1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 21 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 21 2015

ወራጅ ቀጣና ግርጌ 20ኛ ደረጃን የሙጥኝ ብሎ ያጠናቀቀው ሳውዝሐምፕተን የማታ ማታ ሊቨርፑልን አስጨንቆም ቢሆን አቻ በመውጣት ወደታችኛው ዲቪዚዮን ተሰናብቷል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ባለቀ ሰአት ዋንጫ የመውሰድ እድሉን አሳልፎ ሰጥቷል ። ቅዳሜ ዕለት አቻ የወጣው ማይንትስ ለባየርን ሙይንሽን ውለታ ሠርቷል ።

https://p.dw.com/p/4RwTP
Fussball Bundesliga, 34. Spieltag l Borussia Dortmund vs FSV Mainz 05 l Enttäuschung
ምስል Leon Kuegeler/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ወራጅ ቀጣና ግርጌ 20ኛ ደረጃን የሙጥኝ ብሎ ያጠናቀቀው ሳውዝሐምፕተን የማታ ማታ ሊቨርፑልን አስጨንቆም ቢሆን አቻ በመውጣት ወደታችኛው ዲቪዚዮን ተሰናብቷል ። ሳውዝሀምፕተኖች እስከ ዛሬ የት ነበሩ ያሰኛል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ባለቀ ሰአት ዋንጫ የመውሰድ እድሉን አሳልፎ ሰጥቷል ። ቅዳሜ ዕለት አቻ የወጣው ማይንትስ ለባየርን ሙይንሽን ውለታ ሠርቷል ። ባየርን ሙይንሽን ዋንጫውን ለመውሰድ ኮሎኝን ማሸነፉ ብቻ በቂ አልነበረም ። ሔርታ ቤርሊን እና ሻልከ ከሊጉ ተሰናብተዋል ። ሽቱትጋርት በቡንደስሊጋው ለመቆየት አለያም ለመሰናበት ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ሆኖ ከጨረሰው ሐምቡርግ ጋር ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታ ይጠብቀዋል ። 

አትሌቲክስ

ሞሮኮ ውስጥ በተከናወነው የራባት ዳያመንድ ሊግ የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ገንነው ወጥተዋል ። በሴቶች የ1500 ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ፦ 3:54.03 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች ። የሀገሯ ልጆች ፍሬወይኒ ኃይሉ፤ ብርቄ ኃየሎም እና ወርቅነሽ መለሰ እስከ አራተኛ ደረጃ ተከታትለው በመግባት ለድል በቅተዋል ። አትሌት ፍረወይኒ ኃይሉ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው 3:57.65 ሮጣ በማጠናቀቅ ነው ።  አትሌት ብርቄ ኃየሎም ለጥቂት 0.01 ማይክሮ ሰከንድ በመቀደም ሦስተኛ ወጥታለች ። ብርቄ በአፍሪቃ ከ18 ዓመት በታች ምርጥ ሰአት ያስመዘገበች አትሌት ናት ። ወርቅነሽ የገባችበት ሰአት 4:01.81 ነው ።

የአትሌቲክስ ፉክክር፦ ምስል ከክምችት ማኅደር
የአትሌቲክስ ፉክክር፦ ምስል ከክምችት ማኅደርምስል Aleksandra Szmigiel/REUTERS

በወንዶች የ3000 ሜትር የመሰናከል የሩጫ ፉክክር አትሌት ኤል ባካሊ በሀገሩ ደጋፊዎች ፊት ክብረወሰን ሰብሮ አሸንፏል ። የገባበት 7:56.68 የራሱም ምርጥ ሰአት ተብሎ ተመዝግቦለታል ።

ካናዳ ውስጥ በተከናወነው የኦታዋ ኢንተርናሽናል ማራቶን ፉክክርም በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸነፊ ሆነዋል ። በወንዶች አትሌት ይሁንልኝ አዳነ 2:08:22 በመሮጥ በአንደኝነት አጠናቋል ። አብርሃ ገብረጻዲቅ 2:09:13 እንዲሁም አብዲ ገለቹ 2:10:38 በመሮጥ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል። አራተኛ ደረጃውም የተያጠው በኢትዮጵያዊው አትሌት ዐይቸው በንቲ ነው።  በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዋጋነሽ መካሻ 2:24:47 በመሮጥ አሸንፋለች ። የካናዳዋ ማሊንዲ ኤልሞር እና ለጀርመን የምትሮጠው ሜላት ቀጀላ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል ።  ሜላት በዋጋነሽ በ3 ደቂቃ ከ3 ሰከንድ ነው የተበለጠችው ። በማሊንዲ ግን በ6 ሰከንድ ብቻ ።

እግር ኳስ

በሰሜን ጀርመን ሐምቡርግ ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የ«ኢትዮ ጀርመን የ2023 እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር» በኢትዮ ኮሎኝ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል ። ካለፈው ዐርብ ጀምሮ እስከ እሁድ ድረስ በነበረው የእግር ኳስ ግጥሚያ ከተለያዩ የጀርመን ግዛቶች የተውጣጡ ዐሥር ቡድኖች ተካፋይ ሆነዋል ። ኢትዮ ኮሎኝ ኢትዮ ፍራንክፉርትን በጨዋታም በግብም በመብለጥ 3 ለ0 አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል ። የኮሎኝ ከተማ አካባቢ ነዋሪ እና የኢትዮ ኮሎኝ ቡድን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ አበበ ።  

አቶ ዳንኤል ብሥራት በአውሮጳ የኢትዮጵያውያኖች የባህል እና የስፖርት ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው ። እሳቸውም ከሁለት ወራት በኋላ ሆላንድ ዋና ከተማ አምስተርዳም ውስጥ ለ18ኛ ጊዜ ስለ ሚከናወነውን ውድድር እና የባህል መሰናዶ ቀጣዩን ብለዋል ። ከኢትዮጵያ ስድስት ቡድኖች መጋበዛቸውንም አክለዋል ።

ወደ ቡንደስሊጋው ለመመለስ ጫፍ የደረሰው ሐምቡርግ ደጋፊዎች
ወደ ቡንደስሊጋው ለመመለስ ጫፍ የደረሰው ሐምቡርግ ደጋፊዎችምስል Uwe Anspach/dpa/picture alliance

ፕሬሚየር ሊግ

ሉቶን ታውን ከ31 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየ ሊግ ማለፍ ችሏል ። ሉቶን በዌምብሌይ ስታዲየም ከኮቬንትሪ ሲቲ ጋር ያደረገው የ90 ደቂቃ ጨዋታ አንድ እኩል በመጠናቀቁ በተሰጠው የፍጹም ቅጣት ምት መለያ 6 ለ5 አሸንፎ ነው ማለፍ የቻለው ።  በርንሌይ እና ሼፊልድ ዩናይትድም ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ተመልሰዋል ። በአንጻሩ፦ ላይስተር ሲቲ፣ ሊድስ ዩናይትድ እና ሳውዝሀምፕተን የመጨረሻ ደረጃ ይዘው ከፕሬሚየር ሊጉ ተሰናብተዋል ።  በተለይ ዘንድሮ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ ከፕሬሚየር ሊጉ የተሰናበተው ሳውዝሀምፕተን ሊቨርፑልን ትናንት አስጨንቆ ነበር ። ከ2 ለ0 ተነስቶ ሊቨርፑልን 4 ለ2 በመምራት ለማሸነፍም ተቃርቦ ነበር ። ከሊቨርፑል ጋር የመጨረሻ ጨዋታውን ያደረገው ሮቤርቶ ፊርሚኖ፣  ዲዬጎ ጆታ እና ኮዲ ጋክፖ ግብ አስቆጥረው ቡድናቸውን ከውርደት ታድገዋል ። ሊቨርፑል እና ብራይተን ለአውሮጳ ሊግ ሲያልፉ፤ ኒውካስል ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፤ አርሰናል እና ለድል የበቃው ማንቸስተር ሲቲ በቀጣይ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ተካፋይ ናቸው ። ኤቨርተን 17ኛ ደረጃ ይዞ እንደምንም ለጥቂት ከመሰናበት ተርፏል ።

ዘንድሮ 12ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ቸልሲ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ፍራንክ ላምፓርድን በማሰናበት ማውሪሲዮ ፖቼቲኖን አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል ።  የ51 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ ፖቸቲኖ በአምስት ዓመት ውስጥ ለቸልሲ ስድስተኛው ቆሚ አሰልጣኝ ሆነዋል ማለት ነው ። ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ የቶትንሀምሆትስፐር እና የፓሪ ሳንጃርሞ የቀድሞ አሰልጣኝ ነበሩ ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋም ሀደይንሃይም እና ዳርምሽታድት ወደ ቡድንደስሊጋው ማለፍ ችለዋል ። በተለይ የሀይደንሀይም ቡድን ግስጋሴ ጀርመን ውስጥ በርካቶችን አስደምሟል። ሀይደንሀይም በአጭር ጊዜያት ወደ ቡንደስሊጋው ማለፉ ለቡድኑ ደጋፊዎች አሁንም ድረስ የፌሽታ ምንጭ ሆኗል ።  

ባለቀ ሰአት ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ዋንጫውን የመነተፈው ባየርን ሙይንሽን ተጨዋቾች
ባለቀ ሰአት ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ዋንጫውን የመነተፈው ባየርን ሙይንሽን ተጨዋቾች ምስል Alexander Hassenstein/Getty Images

በቡንደስሊጋው የቆየ ታሪክ ያለው ሀምቡርግ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ለመውጣት እና እነሀይደንሀይምን ለመከተል ከሰሞኑ የደርሶ መልስ ጨዋታ ይጠብቀዋል ። ሐምቡርግ ወደ ቡንደስሊጋው የሚገባ መስሎት ደጋፊዎቹ ቦርቀው ነበር ። የሀደንሀይም ውጤትን ግን መጠበቅ ነበረበት ። የፊታችን ሐሙስ እና የዛሬ ሳምንት በሚኖረው ጨዋታ ሽቱትጋርትን ካሸነፈ ነው ወደ ቡንደስሊጋ የሚመለሰው ። ሽቱትጋርት በቡንደስሊጋው 16ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቁ እዛው ለመቆየት የደርሶ መልስ የመጨረሻ ጨዋታ ማድረግ እና ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። እናስ ሽቱትጋርት ወይንስ ሐምቡርግ? ጨዋታዎቹን መከታተል ነው ።

በቡንደስሊጋው ጃማል ሙሲያላ ባየርን ሙይንሽንን ባለቀ ሰአት ታድጓል ። ዋንጫውን ይወስዳል የተባለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ግን በ24ኛው ደቂቃ ላይ ዋንጫውን ከእጁ አሳልፎ ሰጥቷል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከ11 ዓመታት ግድም በኋላ የቡንደስሊጋውን ዋንጫ ሊያነሳ ነው ተብሎ ነበር ። የመጨረሻ ጨዋታውን ሁለት እኩል እንዲያጠናቅቅ ያስገደደው ማይንትስ ጉድ አደረገው እንጂ ። ባየርን ሙይንሽን ኮሎኝን 2 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን እንደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ 71 በማድረስ በግብ ክፍያ ግን የተለመደ ዋንጫውን ወስዷል ። ለቦሩስያ ዶርትሙንድ ደጋፊዎች መሪር ሐዘን፤ ለባየርን ሙይንሽን ደግሞ የማታ ሲሳይ ። ላለው ይጨመርለታል እንዲል ባየርን ሙይንሽን በወንዶቹ ለ33ኛ እንዲሁም በሴቶች ቡድኑ ለ5ኛ ጊዜ ዋንጫ አንስቷል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ