1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት የማቆም ውሳኔ፣ ርዳታ እና የሳውዲ ተመላሾች

ዓርብ፣ መጋቢት 23 2014

መንግሥት ለሰብዓዊነት በሚል በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የማቆም ውሳኔውን ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል። የመንግሥትን መግለጫ ተከትሎም በህወሃት የሚመራው የትግራይ ክልል አስተዳደር ውሳኔውን መቀበሉን አሳውቋል። ከሁለቱም ወገን የተሰማውን ግጭት የማቆም ውሳኔ ተከትሎም በርካቶች የተለያዩ አስተያየቶችን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን አካፍለዋል።

https://p.dw.com/p/49JjI
Äthiopien | Stadtansicht Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊነት በሚል በሰሜን ኢትዮጵያ የአንድ ወገን ግጭት የማቆም ውሳኔውን ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል። የመንግሥትን መግለጫ ተከትሎም በህወሃት የሚመራው የትግራይ ክልል አስተዳደር ውሳኔውን መቀበሉን አሳውቋል። ከሁለቱም ወገን የተሰማውን ግጭት የማቆም ውሳኔ ተከትሎም በርካቶች የተለያዩ አስተያየቶችን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን አካፍለዋል። አብዛኛው አስተያየት ጽንፍ የያዘ በመሆኑ አዎንታዊ ከሆኑት ጥቂቶቹን ለዛሬ መራርጠናል። ሄለን ጌታቸው በፌስቡክ፤ «አረ ይቁም ሰላማችን ይሻለናል፤ ሰላም ይበልጣል፤ ከሁሉም የሰላም ዋጋው ትልቅ ነው» ሲሉ አቤል አበበም ፤ «፣ይኽን ነው ለትግራይ የምንፈልገው፤ አማራንም ሆነ አፋር ክልልንም አንዘንጋ» ነው ያሉት። መኮንን ዳምጠው በደግሞ «ግጭት ነው እንዴ? ጦርነት አይደል?» በማለት ጠይቀዋል። እሸቱ ሞላ ፤ «ሰብአዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማለት ዳቦ ይዘንብላችኋል ማለት አይደለም። ገና ተፈልጎ፤ ተጓጉዞ ,,,ነው» በማለት ለተቸገረው ወገን ሊደርስ ይገባዋል ስላሉት የርዳታ ሁኔታ ሃሳባቸውን አጋርተዋል። 

Äthiopien Humanitäre Hilfe
ምስል Alemnew Mekonen/DW

መንግሥት ባወጣው መግለጫ፥ ሰብዓዊነትን መሰረት በማድረግ ግጭት ማቆሙን ገልጾ ሳምንቱን ሙሉ ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ በአየር እንዲያጓጓዝ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች መፍቀዱን አስታውቋል። በዚህም መሰረት መድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁሶች፣ ገንዘብ እና አልሚ ምግቦች በተቻለ መጠን በአየር መጓጓዝ መጀመራቸውን ጠቅሷል። ሆኖም የህወሃት ታጣቂዎች የማኋኋዝ ሂደቱን እያደናቀፉ ነው ሲል ከሷል። አያይዞም የህወሃት ታጣቂዎች በጦርነቱ ወቅት ከተቆጣጠሯቸው ከአፋርም ከነ ከአማራ ክልል እንዲወጡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግም አሳስቧል። ህወሃት በበኩሉ ክሱን በማስተባበል መንግሥት ቃሉን አክብሮ ርዳታውን እንዲልክ ጫና እንዲደረግበት ጥሪ አቅርቧል። ወይ ጊዜ የሚል ስም ያላቸው የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «አረ ተው በሰው ህይወት አትቀልዱ፤ መቼም ይህንን መሰሉን ውሸት ለምደነዋል ይልቁንስ ለሌላ እልቂት እየተዘጋጀን ነው ማለት አይሻልም?» ሲሉ ይጠይቃሉ። «እባካችሁ ፖለቲካውን አቁማችሁ ሰብዓዊነትን አስቀድሙ እና ኃላፊነት እንዳለበት መንግሥት ተንቀሳቀሱ» ያሉት ደግሞ ነጊሾ ሹሜ ናቸው።

Logo I Facebook und diem
ምስል Thiago Prudencio/SOPA/ZUMA/picture alliance

የሁለቱም ወገን መግለጫ ያልጣማቸው የሚመስሉት ኑር ሳልህ ደግሞ፤ «ተራ የቃላት ጨዋታ እየተጫወተ ያለው ማን እንደሆነ ይታወቃል፣ ይህ ተራ የቃላት ጨዋታ ሀገር ውሰጥ ያለውን የተወሰነ ህዝብ ያደናግር ይሆናል እንጂ፣ ዓለምን በዚህ ዘመን በዚህ ማደናገር አይቻልም።» ይላሉ። ርዳታውን አስመልክተው አስተያየት ከሰጡት መካከል ደግሞ ድላይ አበበ ደግሞ «እስኻሁን ድረስ ምንም ኣላየንም ወሬ ብቻ» ብለዋል።

መሀመድ አሊ መሀመድ ደግሞ ጥንቃቄ ላይ አተኩረዋል፤ «የሚላኩ ነገሮች በደንብ ቢፈተሹ ጥሩ ነው!!! 1: የሣተላይት ሥልኮች 2: የሬዲዮ ኦፒዎች 3: መነፀሮች ሊላኩ ይችላሉ! ጥንቃቄ ይደረግ» ይላሉ።

እርዳታ ጭነው ከዚህ ቀደም ወደ ትግራይ ስለገቡ ተሽከርካሪዎች የጠየቁት መኮንን ገመስቀል ደግሞ፤ «በእርዳታ ስም የገቡ ከአንድ ሽህ በላይ የመጀመሪያዎች መቸ ተመለሱ? ድጋሜ የንፁሀን ሰው ደም ለማፍሰስ?»  ነው ያሉት። ኩካ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «ታጣቂዎቹ መንገዱን እና አካባቢውን ለቀው መውጣት ቢችሉና የህዝብን ረሃብ ለመደራደሪያነት ባያውሉት መልካም ነበር።» ይላሉ። ኡም ፈራሀን ደግሞ፤ «የትግራይ ርሀብተኞችን እየተቃወምን አይደለም ነገር ግን ሌሎች አካባቢዎች እንደዚሁ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ያለመጠለያ ዝናብና ፀሐይ የሚፈራረቅባችው ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ትቂት የሚባሉ አይደሉም።» በማለት በሌላ አካባቢም ርዳታ የሚጠብቁ መኖራቸውን ሲያመላክቱ፤ ተስፋዬ ካሳ በበኩላቸው፤ «ለወሎ ሕዝብማ ማን ይድረስለት 5 ወር በጁንታ ታፍኖ ሲሰቃይ ሀብት ንብረቱ ሲዘረፍ አሁንም በኑሮ ውድነትና በሕገወጥ ነጋዴዎች እየተሰቃየ መንግሥት ዞር ብሎ አላያቸውም።» ይላሉ። ሞላ ወልደገብር ደግሞ፤ «እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ግን ቻይ አለ?» በማለት ጠይቀዋል።

Saudi-Arabien | äthiopische Häftlinge
ምስል Privat

በዚህ ሳምንት የተሰማው አዎንታዊ ዜና ሳውድ አረቢያ ውስጥ ስቃይ ላይ ከሚገኙ ወገኖች ጥቂቱ ወደ ሀገራቸው መመለስ መጀመራቸውን የተመለከተው ነው። ረቡዕ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መሠረት ከዘጠኝ መቶ በላይ ሳውዲ በስደት የቆዩ ወገኖች አዲስ አበባ ገብተዋል። እሌኒ ግርማ ፤ «እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን ሁሉም እንደሚገቡ ተስፋ አለን ።» ሲሉ ፤ ሃዲ ዋሲ ደግሞ፤ «አለሀምዲሊላህ አላህ መጨረሻውን ያሳምረው» ብለዋል። ሳውዲ ውስጥ በተለያዩ እስር ቤቶች ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች እንዳሉ ነው የተገለጸው። በዚህም ምክንያት በቀን እነሱን ወደ ሀገር ለመመለስ የሚደረገው በረራ እንዲጨምር የተመኙ እጅግ ብዙ ናቸው። ተስፋ ሲራጅ፣ «አባይን በጭልፋ ነው ስራችሁ፤ ያ ሁሉ ህዝብ ተቀምጦ በዚህ አካሄድ መች ነው ተሳፍረው እሚያልቁት» ብለው ሲጠይቁ፤ ቢስማህ ለትራ በበኩላቸው፤ «ብቻ ባይዋጥልኝም ተመስገን ልበል ግን በደንብ የምናመስግናችሁ ሁላችንም ጠቅላችሁ ሰታስገብን ነው። ያሁኑ በቂ ሆኖ አይደለም ሰንት ግዜ ልባችን ከተስበረ፤ በሉ ከቻላችሁ ልባችንን ጠግኑልን የሚያኮራ ሥራ ሰርታችሁ።» ብለዋል። ቤዛ ፍቅር ቤዛ ፍቅር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ፤ «ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን፤ ግን ይሕ ብቻ በቂ አደለም፤ ይጨመር፤ በረያድ ያሉት እስረኞች በጣም እስቃይ ላይ ናቸው ድምፃቸውን እንኳን ለማሰማት አልቻሉም ።» ይላሉ። ኤፍሬም ካሳው፤ «አትቀልዱ ትኩረት ሰጥታችሁ እንደገና ልትገመግሙት ይገባል። ከ120 ሺህ በላይ እስረኛ አሁንም እየተሰቃየ ነው። መያዝም አልቆመም። እባካችሁ ህዝብን ሊያረካ የሚችል ሥራ ስሩ።» በማለት ተማጽነዋል። የያሲን ወዳጅ ከቦረና እንዲህ ነው ያሉት፤ «ለመሆኑ ከረመዷን በፊት 35ሺ ያላችሁት ለምን ቀረ በሳምንት 498 ሰው ገብቶ ከመቶሺ በላይ ያሉት መቸ ሊያልቅ ነው? አረ ተው በወገን ስቃይ አትቀልዱ።» ኑልግ አክራምም መንግሥት ያስብበት ይላሉ፤ «መንግሥት አሁንም ያስብበት እስር ቤት ያለውን በአጭር ጊዜ አስገብቶ በውጭ የሚገላታውን ደግሞ መፍትሔ እንዲሰጠው።» የአሚር ቢን ኢብራሂም አስተያየት ይለያል፤ «ያላቸው ንብረት እና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ቤተሰብ እንድቀላቀሉ የበኩሉን ሚና ይወጣ በሀገራቸው ጅብ እንዳያገኛቸው።» ከስደት የተመለሱት ወገኖች ዳግም ለችግር እንዳይዳረጉ ስጋት ያላቸው ይመስላል። ሁሴን ከማልን ያስደሰታቸው ሌላ ነው፤ «ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ ሙስሊምና ክርስቲያን ሳይሉ ኮሜንት ላይ ያላቻውን ደስታ ለወገንና ለሀገራቸው በመግለጽ ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ማየትና መስማት እንዴት ያስደስታል ። ሀገራችን ኢትዮጵያንና ህዝቡን ካለበት መከራና ስቃይ አላህ በቃ ይበልልን አሜን።» በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

Ethiopian Airline Typ einer Boeing 737-800
ምስል AP

 ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ