«ፈንድቃ» ባህላዊ ቡድን በጀርመን
ሐሙስ፣ ሰኔ 4 2007
በዝግጅቱ ላይ የላይቤርያዋ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍና የጀርመኑ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ሙለርንን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች የተገኙበት ይህ መድረክ መቀመጫዉን ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ ያደረገዉ የኢትዮጵያዉ «ፈንድቃ ባህላዊ ቡድን» እንዲሁም የተለያዩ የዓለም ከያኒዎች ባሳዩት ሙዚቃና ዉዝዋዜ ዝግጅቱ ደምቆ እንደነበር የጀርመን ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል። በዕለቱ ዝግጅታችን ባቫራያ ግዛት ላይ ስለተካሄደዉ ዝግጅት መሰናዶ ይዘናል።
G 7 የተባሉት ሰባቱ የበለፀጉት ሃገራት የወቅቱ ሊቀመንበር የሆነችዉ ጀርመን የመራችዉ የዘንድሮ ጉባኤ ባቫርያ ግዛት ሊካሄድ አንድ ቀን ሲቀረዉ ሙኒክ ከተማ እንብር ት ላይ በተካሄደዉ ዝግጅት በዓለም ታዋቂ ሰዎችና ፖለቲከኞች ሙዚቀኞች እንዲሁም የኢትዮጵያዉ ባህላዊ ቡድን ፈንድቃ የዝግጅቱ ተካፋይ ነበሩ። «በሕብረት ረሃብን መዋጋት » በሚል መርሕ ከተለያዩ የዓለም ሃገሮች የተሰባሰቡ ከያኒዎች በሙዚቃ በባህላዊ ዉዝዋዜ ረሃብ ተቃዉመዋል፤ ወዲህም ሰባቱ የበለፀጉት ሃገራት እስከ ጎርጎረሳዊዉ 2030 ዓ,ም ድረስ ከፍተኛ ረሃብን ከምድር እንዲቀርፉ ጠይቀዋል። የጉባኤዉን መጠናቀቅ ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰዉ ፈንድቃ ባህላዊ ቡድን በተለያዩ የኢትዮጵያ ባህላዊ አልባሳትና ዉዝዋዜ መድረኩን ማድመቁ ተነግሮለታል። የፈንድቃ ቡድን መሪ የሆነዉ ከያኒ መላኩ በላይ ኢትዮጵያን ወዳጅ የሆነች ጀርመናዊት ጋዜጠኛ ጋብዛቸዉ እንደመጡ ተናግሮአል።
ፈንድቃ ባህላዊ ቡድንን ጀርመን ባቫርያ ግዛት ሙኒክ ላይ በተካሄደዉ በዚህ ግዙፍ መድረክ እንዲሳተፉ የጋበጠችዉና የመድረኩ አንዷ አዘጋጅ ጀርመናዊትዋ ጋዜጠኛ ቢያተ ቬደኪንድ ፈንድቃ በአፍሪቃ ባህላዊ ሙዚቃና ዉዝዋዜ እንዲሁም በምዕራባዉያኑ ሙዚቃ መካከል እንደድልድይ ሊቆም የሚችል ቡድን በመሆኑ ልጋብዛቸዉ ወሰንኩ ስትል ትናገራለች።
«የጋበዝኩዋቸዉ እኔ ነኝ ። የዚህ መድረክ አንዷ አዘጋጅም ነኝ። የፈንድቃን ባለቤት መላኩን ሳዉቅ ብዙ ዓመት ሆነኝ። ባዘጋጀነዉ መድረክ ላይ የጀርመን ኮከብ ሙዚቀኞችና በዓለም ላይ የሚታወቁ ኮከብ ከያንያን ብቻ እንዲገኙ አልፈለኩም። ከአፍሪቃ ሃገራትም ሙዚቀኞች እንዲጋበዙ በመፈለጌ፤ ወድያዉ በጭንቅላቴ የፈንድቃ ባለቤት መላኩ መጣልኝ ። ምክንያቱም እነ መላኩ ለተመልካች የሚያቀርቡት የዳንስ የሙዚቃ አይነት የፖፕ አይነት ሳይሆን፤ በአፍሪቃዉያኑን ባህላዊ ሙዚቃ እና በምዕራባዉያኑን ሙዚቃ መሃል፤ ድልድይ ሆኖ ሊቆም የሚችል አይነት ሆኖ ስለአገኘሁት ነዉ። ታድያ እዚህ መጥተዉ ዝግጅታቸዉን ካሳዩ በኋላ እጅግ ተወዳጅ ሆነዋል ነአድናቆትንም አትርፈዋል። ይህን የምልሽ መላኩን ስለማዉቀዉ ሳይሆን እዉነታዉን ነዉ። ተጋባዡ ህዝብ አብሮ ደንሶአል፤ ተወዛዉዞአል።»
ቢያተ ኢትዮጵያን በቅርብ ካወቀች አራት አስርተ ዓመታትን እንዳስቆጠረች ትናገራለች። «ከ 40 ዓመት በፊት አዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን መንግሥት የልማት ትብብር ቅርንጫፍ መሥራያ ቤት ዉስጥ አገልግያለሁ። ቆየት ብሎም ሰዎች ለሰዎች በተሰኘዉ የካርል ሃይንስ የርዳታ ድርጅት ዉስጥ እዝያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ አገልግያለሁ። ከዝያም ለካርል ሃይንስ ትልልቅ የቴሌቭዥን ዝግጅቶችን አቅርብያለሁ። በተለይ ካርል 80 ኛ ዓመታቸዉ በተከበረ ጊዜ ። ከዚያን ጊዜ በኃላ ኢትዮጵያን ተዋዉቄ ልቤ ዉስጥ አድርጌያታለሁ ። አሁንም በተከታታይ ረዘም ላሉ ሳምንታት፤ ወራት ኢትዮጵያ ዉስጥ እየተቀመጥኩ ከወጣቶች ጋር እሰራለሁ።»
ኡሸር ከተባለዉ ታዋቂ አማሪካዊ ሙዚቀኛ ጋር እንዲሁም የማንዴላ የልጅ ልጅ የተገኙበት ይህ መድረክ በተለይ በዓለም ሃገራት ሴቶች ላይ የሚደርሰዉ ጭቆና እንዲቀረፍ ፖልዮና የመሳሰሉት በሽታዎች እንዲጠፉ ጥሪ የተደረገበት መድረክም እንደሆን የደንድቃ ባለቤት ከያኒ መላኩ ተናግሮአል።
አዲስ አበባ ዉስጥ ስለሚገኘዉ ስለፈንድቃ ባህላዊ የሙዚቃ ቤት ኒዮርክ ታይምስን ጨምሮ ሌሎች የምዕራባዉያኑ ጋዜጦች ስለ ባህላዊ ዳንሱ ዘግበዉለታል ያለን ከያኒ መላኩ በላይ፤ በዚሁ የባህል ዉዝዋዜ ቤት ሲያገለግል 17 ዓመታት እንዳስቆጠረ ይናገራል።
ድምፃዊ ዉዴ ተስፋዉ ባህላዊ ሙዚቃና ለማሳየት ወደ ጀርመን ስትመጣ የመጀመርያዋ ባይሆንም የአሁኑ ጉብኝትዋ ከሁሉም ጊዜ ለየት ያለ እንደነበር ትገልጻለች። «ደስ የሚል ነበር ጀርመን ባህላዊ ሙዚቃችንን ብቻ ሳይሆን ፤በጀርመን የተለያዩ ቦታዎችን ጎብኘትተናል። ብዙ ነገሮችን አሳይተዉናል። በጣም ደስ ይላል»
ሽሩባዋን ተሰርታ ፤ አሸንክታብ ቀሚስዋን አጥልቃ በባቫርያ መዲና ሙንሽን ላይ ያሳየችዉ የቡድኑ ተወዛዋዥ ዝናሽ ፀጋዬ ታደሰ ወደጀርመን ስትመጣ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ እንደሆነ ነግራናለች ። ፈረንጆቹ በእስክስታ ሹሩባዋም እንደተማረኩ ገልጻልናለች።
« ሱሩባዉን ሲያዩት እስቲ እንካዉ ስንት ሰዓት ፈጀብሽ ያምራል ይሉኛል እስክስታ ዉዝዋዛዬንም እንዴት ነዉ አያምሽም ወይ እንዴት እስክስ ታን ለመድሽ እያሉ ይጠይቁኛል። ሹሩባዉን ስትሰሪ ስንት ሰዓት ፈጀብሽ እያሉ ጠይቀዉኛል ። እኔም ነግሪያቸዋለሁ » መላኩ በላይ፤ በዚሁ የባህል ዉዝዋዜ ቤት ሲያገለግል 17 ዓመታት እንዳስቆጠረ ተናግሮአል።
ካዛንችስ መናሃርያ አካባቢ ብቸኛዉ ባህላዊ የምሽት ቤት እንደሆነ የነገርረን የፈንድቃ ባለቤት ከያኒ መላኩ፤ ከፈንድቃ ሌላ ኢትዮ ከለር በሚል ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን እንዳለ ገልጾአል።
ከኢትዮጵያዉያን ወጣቶች ጋር የተለያዩ ሥራዎችን እንደምትሰራ የምትናገረዉ ቢያተ ለኢትዮጵያዉያን ወጣቶች ፍቅር እንዳላት በተደጋጋሚ ገልፃለች መልክትም አላት።
«ለኢትጵያ ወጣቶች ማስተላለፍ የምፈልገዉ መልክት፤ ጠንካራ፤ ወኔ ሙሉ፤ በራሳቸዉ የሚተማመኑ፤ ለትዉልዳቸዉ የሚሰሩ የሚታገሉ እና በስማቸዉ የሚቆም ነገርን፤ እዉቅናና የሚያስገኝ ነገር፤ ለማድረግ እንዲታገሉ ነዉ። በፖለቲካ አልያም ለፖሊተከኞች ሳይንበረከኩ በጋራ በራስ በመተማመን መቆም ይኖርባቸዋል። ወጣቱ የተማረ እዉቀት ያለዉ በመሆኑ ለማንም በምንም ሳይንበረከክ ለጥሩ ነገር በጋራ መቆም ይኖርበታል»
የተመደበልን ሰዓት አጠረና የቡድኑን አባላት ባለክራሩ ፋሲካ ሃይሉን ባለመሰንቆዉ እንድሪስን በመሰናዶዉ አላካተትንም እንጂ በባህላዊዉ ሙዚቃ መሳርያዉ የተጫወቱልን ሙዚቃ አስደምጠናል። ፈንድቃ የጀመረዉን ባህልን የማስተዋወቅ ሥራ ይቀጥል በቀጣይ ያስፈንድቅ ነዉ መልክታችን። ወጣቱን ባህላዊ ቡድን ለቃለ ምልልሱ እያመሰገንኩ የዕለቱን መሰናዶዬን ላጠናቅ አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሃመድ