ይኸ ጦርነት ኢትዮጵያን ወዴት ያደርሳታል?
እሑድ፣ ጥቅምት 29 2013ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ለሊት በመቐለ በሚገኝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጦር ሠፈር ላይ የትግራይ ልዩ ኃይል ጥቃት ፈጸመ ከተባለ በኋላ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የፌድራል መንግሥት እና ዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ወደለየለት ግጭት ውስጥ ገብተዋል። ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም በመቐለ ከተማ አካባቢ የፌድራሉ መንግሥት በተዋጊ የጦር ጀት ድብደባ መፈፀሙን የትግራይ ክልል አስታውቋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማግስቱ በሰጡት መግለጫ ይኸንንው አረጋግጠዋል። ዐቢይ "የጠላት ኃይል የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌለው ሐብት ላይ ቀንሶ ሀገሩን ለመከላከል የገዛቸውን ዋና ዋና ትጥቆች፤ ሚሳኤሎች፣ ሮኬቶች በመጠቀም ጥፋት ማካሔድ እንዳይችል አቅሙን ማዳከም" ያሉት ዓላማ እንደተሳካ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ምኒስትሩ "በባድመ ግንባር፣ በፆረና፣ በዛላንበሳ በዋና ዋና ቦታ ተሰልፈው ያሉ የሠራዊት አባላት እና ትጥቆቻቸው ሙሉ በሙሉ ከጠላት ፍላጎት ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል" ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ በክልሉ የሠፈረው የኢትዮጵያ ጦር የታጠቃቸውን የጦር መሳሪያቸው የክልሉ መንግሥት በእጁ እንዳስገባ ተናግረው ነበር።
ግጭቱ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ጭምር ተቀስቅሷል። ለመሆኑ ይኸ ጦርነት ኢትዮጵያን ወዴት ያደርሳታል። ይኸ የውይይት መሠናዶ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ቀውስ ላይ አተኩሯል። ውይይቱ የተካሔደው ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ነው።
በብሪታኒያው ሮሐምተን ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ የሚገኙት አቶ መሐመድ ግርማ፤ በኖርዌይ በርገን ዩኒቨርሲቲ የፒኤች ዲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ ሙሉ በየነ እና በቪየና የዲፕሎማሲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ሞገስ ዘውዱ በውይይቱ ተሳትፈዋል።
ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ