1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 28 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 28 2015

ሐንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ውስጥ ከነሐሴ 13 እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ) ለሚከናወነው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ለምረጥ ሒደቱ ቀጥሏል ። በቀጣዩ የውድድር ዘመን ሐምቡርግ በጀርመን ቡንደስሊጋ ተሳታፊ ለመሆን ሽቱትጋርት ደግሞ ከቡንደስሊጋው ላለመሰናበት የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ ማታ ያደርጋሉ ።

https://p.dw.com/p/4SDC6
DFB Cup - Finale - RB Leipzig v Eintracht Frankfurt
ምስል Annegret Hilse/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሐንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ውስጥ ከ74 ቀናት በኋላ (ከነሐሴ 13 እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ) ለሚከናወነው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ለምረጥ ሒደቱ ቀጥሏል ። በቀጣዩ የውድድር ዘመን ሐምቡርግ በጀርመን ቡንደስሊጋ ተሳታፊ ለመሆን ሽቱትጋርት ደግሞ ከቡንደስሊጋው ላለመሰናበት የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ ማታ ያደርጋሉ ። ሽቱትጋርት ባለፈው ሳምንት በሜዳው ሐምቡርግን 3 ለ0 ረትቷል ። ሐምቡርግ ምሽቱን በሜዳው የሞት ሽረት ግጥሚያ ይጠብቀዋል ።  ላይፕትሲሽ የጀርመን እግር ኳስ ዋንጫን (DFB) በድጋሚ ወስዷል ። ክሪስቶፈር ንኩንኩ የፍጻሜ ጨዋታው ኮከብ ሆኖ ወጥቷል ።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንደተለመደው አመርቂ ድሎችን አስመዝግበዋል ። ስዊድን ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው የአዲዳስ ስቶክሆልም ማራቶን ፉክክር በወንድም በሴትም ዘርፍ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አሸንፈዋል ። በወንዶች ፉክክር አትሌት አሸናፊ ሞገስ 2:10:32 በመሮጥ በእርግጥም አሸናፊ መሆኑን አስመስክሯል ። ደራራ ሁሪሳ ከ29 ሰከንድ በኋላ፤ ጸጋዬ መኮንን ደግሞ ከ2 ደቂቃ በኋላ አሸናፊን ተከትለው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል።   

አትሌቶች ለመሮጥ ተዘጋጅተው
አትሌቶች ለመሮጥ ተዘጋጅተውምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር፦ 2:30:39 የሮጠችው ሲፋን መላኩ በአንደኛነት ለድል በቅታለች ።  ሶሮሜ ነጋሽ ከ2 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ በኋላ ተከትላ በመግባት የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ።  የኔነሽ ዲንቄሳ ከሲፋን 6 ደቂቃ ዘግይታ በሦስተኛነት አጠናቃለች ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለቡዳፔስቱ የዘንድሮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድር ተሳታፊዎችን በዓለም አቀፍ ውጤታቸው መሠረት መምረጡን ዐስታውቋል ።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አመርቂ ድሎችን ካስመዘገቡ አትሌቶች መካከል በማጣሪያ ውድድሩ ከሴቶች ለተሰንበት ግደይ እና አልማዝ አያና ይካተታሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር ። አልማዝ አያና 1 ጊዜ የኦሎምፒክ፣ 2 ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም 2 ጊዜ የዲያመንድ ሊግ ባለድል ነች ። ለተሰንበት ግደይም 2 ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና ወርቅ እና ብር፤ እንዲሁም በኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኘች ድንቅ አትሌት ናት ።

የኦሎምፒክ አርማ እና መወዳደሪያ ስፍራ
የኦሎምፒክ አርማ እና መወዳደሪያ ስፍራምስል Vesa Moilanen/dpa/picture alliance

ለማጣሪያው የተመረጡ አትሌቶች፦ ሚዛን ዓለም፣ እጅጋየሁ ታዬ፣ ቦስና ሙላቴ፣ ፋንታዬ በላይነህ፣ ፎቴን ተስፋይ፣ ጽጌ ገ/ሰላማ እና በተጠባባቂነት ሰናይት ጌታቸው ናቸው። በወንዶች ፉክክር እንደሚመረጥ ሲጠበቅ የነበረው በሪሁ አረጋዊ ቀዳሚ ሆኖ ተመርጧል ። ሰለሞን ባረጋ፣ ታደሰ ወርቁ፣ ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ያሲን ሃጂ፣ ጭምዴሣ ደበሌ እና በተጠባባቂነት ገመቹ ዲዳ መመረጣቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል ።  ለመሆኑ ምርጫውን በተመለከተ የአትሌቲክስ ስፖርት ተንታኞች ምን ይላሉ?

በርካታ ድንቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ያስገኘው 52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሁለት ሳምንት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ተከናውኖ ነበር። ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ ካስቆጠረው የውድድር ዘርፍ ለዓለም ሻምፒዮና አትሌቶችን ለመመረጥ ያስችላልም ተብሎ ነበር ። በውድድሩ በ10 ሺህ ሜትር በወንዶች ቦኪ ድሪባ፣ ይስማው ድሉ፣ ሐብተማሪያም አማረ፤ በሴቶች በኩል ለምለም ኃይሉ፣ ዘይነባ ይመር እና ምሥራቅ ፍቅሩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ወጥተው ነበር ። አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድር ስማቸውን ከዘረዘራቸው አትሌቶች መካከል አንዳቸውም የሉበትም ።  በ52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውጤት ካስመዘገቡ አትሌቶች ለዓለም ሻምፒዮና ፉክክር አለመመረጣቸው ከውድድሩ ይገኛል የተባለው ግብ አልተሳካም ማለት ይቻል ይሆን? በኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮ ስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ምሥጋናው ታደሰ።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር የማጣሪያ ውድድር ዘንድሮ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ሐዋሳ ከተማ ውስጥ ይከናዋናል ተብሎ ነበር ።  አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሐሳቡን በመቀየሩ የማጣሪያ ውድድሩን ስፔን ውስጥ እንደሚያከናውንም ገልጿል ። ቀደም ሲል የማጣሪያ ውድድሮች የሚከናወኑት ሆላንድ ውስጥ ዓለም አቀፍ የስፖርት መገናኛን በመሠረቱት በማናጀር ጆስ ሄርመንስ አማካይነት ሄንግሎ ውስጥ ነበር ። ዘንድሮ ስፔን ለምን ተመረጠች?

እግር ኳስ

ዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫንም ወስዷል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ሦስተኛ ዋንጫ የመውሰድ ዕድል ይኖረው ይሆናል ። የፊታችን ቅዳሜ ማታ በፍጻሜው ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ጋር ይፋለማል ።

ክሪስቶፈር ንኩንኩ አንድ ግብ በማስቆጠር እና ሁለተኛውንም በማመቻቸት ኮከብ ሆኖ ወጥቷል
ክሪስቶፈር ንኩንኩ አንድ ግብ በማስቆጠር እና ሁለተኛውንም በማመቻቸት ኮከብ ሆኖ ወጥቷልምስል Sören Stache/dpa/picture alliance

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቀጣይ የውድድር ዘመን 18ኛ ተሳታፊ ቡድን ዛሬ ማታ ይለያል ። በቡንደስሊጋ ሕግ መሰረት በደረጃ ሰንጠረዡ 17ኛ እና 18ኛ ያገኙ ቡድኖች ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ተሰናብተው ከ2ኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ሁለት ቡድኖች ያድጋሉ ። 16ኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ደግሞ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተና ሆኖ ካጠናቀቀው ቡድን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ እንዲያደርግ ይገደዳል ። ካሸነፈ በቡንደስሊጋው ይቆያል ከተሸነፈ ለባለተራው ቦታውን ይለቃል ።

ዘንድሮ ሻልከ እና ሔርታ ቤርሊን ከቡንደስ ሊጋው ተሰናብተዋል ። በሁለተኛ ዲቪዚዮን ዋንጫ ያነሳው ሀይደንሀይም እና ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ዳርምሽታድት ቡንደስሊጋውን ተቀላቅለዋል ። በአውስቡርግ በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ 16ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሽቱትጋርት በቡንደስሊጋው ለመቆየት ዛሬ አቻ ብቻ ይበቃዋል ። ባለፈው ሳምንት በሜዳው ሐምቡርግን 3 ለ0 ረትቷል ። ሐምቡርግ ምሽቱን በሜዳው የሞት ሽረት ግጥሚያ ይጠብቀዋል ። ወደ ቡንደስሊጋው ዳግም ለመመለስም ከ3 ግብ በላይ ማስቆጠር ይጠበቅበታል ። ይሳካለት ይሆን? ምሽቱን የምንመለከተው ነው ።

በቡንደስሊጋው የሦስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ላይፕትሲሽ ፍራንክፉርትን 2 ለ0 ድል አድርጎ የጀርመን እግር ኳስ ዋንጫን (DFB) በድጋሚ ወስዷል ። በፍጻሜ ግጥሚያው ክሪስቶፈር ንኩንኩ አንድ ግብ በማስቆጠር እና ሁለተኛውንም በማመቻቸት ኮከብ ሆኖ ወጥቷል ። ፈረንሳዊው ግብ አዳኝ በቀጣዩ የጨዋታ ዘመን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለቸልሲ እንደሚሰለፍ ከተነገረም ወራት ተቆጥሯል ። እናም ከሀምሌ ወር በኋላ ክሪስቶፈር ንኩንኩን በቀይ ሳይሆን በሰማያዊ መለያ ነው የምንመለከተው ማለት ነው ።

በሴቶች የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር የጀርመን ቮልፍስቡርግን አሸንፎ ዋንጫ ያነሳው ባርሴሎና ቡድን
በሴቶች የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር የጀርመን ቮልፍስቡርግን አሸንፎ ዋንጫ ያነሳው ባርሴሎና ቡድንምስል Piroschka Van De Wouw/REUTERS

አርጀንቲናዊው የ35 ዓመቱ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ እና የ37 ዓመቱ ስፔናዊ ተከላካይ ሠርጂዮ ራሞስ ከፈረንሳይ ፓሪ ሳን ጃርሞ ጋር የነበራቸው ቆይታ የመጨረሻው ጨዋታ በሽንፈት ተጠናቋል ።  የፈረንሳይ ሊግ ዋንጫን ዘንድሮ ያነሳው ፓሪ ሳን ጃርሞ ቅዳሜ ዕለት በመጨረሻ ግጥሚያው በሊግ አንድ የደረጃ ሰንጠረዥ አማካይ በሚገኘው ክሌሞን ቡድን የ3 ለ2 ሽንፈት ደርሶበታል ። ሠርጂዮ ራሞስ በዚህ የመጨረሻ ጨዋታው አንድ ግብ አስቆጥሯል ። ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ሠርጂዮ ራሞስ ከሪያል ማድሪድ ወደ ፓሪስ ከተማ አቅንተው በፓሪ ሳንጃርሞ የቆዩት ለ2 ዓመታት ብቻ ነው ። ሠርጂዮ ራሞስ እና ሊዮኔል ሜሲ ወደ ሣዑዲ ዓረቢያ አቅንተው ምናልባትም በአል ናስር ቡድን ከክርስቲያቲያኖ ሮናልዶ ጎን ሊሰለፉም ይችሉ ይሆናል የሚሉ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። 

በሌላ ዜና፦ ካሪም ቤንዜማ በሪያል ማድሪድ የመጨረሻ የጨዋታ ዘመኑ አቻ የምታደርገውን ግብ አትሌቲኮ ቢልባዎ ላይ አስቆጥሯል ። ሪያል ማድሪድ የካሪም ቤንዜማ የ14 ዓመታት አገልግሎት ማብቃቱን ትናንት ቤርናቤዎ ውስጥ ይፋ አድርጓል ። ካሪም ቤንዜማ ምናልባትም ወደ ሣዑዲ ዓረቢያ ሊያቀና እንደሚችልም ተዘግቧል ። ካሪም ቤንዜማን ለመተካት ደግሞ የቶትንሀም ሆትስፐር አጥቂ ሔሪ ኬን ወደ ሪያል ማድሪድ ይጓዛል ተብሏል ። በነገራችን ላይ ከካሪም ቤንዜማ በተጨማሪ፦ ኤደን ሐዛርድ፣ ማርኮ አሴንሲዮ እና ማሪያኖ ዲያዝም ከሪያል ማድሪድ ለቅቀው ይሄዳሉ ተብሏል ። ሪያል ማድሪድ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ጁድ ቤሊንግሀምን ለማስመጣት ከጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር በመደራደር ላይ መሆኑ ተነግሯል ።

ስዊድናዊ አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ጫማውን ሰቀለ
ስዊድናዊ አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ጫማውን ሰቀለምስል Antonio Calanni/AP Photo/picture alliance/dpa

እስከ 41 ዓመቱ ድረስ በዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ተሳታፊ የነበረው ስዊድናዊ አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ደግሞ ጫማውን መስቀሉ ተዘግቧል ። ዝላታን ኢብራሒሞቪችም በዘመኑ ለፓሪ ሳን ጃርሞ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እንዲሁም በጣሊያን ቡድኖች በኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን 511 ግቦችን አስቆጥሯል ። በአራት ሃገራትም የሊግ ውድድሮች ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል ። ትናንት ሳን ሲሮ ስታዲየም ውስጥ የጨዋታ ዘመኑ የመጨረሻ ግጥሚያን ለመከታተል ተሰባስበው ለነበሩ ደጋፊዎቹ፦ «እግር ኳስን ተሰናብቻለሁ፤ እናንተን ግን አይደለም»ብሏል። በመጨረሻ ጨዋታው ቡድኑ ኤሲ ሚላን በኦሊቨር ጂሩ እና በራፋኤል ሌኣዎ ሁለት ግቦች ቬሮናን 3 ለ1 አሸንፏል ።

በሴቶች የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ውድድር ባርሴሎና የጀርመን ቮልፍስቡርግን ድል አድርጎ ዋንጫውን ወስዷል ።  ብርቱ ፉክክር በታየበት የቅዳሜ ዕለቱ የፍጻሜ ግጥሚያ ባርሴሎና ያሸነፈው 3 ለ2 በሆነ ውጤት ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ