ጥር 30 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥር 30 201433ኛውን የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ልዩ ብቃታቸውን ያስመሰከሩት ሴኔጋሎች ለመጀመሪያ ጊዜ በእጃቸው አስገብተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለሊቨርፑል በአጥቂ መስመር የሚሰለፈው ሳዲዮ ማኔ ነበር የማሸነፊያዋን የመጨረሻ የመለያ ምት የመታው። ሌላኛው የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሳላኅ በእንባ ተውጦ አምሽቷል። ማኔ እና ሳላህን በአፍሪቃ ዋንጫ ምክንያት ያጣው ሊቨርፑል በኤፍ ኤ ካፕ ድል ቀንቶታል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የማጣሪያ ዙር ማለፉን አረጋግጧል። ቻይና ውስጥ በሚካኼደው የኦሎምፒክ ግጥሚያ በወርቅ ሜዳሊያ ብልጫ ስዊድን ቀዳሚ ናት ጀርመን የአምስተኛ ደረጃ ይዛለች። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። መሪው ባየር ሙይንሽን እየገሰገሰ ነው።
እግር ኳስ
የሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ትናንት በፌሽታ እና ፈንጠዝያ ነበር ያመሸችው። ምክንያት ሴኔጋሎች ለ60 ዓመታት ሲጠብቁት የነበረውን ሕልም «የቴራንጋ አናብስት» ዕውን አድርገውታልና። አናብስቱ ትናንት ካሜሩን ውስጥ አስገምግመው ብቻ አልተመለሱም። 33ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫን በድል ከፍ አድርገው ወደ ሴኔጋል ዳካር አቅንተዋል።
መደበኛው 90 ደቂቃም ኾነ ጭማሪው በአጠቃላይ 120 ደቂቃው እስኪጠናቀቅ ድረስ በአብዛኛው ከፍተኛ ማጥቃት የሰነዘሩት ሴኔጋሎች ነበሩ። እንዲያም በመሆኑ የመጀመሪያው አጋማሽ 7ኛ ደቂቃ ላይ ፍጽም ቅጣት ምት አግኝተው ነበር። እናም የሊቨርፑሉ ሳዲዮ ማኔ እንደሚመታው ሲታወቅ ማግባቱ አይቀርም ተብሎ ነበር። ሆኖም የሊቨርፑል ጓደኛው ግብጻዊው ሳዲዮ ማኔ ለግዙፉ ግብ ጠባቂ አቡ ጋባል ጋባስኪ ጠጋ ብሎ አፉን በእጆቹ በመከለል የሆነ ነገር ሹክ ይለዋል። ምናልባትም ሳዲዮን አውቀዋለሁ የሚመታው በዚህ በኩል ነው ብሎትም ይሆናል። ወይንም ደግሞ የሳዲዮ ማኔን ስነ ልቦና ለመስለብም ይሆናል። ብቻ ሹክ አለው። ሳዲዮ ማኔም ወደ ግብ ጠባቂው ተጠግቶ ወደ ግብ መስመሩ እንዲያመራ በምልክት ዐሳየው። ጓደኛው ሞሐመድ ሳላኅም ግብ ጠባቂው በመገረም ነበር የተመለከቱት። ዳኛው ፊሽካ ነፉ። ሳዲዮ ማኔም መታ። ጋባስኪም ተወርውሮ ኳሷን ግብ ከመሆን አጨናገፈ። የሞ ሳላኅ ዕቅድ ተሳካ። ጨዋታው ቀጠለ።
ሳዲዮ ማኔም ሆነ «የቴራንጋ አናብስቱ» ፋታም አልሰጧቸው ፈርዖኖቹ ሜዳ እየተመላለሱ አስጨነቁ። ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ከእነ ጭማሪ ሰአቱ ተጠናቀቀ። እናም ወደ መለያ ምት አመሩ። የግብጹ ግብ ጠባቂ አቡ ጋባል ጋባስኪ እጅግ ሲፍለቀለቅ ነበር። ከዚህ ቀደም በርካታ ፍጹም ቅጣት ምቶችን ስላጨናገፈ ምሽቱን ሴኔጋሎች አለቀላቸው ተብሎ ነበር። ግብ ጠባቂው በሚጠጣው የውኃ ላስቲክ ላይ የተጻፈ ነገርም በፎጣው ሸሽጎ ደጋግሞ በጥንቃቄ ሲመለከት ነበር። ሁሉም ግን እንዳሰቡት አልሆነም። በመለያ ምቱ የመጨረሻዋን ወሳኝ ኳስ የመታው ሳዲዮ ማኔ ነበር። «የቴራንጋ አናብስት»ን ሊያስፈነጥዝ። በፍጹም ቅጣት ምቱ የተጨናገፈበት እልህ እና ቁጭት አሳድሮበታል። ኳሱን አጥብቆ በማክረር በግብ ጠባቂው በስተቀኝ በኩል ለጋው። ጋባስኪ ነቅቶበታል ሳዲዮ ማኔ በየት በኩል እንደሚመታ። ግን በዚህ ጊዜ ማኔ አክርሮ የመታት ኳስ ከጋባስኪ በስተቀኝ እጅግ ወደ ግቡ ቋሚ ተጠግታ ስለነበር ሊያጨናግፋት አልቻለም።
ጨፈሩ። «የቴራንጋ አናብስት» ዘለሉ። ሞሐመድ ሳላኅ እና ጓደኞቹ አነቡ። ግብጻውያን አምርረው አነቡ። ለስምንተኛ ጊዜ ከእጃችን ይገባል ያሉትን ዋንጫ ሴኔጋሎች ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ መጠበቅ ታከተን ሲሉ ከ60 ዓመት መጠበቅ በኋላ ዋንጫውን ወደ ዳካር ይዘው ተመዋል። 33ኛውን የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ሴኔጋል በመለያ ምት 4 ለ2 አሸንፋ ወስዳለች። የግብጹ ግብ ጠባቂ አቡ ጋባል ጋባስኪ የፍጻሜ ጨዋታው ምርጥ በረኛ ተብሏል። ሳዲዮ ማኔ የዘንድሮ የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ዋንጫ ተሸልሟል። የሀገሩ ልጅ የቸልሲው ግብ ጠባቂ ኤድዋርድ ሜንዲ ምርጥ ግብ ጠባቂ ተሰኝቷል። ሦስተኛ ደረጃን የያዘችው አዘጋጅ ሀገር ካሜሩን ኮከብ ግብ አግቢ ቪንሰንት አቡባከር የወርቅ ጫማ ተሸልሟል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ዙር የማጣሪያ ውስጥ መግባት ችሏል። ቅድመ-ማጣሪያውን ጨምሮ ለአምስተኛ ጊዜ በሚደረገው 4ኛው ዙር ግጥሚያ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጋና፤ ናይጀሪያ እና ሴኔጋል ተጋጣሚዎቻቸውን በሜዳቸው አሸንፈው ማለፋቸው ታውቋል። ለኮስታሪካው የ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዙር የማጣርያ ግጥሚያዋን የምታከናውነው ከጋና ጋር ነው። ጋና ቅዳሜ ዕለት በሜዳዋ ከዩጋንዳ ጋር ባደረገችው የመልስ ጨዋታ አሸንፋ ነው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን ያረጋገጠችው።
ጋና ኡጋንዳን 5 ለ0 ያደባየችው ኬፕ ኮስት ከተማ ውስጥ ነው። ናይጀሪያ በበኩሏ ካሜሩንን አቡጃ ከተማ ውስጥ 3 ለ0 ጉድ አድጋለች። ሴኔጋል ሞሮኮን ከውድድሩ ያሰናበተችው በመለያ ምት 5 ለ 4 ድል አድርጋ ነው። ሦስቱም ጨዋዎች ቅዳሜ ዕለት የተከናወኑ ሲሆን፤ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ታንዛኒያን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም 2 ለ 0 በመርታት ነው ወደ መጨረሻው ዙር ያለፈችው። የቲክቫህ ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ቅዱስ የምሩ ዮፍታኄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በቅርበት ተከታትሏል። ቡድኑ ከቀን ወደ ቀን እየበሰለ የመጣ መሆኑን ይናገራል።
ሴኔጋል የሁለት ጊዜያት የዓለም ዋንጫ ባለድል የኾነችው ናይጄሪያን በመጨረሻው ዙር ትገጥማለች። በሁለት ዙር ደርሶ መልስ በሚደረገው ግጥሚያ ኢትዮጵያም ጋናን ትገጥማለች። የመጀመሪያው ዙር ከመጋቢት 1 እስከ መጋቢት 3 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ሲካኼድ፤ የመልስ ጨዋታው ደግሞ ከመጋቢት 15-17 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት ታቅዷል። አፍሪቃን ወክለው ለዓለም ዋንጫ የሚያልፉት ሁለት ቡድኖች ናቸው።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት በባዬር ሌቨርኩሰን የ5 ለ2 ሽንፈት አስተናግዶ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል። አንድ ቀን ቀደም ብሎ ኤር ቤ ላይፕትሲሽን 3 ለ2 የረታው መሪው ባዬር ሙይንሽን ግን በ52 ነጥብ በመሪነቱ ስፍራ ተደላድሏል። ዶርትሙንድ በ43 ነጥብ ነው የሚከተለው። የትናንቱ ሽንፈት የነጥብ ልዩነቱን ወደ ዘጠኝ ከፍ አድርጎታል። ባዬር ሌቨርኩሰን በ38 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዟል። ላይፕትሲሽ 31 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አውግስቡርግ፤ ሽቱትጋርት እና ግሮይተር ፊዩርትስ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ሰፍረዋል።
የኤፍ ኤ ካፕ
በእንግሊዝ የኤፍ ኤ ካፕ ደግሞ ዋና አጥቂዎቹ ሳዲዮ ማኔ እና ሞሐመድ ሳላኅ በሌሉበት ሊቨርፑል ካርዲቭ ሲቲን 3 ለ1 ድል አድርጓል። ጆታ እና ሚናሚኖ ሁለቱን ግቦች አስቆጥረዋል። በተለይ 76ኛው ደቂቃ ላይ ታዳጊው ሐርቬይ ኤሊየት ኳሷን ተቆጣጥሮ ሰውነቱን በፍጥነት በመጠምዘዝ ያስቆጠራት ግብ ዕጹብ ድንቅ የምትባል ናት። በኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያ ትናንት ቦርመስ በ ቦሬሃም ዉድ 1 ለ0፤ እንዲሁም ላይስተር ሲቲ በኖቲንግሃም ፎረስት የ4 ለ 1 ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ቅዳሜ ዕለት በርካታ ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ ማንቸስተር ሲቲ ፉልሀምን እንዲሁም ኤቨርተን ብሬንትፎርድን 4 ለ 1 አደባይተዋል። ቸልሲ ፕሌይማውዝ አርጊሌን 2 ለ1፤ ቶትንሀም ሆትስፐር ብራይተንን 3 ለ1 አሸንፈዋል።
የቤጂንግ ኦሎምፒክ
ያለፈው ዓርብ ቤጂንግ ቻይና ውስጥ በደማቅ ኹኔታ በተከፈተው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች እስካሁን ድረስ ስዊድን 3 ወርቆችን በመሰብሰብ ትመራለች። የሩስያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በ2 ወርቅ፤ በ3 ብር እና 2 ነሐስ ይከተላል። ኔዘርላንድ፤ ቻይና፤ ጀርመን፤ ኖርዌይ እና ስሎቬኒያ እያንዳንዳቸው 2 ወርቅ በማግኘት እስከ 7ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ሃገራቱ የሚበላለጡት በብር እና ነሐስ ሜዳሊያ ብዛት ነው። ሩስያ አትሌቶቿ የተከለከለ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ተጠቅመዋል በሚል እንደ ሀገር በኦሎምፒክ እንዳትሳተፍ ዕገዳ ተጥሎባታል። ያም በመሆኑ ታሳትፎዋም ሆነ ውጤቱ የሚመዘገበው በሩስያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስም ነው።
ኦሎምፒክ ከመጀመሩ አስቀድሞ በርካታ ሃገራት ቻይናን በሰብአዊ መብት ጥሰት በመክሰስ ውድድሩ ላይ ጥላ ሊያጠላ ይችላል ብለዋል። አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ውድድሩ ላይ ባለመገኘት ተቃውሟቸውን ገልጠዋል። እንዲያም ሆኖ ግን በመክፈቻው ስነስርዓት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ጨምሮ ወደ 20 የሚጠጉ ሃገራት መሪዎች ታድመዋል። ከታዳሚዎቹ መካከል በቻይው አቻቸው ቀጥተኛ ግብዣ የተላከላቸው የሩስያ ፕሬዚደንት ብላድሚር ፑቲንም ተገኝተዋል።
ጃፓን፤ አውስትራሊያ፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ እና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ርምጃ በሚል መሪዎቻቸው በመክፈቻው ላይ እንዲገኙ አልላኩም። ሃገራቱ በእርግጥ አትሌቶቻቸውን ለኦሎምፒክ ውድድር ወደ ቤጂንግ ልከዋል። እንዲያም ሆኖ በደማቅ ስነስርዓት ባለፈው ዓርብ የተከፈተው የቤጂንግ ኦሎምፒክ የካቲት 13 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ