1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያገረሸው የእስራኤል ፍልስጥኤም ግጭት

ሐሙስ፣ መጋቢት 28 2015

በእስራኤል እና ፍልስጥኤማውያን መካከል እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ፍልስጥኤማውያን ቆስለዋል። ከእስራኤል ወገን አንድ ወታደር መቁሰሉ ተረጋግጧል። ከ 400 በላይ ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውለዋል። የፍልስጥኤም እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የሮኬት ጥቃት ሲያደርስ እስራኤል በበኩሏ ለአጸፋው የአየር ጥቃት ሰንዝራለች።

https://p.dw.com/p/4Pmoe
Israel | Die Zusammenstöße in Jerusalem
ምስል Ammar Awad/REUTERS

የእስራኤል ፍልስጥኤማውያን ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉ

በእስራኤል እና ፍልስጥኤማውያን መካከል እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ፍልስጥኤማውያን ቆስለዋል። ከእስራኤል ወገን አንድ ወታደር መቁሰሉ ተረጋግጧል። ከ 400 በላይ ፍልስጥኤማውያን በእስራኤል ወታደሮች ቁጥጥር ስር ውለዋል። የፍልስጥኤም እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የሮኬት ጥቃት ሲያደርስ እስራኤል በበኩሏ ለአጸፋው የአየር ጥቃት ሰንዝራለች። 

በእስራኤል እና ፍልስጥኤማውያን መካከል እንደ አዲስ ያገረሸው ግጭት በሁለተኛ ቀኑ ሮኬት ወደ ማስወንጨፍ እና የአየር ጥቃት ከፍ ብሎ ታይቷል። የእስራኤል ፖሊስ  በጥንታዊቷ። ኢየሩሳሌም ከተማ በሚገኘው የአል-አቅሳ መስጊድን መዉረሩን ተከትሎ ከፍልጥኤማውያን ጋር ግጭት ውስጥ መግባቱ ተገልጿል። ግጭቱ የተከሰተው ፍልስጥኤማውያኑ በቅዱሱ የረመዳን ወቅት እንዲሁም እስራኤላውያን ደግሞ የፋሲካን በዓል ለማክበር እየተዘጋጁ ባለበት ወቅት ነው  ። ጊዜ እና ሁኔታን እየጠበቀ የሚከሰተው የሁለቱ ባላንጣዎች ግጭት ዘንድሮም ከአስለቃሽ ጭስ ድንጋይ ውርወራ ከፍ ምሎ ከባድ መሳሪያ ለማታኮስ አፍታም አልወሰደበትም። ፍልስጥኤማውያን ታጣቂዎች ከጋዛ ሰርጥ ወደ ደቡባዊ የእስራኤል ክፍል ሮኬቶች ሲያስወነጭፉ እስራኤል በአጸፋው የአየር ጥቃት ሰንዝራለች ። 
እንደቀደመው ሁሉ ግጭቱ ተባብሶ አስከፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንዳያስከትል ከወዲሁ አስግቷል። 
እስራኤል እንደምትለው ፖሊስ መስጊዱን የወረረዉ «ሕግ የጣሱ» ያላቸዉን የፍልስጤም ወጣቶችን ለመያዝ እንደሆነ ነበር ያስታወቀችው ። በወቅቱ መስጊዱ ውስጥ የነበሩ  ምዕመናን እንደሚሉት ግን የእስራኤል ፖሊስ መስጊዱ ዉስጥ የነበሩ ምዕመናን ላይ ድብደባ ፈጽሟል፤ አስለቃሽ ጢስም ለቆባቸዋል።
«መስጊዱ ውስጥ ፖሊስ አስለቃሽ ጢስ ለቀቀብን ፣ ከዚያም በእያንዳንዱ ሰው ላይ ድብደባ መፈጸም ጀመሩ ፣ በርካታ ወጣቶችን ይዘው እጃቸውን ወደ ኋላ አስረው ፊታቸውን ወደ መሬት ከደፉ በኋላ ሲደበድቧቸው ነበር።» 
የእስራኤል ፖሊስ ባንፃሩ መስጊዱ ዉስጥ የነበሩ ፍልስጤማዉያን ፖሊሶቹ ላይ ድንጋይና ተቀጣጣይ ነገር መወርወራቸዉን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ለቋል። በአንጻሩ ጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድረው ሀማስ በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኙ ፍልስጤማውያን የአል አቅሳን መስጊድ ለመከላከል በብዛት ወደመስጊዱ እንዲሄዱ ጥሪ አቅርቧል።
የግጭቱን መቀስቀስ ተከትሎ በርካታ ሀገራት ተቃውሟቸውን ወዲያው ነበር ያሰሙት ። ቱርክ ግጭቱን አውግዛ የእስራኤል ፖሊስ አል አቅሳ መግባቱ የመስጊዱን ቅዱስ ስፍራነት መጣስ ነው ስትል ተቃውማለች። የአረብ ሊግም በተመሳሳይ ተቃውሞውን ከማሰማቱም ባሻገር ለትናንት ምሽት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ ነበር። ጀርመን በበኩልዋ ሁለቱም ወገኖችም ሆኑ ተጽእኖ ማድረግ የሚችል ሁሉ ሁኔታውን ከማባባስ  ይልቅ ለማርገብ የተቻላቸውን ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርባለች። 
ነገር ግን ትናንት ረቡዕ ከምሽቱ ጀምሮ ዛሬ እስኪነጋጋ ድረስ ፍልስጥኤማውያን ታጣቂዎች ከጋዛ ሰርጥ ሰባት ያህል ሮኬቶች ማስወንጨፋቸውን እስራኤል ዐስታውቃለች።  ከተተኮሱ ሮኬቶች መካከል አምስት ያህልን ማክሸፏንም ጨምራ ግልጻለች። የተቀሩት ሮኬቶች ግን በገላጣ ስፍራ መውደቃቸውን እና ያደረሱት ጉዳት አለመኖሩን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። 
ለጥቃቱም ራሱን የእስላማዊ ጂሃድ ኃይል ብሎ የሚጠራ ታጣቂ ቡድን ኃላፊነት መውሰዱን አንድ የአካባቢው የመገናኛ ቡዙኃን ዘግቧል። በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት ታጣቂ ቡድን በተደጋጋሚ ከጋዛ ተመሳሳይ የሮኬት ጥቃቶች ሲያደርስ መቆየቱን ዘገባው አክሎ አስነብቧል። 
የእስራኤሉ የመከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት እንዳሉት በእስራኤል ላይ ለሚደረግ ማንኛውም ጥቃት አጸፋው ከባድ ሊሆን እንዲሚችል ነው። 

Israel | Die Zusammenstöße in Jerusalem
ምስል Ammar Awad/REUTERS

«በጣም ግልጽ ማድረግ የምፈልገው ነገር ማንም በእና ላይ ጥቃት ለማድረስ ቢሞክር የእጁን ነው የሚያገኘው። በእስራኤላውያንም ይሁን በወታደሮቻችን ላይ ጥቃት ለማድረስ ዋጋ ይከፍልበታል። በድርጊቱም ይጸጸታል። መልካም የፋሲካ በዓል እንደሚሆንልን ተስፋ አደርጋለሁ።»
የግጭቱን መቀስቀስ ተከትሎ  እስራኤል ለአጸፋው በወሰደችው የአየር ጥቃት በትንሹ 50 ያህል ሰዎች ሳይቆስሉ እንዳልቀረ የፍልስጥኤም የቀይ ጨረቃ ማህበር ዐስታውቋል። በሁለቱ ቀናት ግጭት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከሁለቱም ወገን የሞተ ሰው ግን የለም። የእስራኤል ፖሊስ የአላስቃ መስጊድን መውረሩን ተከትሎ በተከተ ግጭት በቁጥጥር ስር የዋሉ ፍልስጥኤማውያን ቁጥር 450 ደርሷል።  
 ዘግየት ብሎ የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ውስጥ አንድ ወታደሩ በጥይት ተመቶ መቁሰሉን ገልጿል። 
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ በቅዱሱ ሃይማኖታዊ ስፍራ «የተከሰተውን ውጥረት » ለማርገብ መንግስታቸው ጥረት እያደደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 
በመካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ልዑክ ቶር ዌንስላንድ በበኩላቸው በአል አቅሷ መስጊድ የተፈጸመውን ድብደባ እና የጅምላ እስራት እንዲሁም እርሱን የተከተለውን አመጽ የሚያሳይ ምስል ከተመለከቱ በኋላ መደንገጣቸውን ተናግረዋል። ውጥረቱ እንዲረግብም ጠይቀዋል። 
የእስራኤል ፍልስጥኤማውያን ግጭት ከባለፈው የጎርጎርሳውያኑ ዓመት ተባብሶ መቀጠሉ ነው ከዘገባዎች መረዳት የሚቻለው ። በዚህ ዓመት ብቻ እስራኤል በሰነዘረችው ጥቃት 88 ፍልስጥኤማውያን ሲገደሉ ፤ በተመሳሳይ ጊዜ በ,አጸፋው ከፍልስጥኤማውያን ወገን በተሰነዘረ ጥቃት 15 ሰዎች ተገድለዋል። 
እስራኤል  እንደምትለው አብዛኞች ከፍልስጥኤም ወገን የተገደሉት አብዛኞቹ ታጣቂዎች መሆናቸውን ነው። ነገር ግን ፍልስጥኤማውያኑ ፤ ድንጋይ ወርዋሪ ታዳጊዎች እና በግጭሩ ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው ሰዎች ጭምር መገደላቸውን ዐስታውቀው ነበር። 

Israel | Die Zusammenstöße in Jerusalem
ምስል Ammar Awad/REUTERS

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ