ጀርመን ዜጎችዋን ከቻይና አስወጣች
ዓርብ፣ ጥር 22 2012ጀርመን በቻይናዋ ከተማ ኹዋን የሚገኙ ወደ 130 የሚሆኑ ሰዎችን ወደ ሃገራቸዉ ለመመለስ የሃገሪቱ ጦር ልዩ አዉሮፕላንን ዛሬ ላከ። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ በሰጡት መግለጫ ከቻይና ኹዋን ከሚመለሱት 130 ሰዎች መካከል 90 ዎቹ ጀርመናዉያን ናቸዉ፤ 40 ዎቹ ደግሞ ከጀርመናዉያኑ ጋር የተዛመዱ የሌላ ሃገር ዜጎች ናቸዉ። ከተመላሾቹ መካከል ግን በኮሮና ተኅዋሲ ተይዞአል ተብሎ የተጠረጠር አንድም ተመላሽ የለም ተብሎአል። ጀርመን በባቫርያ ግዛት እስካሁን አንድ ሕፃንን ጨምሮ ስድስት በኮሮና ተኅዋሲ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸዉን እና በጥብቅ የምርመራ ክትትል ላይ መሆናቸዉን አረጋግጣለች።
በሌላ በኩል ፈረንሳይ በኹዋን የሚገኘዉን የፔጆ እና ሴትሮን የመከና መለዋወጫ ሦስት ማዕከልን እስከ የካቲት ሰባት ድረስ እንደምትዘጋ አስታዉቃለች። ሲንግፖር እና ሞንጎልያ በበኩላቸዉ ድንበራቸዉን በማጥበቅ ከነገ ቅዳሜ ጀምሮ ባለፉት 20 ቀናት በቻይና የነበሩ የዉጭ ሃገር ዜጎችም ሆኑ ቻይናዉያንን ወደ ሃገራቸዉ እንደማያስገቡ አስታወቀዋል። ሃገራቱ ከቻይና የመጡ እና ወደ ሌሎች ሃገሮች የሚያቋርጡ ተጓዦችንም በአየር ማረፍያ አንቀበልም ብለዋል። ከቻይና የሚመለሱ የሲንጋፖር ዜጎች ግን ሃገራቸዉ ደርሰዉ ከአዉሮፕላን ከወረዱባት ሰዓት ጀምሮ ለ 14 ቀናት በተለየ ስፍራ ተይዘዉ የጤና ክትትል ከተደረገላቸዉ በኋላ ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀል እንደሚችሉ ተመልክቶአል።
በሩስያም ሁለት ቻይናዉያን ላይ የኮሮና ቫይረስ ተሕዋሲ መገኘቱን አስታዉቃለች። በሳይበርያ አቅራብያ የተገኙት እነዚህ ቻይናዉያን የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸዉ ነዉ፤ ከማኅበረሰቡ ጋርም ብዙ ንኪኪ ስላልነበራቸዉ ምንም ስጋት እንደሌለ የሃገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ዛሬ አስታዉቋል። ሩስያ ወደ ጎረቤት ቻይና የነበራትን አብዛኛዉን የአየር በረራና ፤ የመንገደኞች የባቡር መስመር ማቋረጥዋን ይፋ አድርጋለች። ቻይናዉያንን ያለ ቪዛ ወደ ሃገርዋ ታስገባ የነበረዉ አርሜንያ በበኩልዋ ለቻይናዉያን ታቀርብ የነበረዉ ይህን አገልግሎት ዘግታለች።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ