1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 23 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 23 2013

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ኤቨርተን የመሪነቱን ሥፍራ ለሊቨርፑል አስረክቧል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ሻልከ ከረዥም ጊዜ በኋላ ያገኘውን የማሸነፍ እድል አምክኖ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ይገኛል። ከኮሮና ያገገመው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በጣሊያን ሴሪ ኣ ኹለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

https://p.dw.com/p/3kmGD
Fußball Bundesliga Mönchengladbach - RB Leipzig
ምስል Sascha Steinbach/Pool/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ኤቨርተን የመሪነቱን ሥፍራ ለሊቨርፑል አስረክቧል። አርሰናል ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ የተቀዳጀው ድል ለአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ልዩ ትርጉም አለው። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ በደረጃ ሠንጠረዡ በግብ ክፍያ ብቻ ነው የሚለያዩት። ሻልከ ከረዥም ጊዜ በኋላ ያገኘውን የማሸነፍ እድል አምክኖ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ይገኛል። ከኮሮና ያገገመው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በጣሊያን ሴሪ ኣ ኹለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

አትሌቲክስ

ቀድሞ የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማኅበር (IAAF) በመባል የሚታወቀው የዓለም አትሌቲክስ በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ላይ ባደረገው ምርጫ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ «የወሩ ክስተት» የተባለውን ሽልማትን አሸነፈች። የዓለም አትሌቲክስ በይፋዊ የትዊተር መገናኛ አውታር ገጹ ላይ ያሰፈረው የትዊተር ተጠቃሚዎች ድምፅ አሰጣጥ ሒደት ለ24 ሰአታት የቆየ ነበር። ውድድሩም፦ በዓለም አትሌቲክስ የትዊተር ገጽ ላይ የእጩ ተወዳዳሪ አትሌቶች ምስል ያለበት እና «የወሩ ክስተት እጩ» የሚል ጽሑፍ የሰፈረበትን የትዊተር መልእክት የትዊተር ተጠቃሚዎች ወደ ራሳቸው ገጽ እንዲወስዱ የሚጋብዝ ነበር። በርካታ ሰዎች የትዊተር መልእክቱን ለወዳጆቻቸው ያጋሩት የፎቶ መልእክትም አሸናፊ ኾኗል።

Leichtathletik-Meeting in Valencia I Weltrekord 50000 I Letensebet Gidey
ምስል Manuel Bruque/Agencia EFE/Imago Images

አትሌት ለተሰንበት ግደይ ከኬንያዊቷ አትሌት ከፔሬስ ጄፕቺርቺር እንዲሁም ከኡጋንዳውያኑ ከእነ ጆሹዋ ቼፕቴጌ እና ጃኮብ ኪፕሊሞ የበለጠ በርካታ የትዊተር ተጠቃሚዎች መርጠዋት ነው አንደኛ ኾና ያሸነፈችው። የአትሌት ለተሰንበት ግደይ ምስል ያለበትን እጩ መወዳደሪያ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ወደ ራሳቸው ትዊተር ወስደው ለጥፈውታል። በዚህም ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘች አትሌት ኾና ተመርጣለች። ኹለተኛ የወጣው ጆሹዋ ቼፕቴጌ ምስል ያለበትን የትዊተር መልእክት ኹለት ሺህ ሰባት መቶ የትዊተር ተጠቃሚዎች ወደ ራሳቸው የትዊተር ገጽ ወስደው ለጥፈውታል።

አትሌት ለተሰንበት በጥሩነሽ ዲባባ ለ12 ዓመታት ተይዞ የቆየውን የ5,000 ሜትር የሩጫ ውድድር ክብረ ወሰን ስፔን ቫሌንሺያ ውስጥ በተደረገው ፉክክር ከአራት ሰከንዶች በላይ ማሻሻል የቻለች ድንቅ አትሌት ናት።

የቡንደስ ሊጋ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነው የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ ባየር ሌቨርኩሰን ፍራይቡርግን 4 ለ2 አሸንፎ የአራተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። ትናንት በተደረገ ሌላ ግጥሚያ ቮልፍስቡርግ ከሔርታ ቤርሊን ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል። ቅዳሜ እለት ላይፕሲሽ በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የ1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ አርሜኒያ ቢሌፌልድን 2 ለ0 አሸንፏል።

ባየር ሙይንሽን ኮልን 2 ለ1 ሲያሸንፍ ማይንትስ በአውግስቡርግ 3 ለ1 ተሸንፏል። ቬርደር ብሬመን ከአይትራኅት ፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል።

Bundesliga Freiburg gegen Leverkusen
ምስል Alex Grimm/Getty Images

ሽቱትጋርት እና ሻልከም አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። በተለይ ቬልቲንስ አሬና ውስጥ 1 ለዜሮ ሲመራ የቆየው ሻልከ ከረዥም ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኋላ በድንገት የተገኘ የማሸነፍ እድሉን ነው ያመከነው።

ባየር ሙይንሽን 15 የግብ ክፍያ ይዞ የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራል። ተመሳሳይ 15 ነጥብ ያለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 11 የግብ ክፍያ አለው፤ ኹለተኛ ደረጃ ላይገኛል። ላይፕሲሽ 13 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ባየር ሌቨርኩሰን በ12 ነጥብ ይከተለዋል።

ኹለት ነጥብ ብቻ የያዙት ኮልን እና ሻልከ በወራጅ ቃጣናው ግርጌ እና ውስጥ 16ኛ እና 17 ደረጃ ላይ ናቸው። ማይንትስ በ13 የግብ እዳ እና በዜሮ ነጥብ የመጨረሻ 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ፕሬሚየር ሊግ

አርሰናል ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው ገጥሞ 1 ለ0 ማሸነፉ ለቡድኑ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል።  በፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግ 68ኛ ደቂቃ ብቸኛ ግብ 3 ነጥብ ይዞ መውጣት ለቻለው አርሰናል የትናንቱ ውጤት ልዩ ነበር።  አርሰናል ከ14 ዓመታት ወዲህም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ገጥሞ ድል ሲያደርገው። ይኽ ድል ለአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በልዩ ኹኔታ የሚታየውም ለእዚህ ነው።  

ፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግ 13ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊኾን የሚችል ዕድል ነበር ያመለጠው። ከላይፕሲሽ ጋር በሻምፒዮንስ ሊግ ተጋጥሞ 5 ለ 0 ድል ያደረገው ማንቸስተር ዩናይትድ ለአርሰናል እጅ ሰጥቷል።  

Bildkombo Fußball England | Sadio Mane Liverpool | Aubameyang  Arsenal

አርሰናል ትናንት 21ኛው ደቂቃ ላይ በግሪንውድ የግብ ሙከራ ቢያደርግም በግብ ጠባቂው ቤርንት ሌኖ በቀላሉ ተጨናግፏል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግ እና ዊሊያምስ ተቀባብለው ዊሊያምስ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት የግቡን ማእዘን ገጭቶ ነበር የወጣው። በቀኝ በኩል ዊሊያምስ ጠንካራ ኾኖ ነበር። 68ኛው ደቂቃ ላይ ፖግባ ላይ በተፈጸመው ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ፒዬር ኤመሪክ አውባሜያንግ ከመረብ አሳርፎ በዚሁ አርሰናል አሸናፊ መኾን ችሏል።

አርሰናል 12 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ ላይ ይገኛል። ተመሳሳይ ነጥብ ያለው ላይስተር ሲቲ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኾኖም ዛሬ ማታ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር በሚያደገው ተስተካካይ ጨዋታው ካሸነፈ እንደውም ኹተኛ ደረጃን መያዝ ይችላል። ሊቨርፑል ዌስትሀምን ቅዳሜ ዕለት 2 ለ 1 በመርታት የመሪነት ስፍራውን ከኤቨርተን ተረክቧል።

ኤቨርተን ከኒውካስል ጋር ባደረገው ግጥሚያ ቅዳሜ ዕለት 2 ለ1 በመሸነፉ 14 ነጥቡን እንደያዘ ወደ ኹለተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። ላይስተር ሲቲ ዛሬ ማታ ካሸነፈ 15 ነጥብ ስለሚኖረው የኹለተኛ ደረጃውንም ለመልቀቅ ይገደድ ይኾናል። ፉልሃም ከዌስት ብሮሚች ጋርም ዛሬ ማታ ተስተካካይ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። 12 ነጥብ ያለው ቸልሲ ደረጃው 6ኛ ነው።  ማንቸስተር ዩናይትድ 7 ነጥብ ይዞ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ማንቸስተር ሲቲ 11 ነጥብ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል።

የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ሰርጂዮ አጉዌሮ ከጉዳቱ ባለማገገሙ በዚህ ሳምንት ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ለሚኖረው ወሳኝ ግጥሚያ መሰለፍ አይችልም። ይህንንም አሰልጣን ፔፕ ጓርዲዮላ ዛሬ ተናግረዋል።  መሪው ሊቨርፑል እሁድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ከመጋጠሙ በፊት በነገው እለት ለሻምፒዮንስ ሊግ ከአታላንታ ጋት ይጫወታል። ምናልባትም የነገው ጨዋታ በእሁድ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያ ላይ ለሊቨርፑል ተጽእኖ ሊፈጥርም ይችል ይኾናል።

Champions League |  Liverpool FC v FC Midtjylland
ምስል Phil Noble/Getty Images

በነገው የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ፦ ባየር ሙይንሽን ከዛልስቡርግ ጋር ይጫወታል። ዳቪድ አላባ ከባየር ሙይንሽን ሊለቅ መኾኑም ተነግሯል። ሪያል ማድሪድ ከኢንተር ሚላን ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቅ ነው። የሪያል ማድሪዱ አሰልጣን ዚነዲን ዚዳን፦ የነገው ግጥሚያ እንደ ፍጻሜው ውድድር የምናየው ነው ብሏል። ሪያል ማድሪድ በምድብ ለ ውስጥ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

የሊቨርፑል ጆዬል ማቲፕ እና ናቢ ኪዬታ ከቡድናቸው ጋር የመጀመሪያ ልምምዳቸውን አድርገዋል። አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ፦ ከጣሊያኑ አታላንታ ጋር በሚኖራቸው ግጥሚያ ማንን እንደሚያሰልፉ ግራ የተጋቡ ይመስላል። ልምምድ ባያደርግም ቲያጎ አልካታራም ከቡድኑ ጋር ወደ ተጓዥ መኾኑ ተገልጧል። ማን ዋና ተሰላፊ እንደሚኾን በስተመጨረሻ እንደሚነገር ዬርገን ክሎፕ ዐሳውቀዋል።

አትሌቲኮ ማድሪድ ከሎኮሞቲቭ ሞስኮ፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከሻካታር ዶኒዬትስክ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከኦሎምፒያኮስ፤ ፖርቶ ከማርሴ፣ አያክስ አምስተርዳም ከሚድቺላንድ የሚጋጠሙት በነገው ዕለት ነው። ረቡዕም በርካታ ግጥሚያዎች አሉ።

ሴሪ ኣ

ለሁለት ሳምንታት በኮሮና ምክንያት መሰለፍ ባይችልም ከተቀያሪ ወንበር ላይ ተነስቶ በኹለተኛው አጋማሽ ወደ ሜዳ የገባው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሁለት ግቦችን ለጁቬንቱስ ማስቆጠር ችሏል።  የ35 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ በኮሮና የተነሳ አራት ግጥሚያዎች ላይ መሳተፍ አልቻለም ነበር። በትናንቱ ግጥሚያም አሰልጣኝ አንድሬ ፒርሎ ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ተቀያሪ አድርጎት ነበር።

Fußball UEFA Champions League Ajax Amsterdam - Juventus FC
ምስል Imago Images/Beautiful Sports

በጨዋታው የኹለተኛ አጋማሽ 56ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ግን ክሪስቲያo ሮናልዶ ሦስት ደቂቃ በላይም አልቆየ ጁቬንቱስን 2 ለ1 መሪ እንዲኾን ለማስቻል። ቀዳሚዋን ግብ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ለጁቬንቱስ ያስቆጠረው አልቫሮ ሞራታ ነበር።  ሮናልዶ በ59ኛው ደቂቃ ላይ አግብቶ ጁቬንቱስ መሪ እስኪኾን ድረስም ቶማሶ ፖቤጋ በ34ኛው ዲቂቃ ላይ ባገባው ግብ ስፔትሲያ አቻ መኾን ችሎ ነበር። 67ኛው ደቂቃ ላይ ራቢዮት 3ኛዋን ግብ ሲያስቆጥር፤ 76ኛው ደቂቃ ላይ ይኸው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለራሱ ኹለተኛውን ለጁቬንቱስ አራተኛውን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል። በዚህም መሠረት ጁቬንቱስ ተጋጣሚው ስፔትሲያን 4 ለ1 ድል ማድረግ ችሏል።

ስፔትሲያ በደረጃ ሰንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ግርጌ 17ኛ ላይ ነው የሚገኘው።  ጁቬንቱስ በ12 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሳሱዎሎ ከጁቬንቱስ በ2 ነጥብ በልጦ ደረጃው ኹለተኛ ነው። መሪው ኤሲ ሚላን እስካሁን ባደረጋቸው ግጥሚያዎች 16 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል።  በትናንቱ ግጥሚያ፦ መሪው ኤሲ ሚላን ዑዲኒዜን 2 ለ1፤ ሳሱዎሎ ናፖሊን 2 ለ 0 አሸንፈዋል። ቶሪኖ በላትሲዮ የ4 ለ3 ሽንፈት ሲገጥመው፤ ሮማ ፊዮሬንቲናን 2 ለ0 ድል አድርጓል። ጄኖዋ እና ሳምፕዶሪያ አንድ እኩል ተለያይተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ