ዶናልድ ያማማቶ ወደ ኤርትራና ኢትዮጵያ ሊጓዙ ነው
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 13 2010በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪቃ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ነገ ሚያዝያ 14 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ኤርትራ ይጓዛሉ። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በድረ-ገፁ እንዳለው አምባሳደሩ በአስመራ ቆይታቸው በሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳዮች ላይ ከኤርትራ መንግሥት ሹማምንት ጋር ይመክራሉ። ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር የመገናኘት እቅድ ያላቸው አምባሳደሩ በአስመራ የሚገኘውን የሀገራቸውን ኤምባሲ ይጎበኛሉ ተብሏል። አምባሳደሩ በኤርትራ የሚያደርጉትን የሶስት ቀናት ቆይታ ሲያጠናቅቁ ሚያዝያ 16 ወደ ጅቡቲ ይጓዛሉ።
ያማማቶ በጅቡቲ በፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ርዳታ እና የጸጥታ ትብብር ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚመክረውን የሁለትዮሽ ስብሰባ ይሳተፋሉ። ከሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ይገናኛሉ። ረዳት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅሞች እና ሥጋቶች ላይ ይመክራሉ ተብሏል። የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካ በቅጡ ያውቃሉ የሚባሉት ያማማቶ ወደ ሶስቱ ሀገራት የሚያደርጉት ጉብኝት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።
በድንበር ይገባኛል ውዝግብ ከጎረቤቶቿ ጋር ቁርሾ ውስጥ የገባችው ኤርትራ ከኢትዮጵያም ይሁን ከጅቡቲ ጋር ያላት ግንኙነት ከሻከረ በርካታ አመታትን አስቆጥሯል። በሁለት ቀናት ልዩነት አስመራ እና አዲስ አበባን የሚያካልሉት አምባሳደሩ ሁለቱን አገሮች ለማሸማገል ውጥን ይኑራቸው አይኑራቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያለው ነገር የለም።
ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ለተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው አይዘነጋም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከኤርትራ መንግስት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየውን አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን። የበኩላችንንም እንወጣለን" ማለታቸው ይታወሳል። “በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነታችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ተስፋለም ወልደየስ