1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጉጂ ዞን 12 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

ረቡዕ፣ ጥር 15 2016

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ታጣቂዎች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ገድለው ሌሎች ሁለት አቆሰሉ ፡፡ በወረዳው ኤርጋንሳ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ትናንት ተፈጸመ በተባለው ጥቃት የተገደሉት የክልሉ መንግሥት የሚሊሺያ ታጣቂዎች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4bd9p
ምዕራብ ጉጂ
ምዕራብ ጉጂ መንደር ውስጥ ነዋሪዎችምስል DW/S.Wegayehu

ጉጂ ዞን ታጣቂዎች ነዋሪዎች ላይ ጥቃት አደረሱ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ታጣቂዎች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ገድለው ሌሎች ሁለት አቆሰሉ ፡፡ በወረዳው ኤርጋንሳ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ትናንት ተፈጸመ በተባለው ጥቃት የተገደሉት የክልሉ መንግሥት የሚሊሺያ ታጣቂዎች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ በአጎራባች የኮሬ ዞን ኬሌ ሆስፒታል በማገልገል ላይ የሚገኙ አንድ የህክምና ባለሞያ ትናንት በሆስፒታሉ ዘጠኝ አስክሬን መመልከታቸውን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ታጣቂዎች ዐሥራ ሁለት ሰዎችን ገድለው ሌሎች ሁለት አቆሰሉ ፡፡ በወረዳው ኤርጋንሳ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ትናንት ማክሰኞ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት የተገደሉት የክልሉ መንግሥት የሚሊሺያ ታጣቂዎች መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳሉት ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈፀሙት በአካባቢው ሰፍሮ ነበረ ያሉት የአገር መከላከያ ሠራዊት ቀበሌውን ለቆ ከወጣ ከቀናት በኋላ ነው ፡፡ " ታጣቂዎቹ መከላከያ ሠራዊቱ ከሥፍራው መነሳቱ መረጃ ሳይደርሳቸው አንዳልቀረ እገምታለሁ " ያሉ አንድ የኤርጋንሳ ቀበሌ ነዋሪ " በጥቃቱ 12 ሰዎች ናቸው የተገደሉት ፡፡ ሟቾቹ የቀበሌ ታጣቂዎች ሲሆኑ የገደሏቸውም ሸኔ ተብለው የሚጠሩ ናቸው ፡፡ ገዳዮቹ ከሟቾቹ አስክሬን ላይ መሣሪያዎችን ለቅመው  ይዘው ሄደዋል ፡፡ ሦስቱ አስከሬን እዚሁ ሲቀር ዘጠኙን ከቡሌ ሆራ በመጡ ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ተወዷል  "ብለዋል ፡፡

አስክሬኖች በኬሌ ሆስፒታል

ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ገላና ወረዳም ሆነ ምዕራብ ጉጂ ዞን  አስተዳደር ደውሏል ፡፡ ይሁንአንጂ ይመለከታቸዋል የተባሉት ባለሥልጣናት የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በጥቃቱ ዙሪያ  አስተያየት ለመስጠት ፍላጎት ሳያሳዩ ቀርተዋል ፡፡ በአጎራባች የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ኬሌ ሆስፒታል በማገልገል ላይ የሚገኙ አንድ የህክምና ባለሙያ ግን ትናንት በሆስፒታሉ ዘጠኝ አስክሬን መመልከታቸውን ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡ ጠዋት ላይ በአጎራባች የጉጂ ዞን በሚገኘው ገላና ወረዳ ውስጥ ተኩስ መካሄዱ ሲወራ አንደነበር የጠቀሱት የህክምና ባለሙያው " ማታ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ ዘጠኝ አስክሬን ወደ ሆስፒታሉ ገብቶ አደረ ፡፡ ዛሬ ጠዋት ደግሞ በኦሮሚያ የፖሊስ ፓትሮል ተሽከርካሪዎች ወደ ገላና ወረዳ ተወስዷል ፡፡ ካዛ ውጭ በጥይት ተመተው ለመጡ ሁለት ሰዎች ህክምና ተደርጎላቸዋል  " ብለዋል ፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን
የምዕራብ ጉጂ ዞን ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚለውና መንግሥት ሸኔ ሲል የሚጠራው ታጣቂ ሀይል ከሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ ዞኖች አንዱ ነው ፡፡ ምስል DW/S.Wegayehu

የሥጋት ኑሮ

በትናንቱ ጥቃት ዙሪያ የአሮሚ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን እስከአሁን ያሉት ነገር የለም ፡፡ ነዋሪዎች ግን በቀበሌው በመንግሥት ሚሊሺያዎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መካከል ባለው ፍጥጫ የተነሳ በሥጋት ውስጥ እየኖሩ እንደሚገኙ  ይናገራሉ ፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚለውና መንግሥት ሸኔ ሲል የሚጠራው ታጣቂ ኃይል ከሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ ዞኖች አንዱ ነው ፡፡ በአካባቢው በሁለቱ ሀይሎች መካከል በየጊዜው በሚካሄደው የተኩስ ልውውጥ የተነሳ በርካቶች ለሞትና መፈናቀል መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው ፡፡

ሸዋንዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ