የዘንድሮው የጀርመን የክብር ኒሻን ተሸላሚ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 8 2013በጀርመንኛ መጠሪያው «ፈርዲንስትክሮይትስ አም ባንደ»፣የፌደራል ጀርመን መንግሥት በፖለቲካው በኤኮኖሚው በባህል እንዲሁም በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ወይም በበጎ አድራጎት መስክ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የሚሰጠው የክብር ሽልማት ነው።ይህ ሽልማት ዘንድሮ ለትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ተበርክቷል። የኤኮኖሚና የአስተዳደር ምሁሩ ዶክተር ፀጋዩ በአሁኑ ጊዜ በታዋቂው የጀርመን መኪና አምራች ኩባንያ በሜርሰዲስ ቤንዝ ውስጥ በሰው ኃይል ዘርፍ በብዝሃነት ክፍል በሃላፊነት ይሰራሉ።ከመደበኛ ሥራቸው ውጭም በትርፍ ጊዜያቸው በሚያዘወትሩት የጅዶና ጁጁትሱ ስፖርትም ይታወቃሉ ። በዚሁ ስፖርት ጥቁር ቀበቶ ና ከዚያም ከፍ ላይ ደረጃ ያላቸው ዶክተር ፀጋዮ ሥልጠና ይሰጣሉ ፤ በፈታኝነትም ያገለግላሉ። በአሁኑ ጊዜ የዓለም አቀፍ ጂ ጁትሱ ፌደሬሽን የስነ ምግባር ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው።
ዶክተር ፀጋዬ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ነበር በኢትዮጵያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የነጻ ትምህርት እድል አግኝተው ምሥራቅ ጀርመን የመጡት።ስቪካው በተባለችው የምሥራቅ ጀርመን ከተማ ቋንቋ ተማሩ። ብዙም ሳይቆዩ የበርሊኑ ግንብ ፈርሶ ሁለቱ ጀርመኖች ከተዋሀዱ በኋላ ከበርሊኑ ሁምቦልት ዩኒቨርስቲ በንግድ አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪ ያዙ ። በዛው ዩኒቨርስቲ በረዳትነት ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ በኢኮኖሚክስ ወይም በምጣኔ ሃብት በተለይም የንብረት ባለቤትነት መብትን በመሳሰሉ የኤኮኖሚ ህጎችና በኢንቬስትመንት ላይ ባተኮረ የትምህርት ዘርፍ የዲክትሬት ዲግሪ ለመያዝ በቁ ።ባለፈው ሳምንት ሀሙስ ነበር በጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ስም፣በበርሊን ክፍለግዛት የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አስተዳደር የውስጥ ጉዳዮችና የስፖርት ክፍል የስፖርት ዘርፍ ዋና ጸሀፊ አሌክሳንደር ድትሴምብሪትስኪ የክብር ኒሻን ሽልማቱንና ሽታይንማየር የፈረሙበት የእውቅና ምስክር ወረቀት ለዶክተር ፀጋዮ የሰጡት።በኮሮና ምክንያት ሲገፋ በቆየው የሽልማቱ ስነ ስርዓት ላይ ዶክተር ፀጋዬ ና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ 5 ሰዎች ብቻ ናቸው የተገኙት። በርሊን ምክር ቤት አስተዳደር የውስጥ ጉዳዮችና የስፖርት ክፍል ውስጥ በተካሄደው የሽልማት በስነ ስርዓት ላይ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን ተገንተዋል።አምባሳደር ሙሉ ለዶክተር ፀጋዬ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት ሽልማቱ ለኢትዮጵያ እንደተሰጠ የሚቆጠር ነው ብለዋል። ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ሲሉ የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል ።
«ፌደራል ክሮስ ኦፍ ሜሪት የከፍተኛ አስተዋጽኦ ሽልማት በመሆኑ በሃገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚሰጥ በጣም ነው ደስ ያለን። የኢትዮጵያ ሽልማት አድርገን ነው የወሰድነው።ለፍቶ በጥረቱ ያገኘው ስለሆነ ደስ ይላል።የሁላችንም ደስታ ነው።ብዙ ለወጣቶችም አርአያ የሚሆን ነው። የትም ሃገር ሆነን ውጣ ውረድ አልፈን መኖር ብቻ ሳይሆን ከራሳችን አልፈን ለሰውም ኖረን እንደገና ለህዝብ ለዓለምም አርአያነት ትልቅ ነገር ነው።እና ዶክተር ፀጋዬ ሌትም ቀንም ይሰራል።ለሊት ቁጭ ብሎ የሚያድርበት ጊዜ አለ።ስለ ኢትዮጵያ የተሳሳተ መረጃ ሲመጣ ይሄ ልክ አይደለም ብሎ ለሚመለከታቸው ሁሉ በጀርመንና በእንግሊዘኛ ጽፎ እኔን እስኪ እይልኝ እያለ እርሱ ቁጭ ብሎ ሲያድር እኔም ቁጭ ብዬ የማድርበት ጊዜ አለ።የጀርመን መንግሥት ደግሞ እስካሁን ላደረገው አስተዋጽኦ ይሄን ሪኮግኒሽን በመስጠቱ በጣምደስ ብሎኛል ።የጀርመን መንግሥት ይህ ዓይን ስላለው እናመሰግነዋለን።»
ኢትዮጵያዊዉ የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ ልዑል ዶክተር አስፋ ወሰን አስራተም በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓም ከዛሬ 5 ዓመት በፊት ይህን የፌደራል ጀርመን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ተሸልመዋል። ለአዉሮጳና አፍሪቃ አህጉራትና ሕዝቦች መቀራረብ ላበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦ ሽልማቱ የተሰጣቸው ልዑል ዶክተር አስፋወሰን፣እንደሚሉት ዶክተር ፀጋዬ ለዚህ ክብር መብቃታቸው ብዙ ነገሮችን ያሳያል።
«መቼም ይሄ የሚያሳየው በጣም ከፍተኛ ክብር መሆኑ የማያጠራጥር ነው።ይሄ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ በጀርመን ሃገር የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጀርመን ማኅበረሰሰብ ውስጥ ምን ዓይነት ከፍተኛ ቦታ ይዘው እንደሚገኙና በእውነቱ ከብዙ ዓመት ኑሮ በኋላ የቱን ያህል ከጀርመን ማኅበረሰብ ጋር መዋሃዳቸውን ነው የሚያሳየው። ጀርመኖችም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ይሄ ስለሆነ በመሃከላችን እንደገና አንድ ሰው ፈልገው እንዲህ ዓይነቱን ክብር መስጠታቸው እነርሱን ያስመሰግናቸዋል።በኢንተግሬሽንም በኩል የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቦታ ያስይዘዋል።ስለዚህ እኔ ራሴ በጣም አድርጎ ነው ደስ ያለኝ።የኔ ተከታይ ሆኖ ዶክተር ጸጋዬ በእውነቱ በብዙ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ኮምንቲ ብዙ እርዳታ የሰጠና ለአገሩም በጣም የሚያስብ ልጅ በመሆኑ እጅጉን አድርጌ ነው የተደሰትኩት። እንግዲህ የዶክተር ፀጋዬን ምሳሌ ተከትለው ሌሎችም ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን የሃገራችውን ስም በውጭ ሃገር ለማስጠራት የሚያደርጉትን ትግል ሁሉ እንደሚቀጥሉ ወደፊት ደግሞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብዬ ከልብ አምናለሁ።»
ኔትሽቴት ኒፍሉዮዶ ዶክተር ጸጋዬን በቅርብ የሚያውቋቸው የቀድሞ የስራ ባልደረባ ናቸው።ከዶክተር ፀጋዬ ጋር ጥሩ ጓደኛሞችም ነን ይላሉ ዶክተር ፀጋዬ ይህን ሽልማት ማግኘታቸው በጣም አስደስቷቸዋል። ለሽልማቱ መመረጣቸውን ከነገሯቸው ሰዎች አንዱ ነኝ የሚሉት ኒፍሉዮድ ዶክተር ጸጋዬን እንዲህ ገልጸዋቸዋል።
«በጣም ብልህ ንቁና ተግባቢ ሁሌም ሌሎችን በትዕግስት የሚያዳምጥ ጆሮ ያለው፣ የጀርመናውያንንም ሆነ የውጭ ሃገር ዜጎችን ችግሮች በጥሩ ስሜት የሚረዳ መልካም ሰው ነው።አንድ ሰው ከየትም ይሁን ከየት ለርሱ ምንም ልዩነት የለውም። »
በርሳቸው እምነት ዶክተር ጸጋዬም ሽልማቱ የሚገባቸው ሰው ናቸው።
«ምክንያቱም ሁሌም የትውልድ ሃገሩን ጥቅሞችና የጀርመንንምጥቅም ከግምት ውስጥ እያስገባ ነው የሚንቀሳቀሰው።ለሚሰራበት ማኅበረሰቡ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል።በስፖርት ንቁ ተሳታፊ ነው።በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይም ከልጃቸው ማያ ጋር ይሳተፋሉ። እነዚህ በሕይወት ዘመናቸው ያከናወኗቸው ተግባራት ናቸው።ይህ ተግባር የሚያሸልም ነው።በእኔ እምነት ሽልማቱ ለዶክተር ጸጋዬ በእውነት የሚገባ ነው።»
ዮሐንስ ዳክስተር በዓለም አቀፍ የፖሊስ ጁዶ ፌደሬሽን እና ስፖርት ኮሚሽን ዋና የፖሊስ ኮሚሽነር ናቸው። የቀድሞ የአውሮጳ ጁዶ ውድድር አሸናፊ ዳክስተር ከዶክተር ፀጋዬን ከተዋወቁ 13 ዓመት ሆኗቸዋል።ለዶክተር ጸጋዬ ትልቅ አክብሮት አላቸው። የዓላማ ጽናት ያለው መፍትሄ ለመፈልግ የማይቦዝኑ ሰው ሲሉ አወድሰዋቸዋል።
«ለኔ ዶክተር ጸጋዬ ሀቀኛ ሰው ነው።አንድ የተነሳበትን ዓላማ ይዞ የሚቀጥል ሰው ነው።ብዙ የሚያናድዱ ወደ ኋላ የሚመልሱ ነገሮች ቢኖሩም በዩዶ መርህ መሠረት ተስፋ አይቆርጡም ።በነገራችን ላይ እውነተኛ የሰብዓዊነት አርበኛም ነው።ሰዎችን መርዳታ ይወዳል።ችግር ሲያጋጥም መፍትሄ ለማግኘት ሳይታክት ደጋግሞ የሚሞክር ፤ሁሌም ሰዎች ለተሻለና ዘላቂ እድገት እንዲበቁ የሚያስችል መፍትሄ የሚፈልግ ሰው ነው »
ባክስተር የጀርመን መንግሥት ለዶክተር ጸጋዬ ይህን ሽልማት የሰጠው ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪቃ ባደረጉት አስተዋጽኦ መሆኑን ገልጸው በአማርኛ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ልዑል ዶክተር አስፋወሰን ደግሞ ዶክተር ፀጋዬን ወገኖች የሚረዳ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ሲሉ ነው ብለዋቸዋል።
አምባሳደር ሙሉም ዶክተር ጸጋዬ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማገዝ ያለእረፍት የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።የዘንድሮው የጀርመን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ተሸላሚ ዶክተር ጸጋዬ ዶቼቬለ የአማርኛው ክፍልን ጨምሮ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሀን በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልሶችን በመስጠትና በውይይቶች ላይም በመካፈል ይታወቃሉ።ለዚህ ክብር የበቁትን ዶክተር
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ