የግንቦት 22 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 22 2014በበርካቶች ዘንድ እጅግ በልዩ ኹኔታ ሲጠበቅ የነበረው የሪያል ማድሪድ እና ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ግጥሚያ አዘጋጇ የፓሪስ ከተማን ወደ ኹከት እና ብጥብጥ ቀይሮት ነበር። ለኹከቱ በዋናነት ተጠያቂ የተደረጉት በሪያል ማድሪድ 1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው ሊቨርፑል ቡድን ደጋፊዎች ናቸው ተብሏል። ኹከቱን ተከትሎ የፈረንሳይ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚንስትር ደረጃ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የደጋፊዎች ኹከት እና የፈረንሳይ መንግሥት ዛሬ የደረሰበትን ውሳኔ በተመለከተ ከፓሪስ ከተማ ቃለ መጠይቅ አድርገናል። የአማራ ክልል ሐዋሳ ከተማ ውስጥ እተካሄደ ባለው የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ላይ እንደማይሳተፍ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ዐስታውቋል። የጽ/ቤቱ የስልጠናና ውድድር ኃላፊን አነጋግረናል። በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ኖቫክ ጄኮቪች እና ራፋኤል ናዳል ለሩብ ፍጻሜ ደርሰዋል። በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር ሁለት ሩስያውያት ተወዳዳሪዎች ለሩብ ፍጻሜ በቅተዋል።
እግር ኳስ
በሻምፒዮንስ ሊግ ሊቨርፑል፣ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ እና ደጋፊዎች የተመኙት አልሆነም። ቡድናቸው በፕሬሚየር ሊግ በማንቸስተር ሲቲ በአንድ ነጥብ ልዩነት ያጣውን ዋንጫ በሻምፒዮንስ ሊግ ድል ያካክሳል በሚል ብዙዎች ተስፋ ሰንቀው ነበር። ለዚያም ይመስላል አሰልጣኙ ደጋፊዎች ትኬት ኖራቸውም አልኖራቸው የፍጻሜው ውድድር ወደ ሚከነወንበት ፓሪስ ከተማ እንዲያቀኑ የተናገሩት። ይህ ንግግራቸው ግን የማታ ማታ መዘዝ አስከትሏል። ሪያል ማድሪድ ቅዳሜ ዕለት በፈጣኑ አጥቂው ቪንሺዬስ ጁኒየር ብቸኛ ግብ ለድል ሲበቃ ወደ ከተማዪቱ የተመሙ ከ62 ሺህ በላይ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ማመን አልቻሉም። የፍጻሜው ጨዋታ ሳይጀመር 30 ደቂቃ ያህል መራዘሙ እና ሽንፈቱ ተደማምሮ የሊቨርፑል ደጋፊዎችን እጅግ አበሳጭቷል። የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1956 አንስቶ ለ14ኛ ጊዜ የአውሮጳ ዋንጫን ምንሳት በመቻላቸው ወደ ሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ያቀኑት በፌሽታ ነው። በንዴት እና በሐዘን የተዋጡት የሊቨርሉል ደጋፊዎች ደግሞ አብዛኞቹ በፓሪስ ጎዳናዎች ከፖሊስ ጋር ግብ ግብ ሲፈጥሩ አምሽተዋል።
ሪያል ማድሪድ በቅዳሜው ድል ሊቨርፑልን በፍጻሜ ሲረታ ለሁለተኛ ጊዜ መኾኑ ነው። ከአራት ዓመት በፊትም ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን በሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ገጥሞ 3 ለ1 ድል በማድረግ ዋንጫውን አንስቶ ነበር። የኹኔታዎች መደጋገም የሊቨርፑል ዋነና ደጋፊዎችን እጅግ ሳያበሳጫቸው አልቀረም። ቅዳሜ ዕለት ሰላማዊቱ የፓሪስ ከተማን የጦር ቀጠና አስመስለዋት ነበር ያመሹት።
ፓሪስ ከተማ ውስጥ በቅዳሜው የሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር ወቅት በተከሰተ የደጋፊዎች ኹከት ከ200 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል። የፓሪስ ከተማ ፖሊስ ከ100 በላይ ሰዎችን ከኹከቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተገልጧል። ፈረንሳይ እንደ ጎርጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2023 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የራግቢ ውድድሮችን ታስተናግዳለች። በ2024 ደግሞ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የሚከናወኑት እዛው ፈረንሳይ ውስጥ ነው። ይህ በመሆኑም የፈረንሳይ መንግሥት የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ላይ የተከሰተውን ኹከት የሚያጣራ ቡድን አቋቁሞ ዛሬ የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባ አድርጓል። የፈረንሳይ የስፖርት ሚንስትር አሜሊ ኡዲያ-ካስቴራ ኃላፊነቱን የሚወስዱት ቲኬት ያልገዙ አልያም የተጭበረበረ ቴኬት የያዙ በዋናነት የሊቨርፑል ደጋፊዎች ናቸው ብለዋል።
ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን 1 ለ0 ያሸነፈበት የቅዳሜው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ውድድር ባስከተለው የደጋፊዎች ኹከት ፖሊስ የተጠቀመው አስለቃሽ ጢስ በኹከቱ የሌሉበት ሕጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተተችቷል።
ከዚሁ ከሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር ሳንወጣ የሪያል ማድሪድ አምበል እና ተከላካይ ብራዚሊያዊው ማርሴሎ ሪያል ማድሪዶች ዋንጫ ተሸክመው ወደ ሳንቲያጎ ቤርናባው ከገቡ በኋላ ከቡድኑ መሰናበቱን በእንባ ተውጦ ዐሳውቋል። ከሪያል ማድሪድ ጋር አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን መውሰዱን ለመግለጥ በሚልም በአምስቱም ጣቶቹ ላይ አምስት ትልልቅ የወርቅ ቀለበቶችን አስሮ ታይቷል። የ34 ዓመቱ ማርሴሎ ከ15 ዓመት የሪያል ማድሪድ ቆይታው በኋላ ሲሰናበት በበርካታ ድሎች ተሞልቶ ስለነበር ደበስታ፣ ሲቃ እና ሐዘንም ተውጦ ነበር። በሚቀጥለው የበጋ ወር ከሪያል ማድሪድ የሚሰናበተው ጋሬት ቤል በበኩሉ ከደጋፊዎች ዘንድ በጭብጨባ ድጋፍ ተሰጥቶታል። እሱም በአንጻሩ ለደጋፊዎች በማጨብጨብ ምስጋናውን ዐሳይቷል። የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ለተሰጣቸው ድጋፍ በስታዲየም ለተገኙ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘንድሮ አራት ዋንጫዎችን ያነሳሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ በስተመጨረሻ በሁለት ዋንጫዎች ብቻ ተወስነዋል። በኤፍ ኤ ካፕ እና ካራባዎ ዋንጫዎች። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ማንቸስተር ሲቲ እንደምንም ጉረሮ ለጉረሮ ተናንቆ በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ነጥቋቸዋል። የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫንም ቢሆን ሪያል ማድሪድ በትግል ነው የወሰደው ማለት ይቻላል። በተለይ የሳዲዮ ማኔ የግብ ማእዘን የመለሰው እና ሞ ሳላህ ከርቀት የተላከለትን ኳስ በድንቅ ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢልክም በሪያል ማድሪዱ ግዙፉ ግብ ጠባቂ ቲቦ ኮቱዋ የተጨናገፈበት ይጠቀቃሳሉ። ሁለቱ ኳሶች ግብ ከመሆን ያጨናገፈው ግብ ጠባቂ ሌላ ቢሆን ውጤቱ ምን ይመስል እንደነበር ግልጥ ነው። ቅዳሜ ዕለት ቲቦ ኮቱዋ ሊቨርፑልን አሸነፈ ማለት ይቀላል። ሊቨርፑል ዘንድሮ ሁለት ዋንጫዎችን ወስዶ ሁለት የዋንጫ ፍጻሜ ላይ እጅግ በጠበበ ልዩነት ሁለተኛ መሆኑ የቡድኑን ጥንካሬ አመላካች ነው። አሰልጣኙም ሽንፈቱን በማንም ሳያመካኙ «እነሱ አገቡ እኛ አላገባንም። የማሸነፍ እና የመሸነፍ ልዩነትም ያ ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት በበጀት ችግር ምክንያት ሐዋሳ ከተማ ውስጥ እተካሄደ ባለው የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ የአማራ ክልል እንደማይሳተፍ ዐስታወቀ። የጽ/ቤቱ የስልጠናና ውድድር ኃላፊ አቶ ምትኩ አክሊሉ ዛሬ ለዶይቸ ቬሌ (DW)እንዳመለከቱት በአማራ ክልል ምስራቅ ዞኖች ከነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ ብዙ ዞኖች የበጀት እጥረት ስላጋጠናቸው በውድድሩ መሳተፍ አልቻሉም።
የተለያዩ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በውድድሩ መሳተፍ እንዳልተቻለ አቶ ምትኩ ተናግረዋል። አጠቃላይ በውድድሩ ለመሳተፍ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚጠይቅም አስረድተዋል። በተመሳሳይ መልኩ በቅርቡ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የሴቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ የአማራ ክልል መሳተፍ እንዳልቻለም ለባህር ዳር ወኪላችን ዓለምነው መኮንን አክለው ተናግረዋል። አገር አቀፍ የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ከግንቦት 21 ጀምሮ እስከ ሰኔ 4 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካኼደ ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፦ ይህ ውድድር ከዕውቅናው ውጪ እንደሆነ ዛሬ በተጻፈ ደብዳቤ ይፋ አድርጓል። «አትሌቲክሱን በሚመለከት ለሚነሱ ማናቸውም ችግሮች» ፌዴሬሽኑ «ኃላፊነት የማይወስድ እና ተጠያቂ የማይሆን መሆኑን» በደብዳቤው ገልጧል። «በሕግ አግባብ» የራሱን ርምጃ እንደሚወስድም ፌዴሬሽኑ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሩ ዛሬ ይፋ አድርጓል። የደብዳቤው ግልባጭም ለየክልሎቹ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ተልኳል።
የሜዳ ቴኒስ
በፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ራፋኤል ናዳል እና ኖቫክ ጄኮቪች ወደ ሩብ ፍጻሜ ማለፋቸውን አረጋገጡ። ስፔናዊው የሜዳ ቴኒስ ባለድል ራፋኤል ናዳል ለሩብ ፍጻሜው የበቃው ተጋጣሚው ፌሊክስ ኦውገር-አሊያሲምን ትናንት አምስት ዙር በፈጀው ግጥሚያ ሁለት ጊዜ 6 ለ3 እና 6 ለ2 በማሸነፍ ነው። ቀሪዎቹን ሁለት ዙሮች ፌሊክስ ኦውገር-አሊያሲም 6 ለ3 እና 6 ለ3 ነው። በሌላ ግጥሚያ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች በሦስት ዙር ሁለት ጊዜ 6 ለ3 እና 6 ለ1 አሸንፏል። በዚህም ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፉት ራፋኤል ናዳል እና ኖቫክ ጄኮቪች ነገ ይጋጠማሉ።
በሴቶች ውድድር የሩስያ ተጨዋቾች ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፈዋል። ዳራያ ካሳትኪና ዛሬ ፓሪስ ውስጥ ከጣሊያናዊቷ ካሚላ ጂዮርጂ ጋር ባደረገችው ውድድር ሁለት ጊዜ 6 ለ2 አሸንፋ ለፍጻሜ በቅታለች። ቬሮኒካ ኩዴርሜቶቫ በበኩሏ አሜሪካዊቷ ማዲሶን ኪይስን ሁለት ጊዜ 6 ለ3 እ3ና 6 ለ1 አሸንፋ ነው ለሩብ ፍጻሜ የደረሰችው። ዳራያ ካሳትኪና ቬሮኒካ ኩዴርሜቶቫ ነገ በሩብ ፍጻሜው ይጋጠማሉ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ