነው። እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሠረት ብሪታንያ እስከ ዛሬ ድረስ  ከ260 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተዋል። ከ36 ሺህ በላይ ሰዎች በተሐዋሲው ምክንያት ለኅልፈት ተዳርገዋል። በኮሮና ምክንያት የተቋረጠው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰኔ 5 አለያም ሰኔ 12 ሊጀምር እንደኾነ እየተነገረ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ