የጥር 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥር 5 2017ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዱባይ ማራቶን በወንድም በሴትም ፉክክር በበላይነት አጠናቀዋል ። በወንዶች እስከ 14ኛ በሴቶች ደግሞ እስከ 16ኛ ደረጃ ድረስ ከኢትዮጵያውያን ውጪ ማንም ጣልቃ አልገባም ። በሳምንቱ መጨረሺያ በተከናወነው የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ እግር ኳስ ግጥሚያ በሜዳው ማንቸስተር ዩናይትድን አስተናግዶ አቻ የወጣው አርሰናል በፍጹም ቅጣት ምት መለያ ተሸንፏል ። ማንቸስተር ሲቲ፣ ቸልሲ እና ሊቨርፑል ተጋጣሚዎቻቸውን የግብ ጎተራ አድርገዋል ። በቡንደስሊጋው ላይፕትሲሽ በግብ ሲንበሸበሽ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽንፈት ገጥሞታል ። ባዬርን ሙይንሽን እና ባዬርን ሌቨርኩሰን ድል ከቀናቸው መካከል ናቸው ።
አትሌቲክስ
ዱባይ ውስጥ ትናንት (ጥር 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) በተካሄደው የ2025 የማራቶን ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም አስደናቂ ድል አስመዘገቡ። በወንዶች ፉክክር ኢትዮፕያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 14ኛ ተከታትለው በመግባት በበላይነት አጠናቀዋል ። በሴቶች ደግሞ ኢትዮፕያውያቱ ከአንደኛ እስከ ዐሥራ ስድስተኛ ድረስ ማንምም ጣልቃ አላስገቡም ። በሁለቱም ውድድሮች አሸናፊ ለሆኑት አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ80,000 የዩኤስ ዶላር መሰጠቱን ገልፍ ኒውስ በድረ ገጹ ዘግቧል ። በወንዶች ፉክክር ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጪ ኬኒያዊው አትሌት ዴኒስ ኪሜቶ 15ኛ ደረጃ አግኝቷል ። የ41 ዓመቱ ኬኒያዊ አትሌት የቀድሞ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ነበር ።
በወንዶች ፉክክር አትሌት ቡቴ ገመቹ ያሸነፈው 2:04:51 በመሮጥ ነው ። ብርሃኑ ጸጉ በቡቴ በ23 ሰከንዶች ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል። ሽፈራው ታምሩ 2:05:28 በመሮጥ ሦስተኛ ወጥቷል ። አትሌት ደሳለን ግርማ፣ ደጀኔ ኃይሉ፤ ጌታቸው ማስረሻ፣ ታደለ ደምሴ፣ ቦኪ ድሪባ፣ እምባዕ ጎይቶም እና ይስማው አጥናፉ እስከ ዐሥረኛ ተከታትለው ገብተዋል ።
በሴቶች ምድብ፦ ከአንደኛ እስከ ዐሥረኛ ደረጃ ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ተከታትለው በገቡበት ተመሳሳይ ፉክክር አትሌት በዳቱ ሒርጳ 2:18:27 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች ። ደራ ዲዳ ከበዳቱ ለጥቂት በአምስት ሰከንድ ብቻ ተበልጣ ሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ትእግስት ግርማ ደግሞ ከአሸናፊዋ ሁለት ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ተበልጣ የሦስተኛ ደረጃ ይዛለች ። ከአራተኛ እስከ ዐሥረኛ ደረጃ በቅደም ተከተል፦ ዘይነባ ይመር፣ ብርቱካን ወልዴ፣ ኩፍቱ ያሂር፣ ጋዲሴ ሙሉ፣ አልማዝ ከበደ፣ ከበቡሽ ይስማ እና ዲባቤ በየነ ናቸው ። 17, 000 ተወዳዳሪዎች በተሳተፉበት የዱባይ ማራቶን ለአሸናፊዎች በአጠቃላይ 504 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ተበርክቷል ። የታኅሣሥ 28 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
የብስክሌት ግልቢያ ፉክክር
በድሬዳዋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው አገር አቀፍ የብስክሌት ግልቢያ ፉክክር ትናንት ተጠናቋል ። ከታኅሣሥ 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ውድድር ላይ 36 ብስክሌተኞች ተሳታፊ እንደነበሩ ተዘግቧል ። ተፎካካሪዎቹ ውድድሩ ከተካሄደበት ከዛው ድሬዳዋ ከተማ፤ ከአዲስ አበባ፣ከትግራይ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተውጣጡ ነበሩ ። በ80 ኪሎ ሜትር የፍጻሜ ውድድር ዐቢይ ዓለም ከወልዋሎ አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ አሸናፊ መሆኑን የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ዐሳውቋል ። በቡድን የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ወልዋሎ አዲስ መድኃኒት ፋብሪካ መሆኑ ተዘግቧል ። ድሬዳዋ ከተማ እና ቶቶ የብስክሌት ቡድኖች2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸውም ታውቋል ።
እግር ኳስ
በእንግሊዝ ኤፍ ኤካፕ ሦስተኛ ዙር ፉክክር ትናንት በሜዳው ኤሚሬተስ ስታዲየም ማንቸስተር ዩናይትድን ያስተናገደው አርሰናል በፍጹም ቅጣት ምት መለያ ተሸነፈ ። ቀዳሚውን ግብ በብሩኖ ፈርናንዴሽ 52ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ማንቸስተር ዩናይትድ ነበር ። ፈርናንዴሽ ቀደም ብሎ ፍጹም ቅጣት ምት አቅራቢያ ተጠልፎ ሲወድቅ ቅጣት ምት ባለመሰጠቱ እጅግ ተበሳጭቶም ነበር ። ብስጭቱ በግቧ ወዲያው ነበር የተካካሰው ። ሆኖም በ61ኛው ደቂቃላ ላይ ዲዮጎ ዳሎት በፈጸመው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱ ጎድቶታል ። ወዲያውኑም ነበር በ63ኛው ደቂቃ ላይ በጋብሪዬል ማጋልሄስ አቻ የምታደርገው ግብ የተቆጠረበት ። ፍጹም ቅጣት ምትን ጨምሮ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን የማንቸስተር ዩናይትድ ቱርካዊው ግብ ጠባቂ አልታይ ባዪንዲር በማጨናገፍ የምሽቱ ኮከብ ሁኖ ወጥቷል ። መደበኛ ጨዋታው አንድ እኩል በመጠናቀቁ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት መለያ ነበር የተሻገሩት ። የታኅሣሥ 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በፍጹም ቅጣት ምት መለያው በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ማንቸስተር ዩናይትድ 5 ለ3 በማሸነፍ ወደ አራተኛው ዙር ማለፍ ችሏል ። በዚህ ውድድር ፍጽም ቅጣት ምት የሳተው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው ካይ ሐቫርትስ ባለቤት ላይ በበይነ-መረብ በርካት ማስፈራሪያዎች እና መጥፎ ምኞቶች ተንጸባርቀዋል ። ከዛቻ እና ማስፈራሪያው ባሻገር ነፍጠ-ጡሯ የካይ ሐቫርትስ ባለቤት ጽንስ እንዲጨነግፍ መጥፎ ምኞታቸውን ጭምር የገለጡ ሰዎች እንደነበሩ የካይ ሓቫርትስ ባለቤት ሶፊያ ሓቫርትስ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሯ ይፋ አድርጋለች ። ካይ ሓቫርትስ መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃ ግድም ሲቀረውም ግብ ሊሆን የሚችል ኳስ አጨናግፏል ።
የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በዐሥር ተጨዋቾች የተወሰነው ማንቸስተር ዩናይትድን ቡድናቸው አለማሸነፉ አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ተናግረዋል ። በተለይ በመጨረሻዎቹ የጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች የበላይነቱ የጎላው አርሰናል በርካታ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶች መክነውበታል። የኅዳር 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ቶትንሀም ከፕሬሚየር ሊጉ ውጪ ያለውን ታምዎርዝ ቡድን በኤፍ ኤካፕ ትናንት 3 ለ0 ለማሸነፈ ከመደበኛ 90 ደቂቃው ባሻገር የጭማሪ ሰአት አስፈልጎት ነበር ። ኒውካስል ብሮምሌይን ትናንት 3 ለ1 አሸንፏል ። ቅዳሜ ዕለት የነበሩ በርካታ የኤፍ ኤካፕ ግጥሚያዎች ደግሞ ቡድኖች በግብ የተንበሸበሹበት ነበር ። ማንቸስተር ሲቲ ሳልፎርድ ሲቲን 8 ለ0 ሸንቷል ። ኪው ፒ አር በላይስተር ሲቲ የ6 ለ2 ሽንፈት ገጥሞታል። ቸልሲ ሞርካምቤን 5 ለ0 ሲያሸንፍ፤ በርመስ ዌስትብሮሚችን 5 ለ1 ድል አድርጓል ። ሊቨርፑል አክሪንግተንን 4 ለ0 አሸንፏል ።
በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት ላይፕትሲሽ ቬርደር ብሬመንን 4 ለ2 አሸንፏል ። አውግስቡርግ በሜዳው በሽቱትጋርት የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። ቅዳሜ ዕለት መሪው ባዬር ሙይንሽን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 1 ለ0 አሸንፏል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሳንክት ፓውሊን 1 ለ0 አሸንፏል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሜዳው ሲግናል ኢዱና ፓርክ በባዬር ሌቨርኩሰን የ3 ለ2 ሽንፈት አስተናግዷል ። የደረጃ ሰንጠረዡን ባዬርን ሙይንሽን በ39 ነጥብ ይመራል ። ባዬር ሌቨርኩሰን በ35 ይከተላል፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርት እና ላይፕትሲሽ በተመሳሳይ 30 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሦተኛ እና አራተና ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። ሐይደንሀይም፣ ሆልሽታይን ኪዬል እና ቦሁም ከ16ና እስከ 18ኛ ወራጅ ቀጣና ጠርዝ እና ውስጥ ይገኛሉ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ