ምስራቅ ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ የተፈጠረው አለመረጋጋት
በምስራቅ ቦረና ሞያሌ ከተማ ትናንት ምሽት የኮንትሮባንድ ፍተሻ ላይ በነበሩ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች የ12 ዓመት ታዳጊ መገደሉን ተከትሎ የተቆጣው የአከባቢው ማህበረሰብ ዛሬ ከመንግስት የጸጥታ አካላት ጋር ግጭት ተፈጥሯል።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የሞያሌ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ አበባው ወኪላችን ስዮም ጌቱ እንደተናገሩት የችግሩን መነሻ የግጭቱ መነሻ ኮንትሮባንድ የሚፈትሹ የፌደራል ፖሊስ አባላት አንድ አዳጊ ወጣትን በመግደላቸው ነው ብለዋል።
“ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት ግድም ፌዴራል ፖሊስ ለኮንትሮባንድ ፍተሻ በሞያሌ ከተማ ሻባሬ ቀበሌ የአንድ ግለሰብ ቤት ገብተው ነበር፡፡ በፍተሻው ምንም ባያገኙም ከህዝብ ጋር ግጭት ውስጥ ገቡ፡፡ በዚያው በተፈጠረ ግብግብ ነው ከፌዴራል ፖሊስ አባላቱ በተተኮሰ ጥይት ቦሩ አዩሪ የተባለ የ12 ኣመት ታዳጊ የተገደለው”
ዛሬ ጠዋት ደግሞ የታዳጊውን ስርዓተ ቀብር ፈጽመው በመመለስ ላይ ነበሩ የአከባቢ ማህበረሰብ በብስጭት ፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን በመግለጽ ተቃውሞውም በተኩስ መበተኑን አስረድተዋል፡፡
“ትናንት ሌሊቱን በሙሉ የተኩስ ድምጽ ስንሰማ ነው ያደርነው፡፡ ዛሬ ደግሞ የታዳጊውን ስርዓተ ቀብር ፈጽመው የሚመለሱ ማህበረሰብ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ነበር፡፡ እናም ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ውጥረት ነግሶ ህዝቡ በተሰማው ተኩስ ነው የተበተነው” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ዶቼ ቬለ ስለክስተቱ ከአከባቢው ባለስልጣናት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ለፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጀኢላን አብዲ በመደወል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም ኃላፊው በጉዳዩ ላይ እስካሁን የደረሳቸው መረጃ አለመኖሩን በመግለጻቸው ለዛሬ ጥረቱ አልሰመረም፡፡
ከ4.9 እስከ 5.1 ሬክተር ስኬል የተለካው ርዕደ መሬት
ትናንት ሌሊቱን በአንድ ሰዓት ውስጥ 3 ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአውሮፓ-ሜዲትራኒያን የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከል (EMSC) አስታውቋል። ተቋሙ ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከ4.9 እስከ 5.1 ሬክተር ስኬል የተለካው ርዕደ መሬት በአንድ ሰዓት ውስጥ 3 ጊዜ መከሰቱንም ነው የገለጸው፡፡
ሌሊቱን በኢትዮጵያ አቆጣጠር 9፡20 ግድም ላይ 5.1 ሬክተር ስኬል ሆኖ ከአዋሽ በስተሰሜን ምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ላይ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀወጥ አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ ባሰማው ንዝረት በርካታ የመዲናይቱ ነዋሪዎችን ከውድቅት ሌሊቱ እንቅልፍ ቀስቅሷል፡፡
እንደ የአዋሽ 07 ከተማ ነዋሪ አስተያየት ከሰሞኑ ተቀዛቅዞ የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ ትናንት ሌሊት ከፍ ብሎ ከመሰማቱ በፊት በቅርቡ ፍልውሃን ባፈለቁ አከባቢዎች ላይ ከመሬት ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ይሰማ ነበር፡፡
“የቮልካኖ ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች መሬቱ ትንሽ ቀዝቅዟል፡፡ ግን ከመሬት ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ይሰማል” ፡፡
ትናንት ሌሊቱን የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሰሞኑ ከፍ ያለ ነው ያሉት የአፋር ክል ዞን 03 ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዶ አሊ በፊናቸው በትናንት ሌሊቱ የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰ አዲስ ውድመት እንደሌሌም አመልክተዋል፡፡
“እንዳያችሁት ማታ 5.2 ድረስ የተመዘገበ ርዕደ መሬት ተከስቷል፡፡ ግን እንዳዲስ ደረሰው ጉዳት የለም”
ይሁንና ዋና አስተዳዳሪው ከዚህ በፊት ተደጋግሞ በዞኑ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ መሰረተ-ልማቶች፣ ተቋማት እና የግለሰቦች ንብረቶች
ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ከተባሉ ከዞኑ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የስጋት ቀጠና ተብለው ከተለዩት ቀበሌያት ወደ አስር ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸውንም አመልክተው፤ ዜጎችን ከአከባቢው የማራቅ ተግባር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባዘግቧል።
በናይጄርያ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 21 የመንግስት ወታደሮች መገደላቸውን
በናይጄርያ «ወሮበሎች» በተባሉ ታጣቂዎች በተፈጸመ የደፈጣ ጥቃት 21 የመንግስት ወታደሮች መገደላቸውን የሃገሪቱ የፖሊስ ባለስልጣናት አስታወቁ። ወታደሮቹ በሌላ ጥቃት የሞቱ ጓሮቻቸው ቤተሰቡች ለቅሶ ደርሰው ሲመለሱ እንደሆነም ታውቋል።
በደቡብ ምዕራብ ናይጄርያ በምትገኘው ሳፋና ወረዳ ካስቲና የተባለች መንደር የፖሊስ ቃልአቀባይ አቡበከር ሳዲቅ አሊዩ «ወንጀለኞቹን ለመያዝ ፖሊስ አስፈላጊውን ስምሪት እያካሄደ ነው» ብለዋል። አካባቢው በርካታ የታጠቁ ሃይሎች የሚንቀሳቀሱበት ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ ለተፈጸሙ የተማሪዎች ዕገታም ተጠያቂዎች እንደሆኑ ቃልአቀባዩ ተናግረዋል። በአካባቢው በታጣቂዎች ግድያን ጨምሮ የቤት ለቤት ዝርፊያም እንደሚፈጸም የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
በጋዛ 32 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን
በአለፉት 24 ሰዓታት እስራኤል በተለያዩ የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች በፈጸመችው ጥቃት 32 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በጥቃቱ 54 ሰዎችም ቆስለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እንዳለው በጋዛ እየተፈጸሙ ባሉ ጥቃቶች አሁንም በፍርስራሾች የተቀበሩ ሬሳዎችን ማውጣት አልተቻለም። የሕክምና ተቋማትም በጥቃቶች ስለወደሙ የቆሰሉትን ለመርዳት አዳጋች አድርጎታል ነው የተባለው።
እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 7 ቀን 2023 በእስራኡልና ሐማስ መካከል ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሞቱ ፍልስጤማውያን ቁጥር 46,537 ሲደርስ የቆሰሉት ደግሞ ወደ 109,600 ተጠግቷል።
የአሜሪካ ልዮ ልዑክ በዶሃ
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በአደራዳሪነት እየተንቀሳቀሰች ያለችው ቀጠር የአሜሪካው ተመራጭ ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛ ምስራቅ ልዩ ልዑክ ተቀብላ አነጋገረች። የቃጠር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባሰራጨው መግለጫ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ከቀጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ሸክ መሐመድ ቢን አብዱል ራሕማን ቢን ጃሲም ጋር በዶሃ ተነጋግረዋል።
የአሜሪካው ተሰናባች ፕረዚደንት ጆ ባይደን ባአለፈው ሐሙስ ግብጽ፣ አሜሪካና ቀጠር በጋራ የሚያካሂዱት የጋዛ የሰላም ውይይት «እውነተኛ ዕድገት ማሳየት አለበት» ብለዋል። ሀማስ ታጋች እስራኤላውያን ባለመልቀቁ በመውቀስ።
ለተኩስ አቁም ስምምነቱ አለመደረስ አንዱ ሌላኛውን ሲወቅስ ይደመጣል። የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው እስራኤል የተኩስ አቁም ውይይቱ የጆ ባይዳን የስልጣን ጊዜ ከተገባደደ በኋላ በዶናልድ ትራምፕ የስልጣን ጊዜ እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳላት ይገልጻሉ።
አሸማጋይዋ ቀጠር ሐማስ የታገቱ እስራኤላውያን እንዲለቅ ተጨማሪ ግፊት እያደረገች እንደምትገንም ዜናው አክሏል።
የዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛ ምስራቅ ልዩ ልዑክ ከቀጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ስላደረጉት ውይይት ግን የተሰጠ ዝርዝር መረጃ እንደሌለ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የጀርመን ፓርቲዎች ውዝግብ
የጀርመን ክርስትያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ CDUን ወክለው እጩ የመራሔ መንግስት ተወዳዳሪ የሆኑት ፍሬደሪሽ ማርትዝ ከቀኝ አክራሪው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ በትብብር እንደማይሰሩ አስታወቁ። ማርትዝ ፓርቲውን ዘረኛና ጸረ ሰሜቲክ ሲሉ ወርፈውታል።
ዕጩ ተወዳዳሪው «በኔ የስልጣን ዘመን ከAFD ጋር ምንም አይነት ትብብር አይኖርም» ሲሉ ተደምጠዋል። ማርትዝ አያይዘውም «ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ጽንፈኛና አገራችንን ከአውሮፓ ሕብረትና ከሰሜን ጦር ቃልኪዳን NATO እንድትወጣ ከሚፈልግ ፓርቲ ጋር መስራት አንፈልግም» ሲሉ አክለዋል።
የጀርመን ሕገመንግስትን የሚታደግ በጀርመንኛ ምህጻሩ GDIS የተባለ ተቋም፤ አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ የሚጠረጠርበትን የጽንፈኝነትና ቀኝ አክራሪነት ጉዳይ እየተከታተለው መሆኑን ገልጿል።
ፓርቲው ከዚህ ቀደም የናዚ መፈክሮችን በማሰማት ሁለት ጊዜ ተከሶ ፍርድቤት ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል። በያዝነው የጎርጎሪሮሳውያኑ ዓመት በየካቲት ወር በሚካሄደው የጀርመን ፌደራል ምርጫ መጤ ጠል የሚባለው AFD አብላጫ ድምጽ አግኝቶ እንዳያሸንፍ ተሰግቷል። ዘገባው የጀርመን ዜና አገልግሎት ነው።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ