1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስመራ ገቡ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11 2012

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ዐቢይ ወደ አስመራ ያቀኑት ለሥራ ጉብኝት መሆኑን ቢገልጽም ተጨማሪ ማብራሪያ አላቀረበም። ሁለቱ መሪዎች የኢትዮጵያ እና የኤርትራን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና የቀጠናውን ትብብር ስለማሳደግ እንደሚወያዩ የኤርትራው ማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/3fWqf
Eritrea - Der äthiopische Ministerpräsident Abiy und der eritreischen Staatschef Afewerki
ምስል Reuters/G. Musa Aron Visafric

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አስመራ ገቡ። ጠቅላይ ምኒስትሩ አስመራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀብለዋቸዋል።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ዐቢይ ወደ አስመራ ያቀኑት ለሥራ ጉብኝት መሆኑን ቢገልጽም ተጨማሪ ማብራሪያ አላቀረበም። ሁለቱ መሪዎች የኢትዮጵያ እና የኤርትራን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና የቀጠናውን ትብብር ስለማሳደግ እንደሚወያዩ የኤርትራው ማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ወደ አስመራ ከተጓዙት የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ድዔታ ሬድዋን ሁሴን ይገኙበታል። አምባሳደር ሬድዋን ባለፈው ታኅሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም.  የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ዴዔታ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ባለፈው ሰኔ ወር ወደ ግብጽ እና ሱዳን አቅንተው ነበር። ፕሬዝዳንቱ ከኤርትራ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ኦስማን ሳሌሕ እና አማካሪያቸው የማነ ገብረአብ ጋር ባለፈው ሰኔ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ካይሮ ተጉዘው ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታኅ አልሲሲ ተወያይተዋል።

ከዚያ በፊት ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ኻርቱም ያቀኑት ኢሳያስ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል ፋታሕ አል ቡርሐን እና ምክትላቸው ሉቴናንት ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ተገናኝተው ነበር።

የዛሬው የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኤርትራ ጉብኝት ኢሳያስ ወደ ኻርቱም እና ካይሮ ካደረጓቸው ጉዞዎች ግንኙነት ይኖረው እንደሁ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ በኩል የተገለጸ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ዕርቅ ካወረዱ ባለፈው ሐምሌ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ሁለት አመታት ሞላቸው። አሁንም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከስምምነት የደረሱባቸው ጉዳዮችም ሆኑ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በተደጋጋሚ ተገናኝተው የተወያዩባቸው ሐሳቦች በግልጽ አልቀረቡም።

እሸቴ በቀለ