1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 1 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 1 2015

ዘንድሮ አልጀሪያ በምታስተናግደው የአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮን (CHAN) ግጥሚያ ተፎካካሪ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በምድብ «ሀ» ከሞዛምቢክ፤ አልጀሪያ እና ሊቢያ ጋር ከቀናት በኋላ ይጋጠማል። በስፔን አገር አቋራጭ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰሎሞን ባረጋ አሸናፊ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4LtgZ
CHAN qualification game in Mekele Äthiopien
ምስል DW/M. Haileselassie

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ከዐራት ቀናት በኋላ አልጀሪያ ውስጥ በሚጀምረው የቻን የአፍሪቃ እግር ኳስ ግጥሚያ ተፎካካሪ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዛሬ ከሞሮኮ አቻው ጋር ሁለተኛ የወዳጅነት ግጥሚያውን ያከናውኗል። ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ግጥሚያው ቅዳሜ ዕለት በሞሮኮ 1 ለ0 ተሸንፏል። በስፔን አገር አቋራጭ የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰሎሞን ባረጋ አሸናፊ ሆኗል። የኤርትራዋ ሯጭ ራሄል ዳንኤልም የአንደኛ ደረጃን አግኝታለች። በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የሦስተኛ ዙር ፉክክር ማንቸስተር ሲቲ ቸልሲን ጉድ ሲያደርግ ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ከሚገኝ ቡድን ጋር ተጋጥሞ በመከራ አቻ ወጥቷል። አርሰናል በእንግሊዝ ሦስተኛ ሊግ ውስጥ ከሚገኘው ኦክስፎርድ ዩናይትድ ቡድን ጋር ዛሬ ማታ በኤፍ ኤ ካፕ ይጋጠማል። 

አትሌቲክስ፦

London Olympische Ringe im Park von Stratford
የኦሎምፒክ ምልክት ጎሕ ሲቀድ አካባቢ ይታያል፤ ከስሩ አንድ ሰው ቆሟልምስል Getty Images/J. Setterfield

የኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር ባለድሉ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰሎሞን ባረጋ በስፔን ኤልሆይባር የ10,8 ኪሎ ሜትር የአገር አቋራጭ ውድድር አሸናፊ ሆነ። በትናንቱ የኤልሆይባር 7,6 ኪሎ ሜትር የሴቶች ፉክክር ደግሞ የኤርትራዋ ሯጭ ራሄል ዳንኤል የአንደኛነት ደረጃን አግኝታለች። አትሌት ሰለሞን በአንደኛነት አሸናፊ ለመሆን የፈጀበት 33 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ ነው። ለባሕሬን ተሰልፎ የሚሮጠው ብርሃኑ ባለው 33 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል። የስፔኑ አደል ሜካል ብርሃኑን ከ12 ሰከንዶች በኋላ ተከትሎ በመግባት የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል። በሴቶች የ7,6 ኪሎ ሜትር ርቀት ፉክክር የኤርትራዋ ሯጭ ራሄል ዳንኤል 1ኛ ደረጃ ያገኘችው 25 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በመሮጥ ነው። ኬኒያዊቷ ኤዲናህ ጄቢቶክ 25 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ሮጣ የሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። የብሪታንያዋ ሯጭ ዊንፍሬድ ያቪ በኤዲናህ በ7 ሰከንዶች ተበልጣ ሦስተኛ ወጥታለች። በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ማኅሌት ሙሉጌታ 7ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።  

እግር ኳስ

ለቻን እግር ኳስ ውድድር ዝግጅት ለማድረግ ወደ ሞሮኮ ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራባት በሚገኘው መሐመድ 6ኛ አካዳሚ ውስጥ ዛሬ 12፡00 ላይ ከሞሮኮ አቻው ጋር ሁለተኛ የወዳጅነት ግጥሚያውን አከናውኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ ዕለት ከዚሁ የሞሮኮ አቻው ጋር ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ 1-0 ተሸንፏል።

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጋጠመው የዓለም ዋንጫ ላይ ካየነው የሞሮኮ ቡድን ጋር አይደለም። በዓለም ዋንጫ አስደማሚ ግጥሚያ አድርጎ ዓለምን ጉድ ያሰኘው ቡድን ሙሉ ለሙሉ የተዋቀረው በዋናነት አውሮጳ ውስጥ በሚገኙ ታዋቂ ቡድኖች በሚሰለፉ ተጨዋቾች ነው። ይህ የኢትዮጵያ ቡድን የተጋጠመው ቡድን ለቻን ውድድር የሚዘጋጅ ነው። የአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮን (CHAN) ውድድር ደግሞ ለሀገር ውስጥ ቡድኖች ብቻ የሚሰለፉ ተጨዋቾች የሚሳተፉበት ነው። ለውጭ ሀገር ቡድን የሚሰለፍ ተጨዋች በዚህ ውድድር መሳተፍ አይችልም። እንዲያም ሆኖ ግን የሞሮኮ ቡድን በቻን ፉክክርም ጠንካራው የሚባል ነው። ባለፈው የቻን ግጥሚያ ሞሮኮ ማሊን 2 ለ0 ድል አድርጋ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫ በመውሰድ ብቸኛዋ ሀገር መሆን ችላለች። በ2018ም ድሉ የሞሮኮ ነበር።  

Kamerun Limbe | Africa Cup of Nations | Limbe Stadium
የአፍሪቃ ሃገራት ሻምፒዮን (CHAN) የካሜሩን ሊምቤ ስታዲየምምስል BackpagePix/empics/picture alliance

የዘንድሮውን የቻን ውድድር የምታዘጋጀው አልጀሪያ ናት። ውድድሩ የፊታችን ዐርብ ጥር 5 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከሦስት ሳምንታት ፉክክር በኋላ ቅዳሜ ጥር 27 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል። በውድድሩ 18 ቡድኖች ሲገኙ በአምስት ምድቦች ተደልድለዋል። ሁለት ምድቦች ሦስት ሦስት ቡድኖችን አካተዋል። በቀሪዎቹ ሦስቱ ምድቦች ውስጥ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በእያንዳንዳቸው አራት ቡድኖች ይገኛሉ።

በምድብ «ሀ» የሚገኙት ዋሊያዎቹ የፊታችን ቅዳሜ ከሞዛምቢክ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አልጀርስ ከተማ ባራኪ ስታዲየም ውስጥ ያከናውናሉ። ከዚያም ከሦስት ቀናት በኋላ ማክሰኞ ጥር 9 በተመሳሳይ ሜዳ ከአስተናጋጇ አልጀሪያ ጋር ይጋጠማሉ። ጥር 13 ደግሞ በምድቡ ከምትገኘው ሊቢያ ጋር አናባ ከተማ ውስጥ ይጫወታሉ።  

በምድብ «ለ» አይቮሪኮስት፤ ሴኔጋል፤ ዴሞክራሲያዊ ኮንጎ እና ኡጋንዳ ተደልድለዋል። በምድብ «ሐ» ሞሮኮ፤ ጋና፤ ሱዳን እና ማዳጋስካር ይገኛሉ። በምድብ «መ» ማሊ፤ አንጎላ እና ሞሪታንያ ይጋጠማሉ። ምድብ «ሠ» ካሜሩን፤ ኮንጎ እና ኒጀርን አካቷል።

ኤፍ ኤ ካፕ

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የሦስተኛ ዙር ፉክክር ኦክስፎር ዩናይትድ ዛሬ ማታ ከለንደን ጠንካራ ቡድን ይጠብቀዋል። በፕሬሚየር ሊጉ የአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናልን ዛሬ ማታ ካሳም ስታዲየም ውስጥ እንደሚያስተናግደው ኦክስፎርድ ዩናይትድ ያለ ዝቅተኛ ቡድን ገጥሞት ዐያውቅም።  በዛሬው ግጥሚያ አርሰናል ተቀያሪዎቹን ብቻ አሰልፎም ቢሆን የሚጠበቅበት ማሸነፍ እና ማሸነፍ ብቻ ነው። ምናልባትም በሰፋ የግብ ልዩነት። ምክንያቱም የአርሰናል የዛሬ ተጋጣሚው ኦክስፎርድ ዩናይትድ በሊግ አንድ ውስጥ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው። በእንግሊዝ የእግር ኳስ ሊጎች ደረጃ፦ ሊግ አንድ ወይንም ሊግ ዋን ከፕሬሚየር ሊግ እና ከእንግሊዝ ሻምፒዮንሺፕ በታች ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሊግ ነው። ኦክስፎርድ ዩናይትድ በሜዳው በደጋፊዎቹ ፊት ዛሬ ማታ አርሰናል መግጠሙ በራሱ ብቻ በቂው ይመስላል።

FA Cup - FC Chelsea v Manchester United
ኤፍ ኤ ካፕ፤ ከዓመታት በፊት ቸልሲ እና ማንቸስተር ዩናይትድን ያስተናገደው ስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየምምስል picture-alliance/dpa/Actionplus

የአርሰናል የአንድ ከተማ የለንደኑ ተቀናቃኙ ቸልሲ ትናንት በማንቸስተር ሲቲ ብርቱ ምት ገጥሞት ከውድድሩ ተሰናብቷል። ቸልሲ በኤፍ ኤ ካፕ የትናንቱ ግጥሚያ በማንቸስተር ሲቲ ኤቲሐድ ስታዲየም ውስጥ የ4 ለ0 ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካኼደው አራተኛ ዙር የኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ ማታ ከሚያሸንፈው ቡድን አንዱን ያስተናግዳል። በብዙ መልኩ ማንቸስተር ሲቲ የሚያስተናግደው አርሰናልን እንደሚሆን ይገመታል።

የኤፍ ኤ ካፕ ፉክክር ቀጥሎ የነገ ሳምንት ማክሰኞ ደግሞ ሊቨርፑል ከዎልቨርሀምፕተን ጋር የመልስ ግጥሚያውን ያካሂዳል። የሁለቱ አሸናፊ ከብራይተን ጋር በአራተኛ ዙር ይጋጠማል። ዘንድሮ በፕሬሚየር ሊጉም አቋሙ እጅግ የዋዠቀው ሊቨርፑል ባለፈው ግጥሚያ በሜዳው አንፊልድ ከዚሁ ከዎልቨርሀምፕተን ጋር ተጋጥሞ ሁለት እኩል ተለያይቷል። ዎልቨርሀምፕተን በፕሬሚየር ሊጉ ወራጅ ቀጣና 19ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

በሦስተኛ ዙር የኤፍ ኤ ካፕ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ማንቸስተር ዩናይትድ ዐርብ ዕለት ኤቨርተንን 3 ለ1 ድል አድርጓል። በበነጋታው ቅዳሜ ቶትንሀም በሊግ አንድ 13ኛ ደረጃ የሚገኘው ፖርትስማውዝን በትግል 1 ለ0 አሸንፏል።  

አጫጭር የስፖርት መረጃዎች

የጣሊያን የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን የፊት መስመር ተጨዋች ጂያንሉካ ቪያሊ በ58 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በጣፊያ ካንሰር ኅመም ዐርብ ዕለት ያለፈው ጂያንሉካ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ አውሮጳ ውስጥ ኮከብ አጥቂ ተጨዋች ነበር። የጣሊያኑ ሳምፕዶሪያ በሴሪ አው ከናፖሊ ጋር ትናንት ከነበረው ግጥሚያ በፊት እንዲሁም የእንግሊዙ ቸልሲ ከኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያው በፊት ለቀድሞ ተጨዋቻቸው ጂያንሉካ የኅሊና ጸሎት አድርገዋል። ጂያንሉካ ከሳምፕዶሪያ እና ቸልሲ በተጨማሪ ለጁቬንቱስ ቱሪንም ተሰልፎ ተጫውቷል። ከጁቬንቱስ ጋር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1996 የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ መሆን ችሏል።

Gianluca Vialli, italienischer Nationalspieler verstorben
የጣሊያን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋች ጂያሉካ ቪያሊ፤ አርፏልምስል Marco Canoniero/imago images

የቀድሞው የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድንን በአሰልጣኝነት እንዲመሩ ዛሬ መቀጠራቸው ተገለጠ። ስፔናዊው አሰልጣኝ የተኩት በዓለም ዋንጫው በሞሮኮ በሩብ ፍጻሜ የተሰናበተውን ቡድን የመሩት የቀድሞው አሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶሽን ነው። ፖርቹጋልን ስምንት ዓመት አሰልጥነው የተሰናበቱት የ68 ዓመቱ ፈርናንዶ ሳንቶሽ በተለይ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ተደጋጋሚ ቁርሾ የገቡ አሰልጣኝ ነበሩ።  አዲሱ የፖርቹጋል አሰልጣኝ በፖርቹጋል ቡድን ለ19 ዓመታት ላገለገለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተገቢውን ክብር እንሰጣለን ብለዋል።  በዓለም ዋንጫ የተሰለፉት 26 የፖርቹጋል ተጨዋቾችን ማነጋገር እንደሚፈልጉም አዲሱ አሰልጣኝ ዐሳውቀዋል። ከ26ቱ ተጨዋቾች መካከል ክርስቲያኖ ሮናልዶም ይገኛል ከእሱ ጋርም መነጋገር እፈልጋለሁ ብለዋል።  

የ49 ዓመቱ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ የቤልጂየም ቡድንን ለስድስት ዓመታት አሰልጥነዋል። ቤልጂየምን በ2018 የዓለም ዋንጫ የሦስተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ አስችለዋል። በ2020 ደግሞ በአውሮጳ እግር ኳስ ፍጻሜ ቤልጂየምን ለሩብ ፍጻሜ አብቅተው ነበር። ቤልጂየም በእሳቸው የአሰልጣኝነት ዘመን በፊፋ መስፈርት ለአራት ዓመታት ከዓለም 1ኛ ደረጃን ይዞም ቆይቷል። ከቤልጂየም ቡድን አሰልጣኝነታቸው እንደሚለቁ ያሳወቁት ከካታሩ የዓለም ዋንጫ በፊት ነበር።

Neu Bildkombo Lionel Messi und Christiano Ronaldo
ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ እስያ ውስጥ ከሰሞኑ ሊጋጠሙ ነው

ሊዮኔል ሜሲ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከሰሞኑ ሊጋጠሙ ነው። የፈረንሳዩ ፓሪስ ሳንጃርሞ ቡድን ዕንዳስታወቀው ከሆነ ከሳምንት በኋላ ከእነ ሊዮኔል ሜሲ ጋር ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ካታር ያቀናል። ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥም ከክርስቲያኖ ሮናልዶ አዲስ ቡድን ኧል ናስር ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል ተብሏል። አል ናስር ቡድን ለክርስቲያኖ ሮናልዶ ቦታ ለመስጠት የካሜሩኑ አንበሳ አጥቂ ቪንሰንት አቡባክርን አሰናብቷል። በሳዑዲ ሊግ በአንድ ቡድን ውስጥ መጫወት የሚችሉት ስምንት የውጭ ሃገራት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው። በዚህም መሠረት እንደ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ከሆነ የ30 ዓመቱ ቪንሰንት አቡበከር ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አቅንቶ ለማንቸስተር ዩናይትድ ሊሰለፍ ይችላል።

ከማንቸስተር ዩናይትድ በብርቱ ጠብ የተለየው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በበኩሉ በሳዑዲ ዓረቢያ ቆይታው በሐብት ላይ ሐብት ተጨምሮለታል። በአል ናስር ቡድን በዓመት ያገኛል ከተባለው ከ200 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ ሳዑዲ ዓረቢያ በ2030 የዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ የሚደረገውን ዘመቻ እንዲደግፍ በሚል ተጨማሪ የ200 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጠው ዛሬ ይፋ ሆኗል። በነዳጅ ሐብት የበለጸገችው ሳዑዲ ዓረቢያ ለክርስቲያቲያኖ ሮናልዶ 200 ሚሊዮን ዶላር የምትከፍለው ከግብጽ እና ከግሪክ ጋር በጋራ የዓለም ዋንጫን ለማሰናዳት ለምታደርገው ዘመቻ ለሚኖረው የአምባሰደርነት ሚና መሆኑን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ከክርስቲያኖ ሮናልዶ በተጨማሪ ሊዮኔል ሜሲም የሳዑዲ ዓረቢያ የ2030 የዓለም ዋንጫ አምባሳደር መሆኑ ይታወቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ