1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፉኩያማ በአዲስ አበባ፤ዐቢይ በአክሱም እና #ይኣክል የኤርትራውያኑ ተቃውሞ 

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2011

የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ፍራንሲስ ፉኩያማ ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች የሚከተሉትን ፍልስፍና እየነቀሱ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአክሱም በምርጫ ጉዳይ ላይ የሰጡት ምላሽ አነጋጋሪ ነበር። በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሚመሩት መንግሥት ይኣክል እያሉ ነው።

https://p.dw.com/p/3KRoS
Instagram-Icon
ምስል picture-alliance/xim

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት ፍራንሲስ ፉኩያማ ወደ ጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት አቅንተው ችግኝ ከመትከላቸው በፊት ባለፈው ማክሰኞ በፖለቲካ እና ምጣኔ-ሐብት ላይ ያተኮረ ንግግራቸውን በአዲስ አበባው ሐያት ሬጀንሲ ሆቴል አድርገዋል። ንግግራቸው የምጣኔ-ሐብታዊ ሽግግር ፖለቲካ እንዴት በሚለው ላይ ያተኮረ ነበር። 

ውይይቱን የታደሙት መሰረት ማሞ በትዊተር ገፃቸው እንዳሰፈሩት አሜሪካው የፖለቲካ ሳይንስ ልሒቅ በአዲስ አበባው መድረክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የልማታዊ መንግሥትን መንገድ የተከተሉ የምስራቅ እስያ አገሮች የግሉ ዘርፍ በምጣኔ-ሐብቱ ውስጥ በተጫወተው ቁልፍ ሚና ስኬታማ መሆናቸውን ተናግረዋል። ፉኩያማ ኋላ ቀር ቢሮክራሲ እና ደካማ የግል ዘርፍ ለኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥት ፈተና መሆናቸውን ተናግረዋል። ለበርካታ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች በተለይ ፉኩያማ የሚያቀነቅኑትን የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ፍልስፍና ለሚያውቁ ሰውየው ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ታይቷል። "ፍራንሲስ ፉኩያማ የኢትዮጵያ ጉብኝት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዜና የሚሆንበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለመገመት ባይከብድም ፤ ተምሬያለሁ የሚለው ሁሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተጠናክሮ የቀጠለው ንቀት እንዴት ቁጭት እንደማይፈጥርበት ሊገባኝ አይችልም" የሚል ትዝብታቸውን  ያሰፈሩት አሸናፊውን እግዚዓብሔርን መረጥኩ የሚል መጠሪያ የሚጠቀሙ የፌስቡክ ተጠቃሚ ናቸው። 
አስተያየታቸውን ሲቀጥሉ "የሰውየው ጉብኝት ኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ አሏት የሚባሉ አንጡራ ሃብቶቿ እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው ውይይት በሚደረግበት ሰሞን መሆኑ የበለጠ የሚያበሳጭ ነው። በነ መለስ ዜናዊ ጊዜ እነ ፖል ሄንዝ አስጠኚ ሆነው እንደተመደቡ ፉኩያማም ለአቢይ የኒዮሊበራሊዝም አስጠኚ ሆኖ ተመድቦም ይሆናል" ሲሉ ጥርጣሪያቸውን ገልጸዋል። 

Francis Fukuyama, ein US-amerikanischer Politikwissenschaftler
ምስል DW

ኢብሳ ዱግዳ በበኩላቸው "አሜሪካዊው የፖለቲካ ሳይንቲስት ሳሙኤል ሐቲንግተን ኢትዮጵያን ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ያወደመ የአምባገነንነት ዛፍ ተከሉ። አሁን ደግሞ ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንቲስት ፍራንሲስ ፉኩያማ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል። እርሳቸው የታሪክ ፍፃሜ እና የመጨረሻው ሰው (The End of History and the Last Man) ከተባለው መፅሐፋቸው የሚተክሉት ዘር ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር አበርክቶት ይኖረው እንደሁ እናያለን" ሲሉ ፅፈዋል። 

የታሪክ ፍፃሜ እና የመጨረሻው ሰው (The End of History and the Last Man) የተባለው የፉኩያማ መጽሐፍ ለገበያ ከቀረበ ጀምሮ ከፍተኛ ውዝግብ እና ክርክር የጫረ  ነው። ፉኩያማ በኮምዩኒዝም እና በሶቭየት ኅብረት ውድቀት ምክንያት ሊበራል ዴሞክራሲ እና ካፒታሊዝም አሸናፊ ሆነዋል ከሚል መደምደሚያ ደርሰዋል። በእርሳቸው ትንታኔ የምዕራባውያኑ ሊበራሊዝም እና ካፒታሊዝም ተገዳዳሪ የላቸውም። ደኅንነት እና ነፃነት ተረጋግጠዋል። በዚህም ሳቢያ ታሪክ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያለው ሚና አብቅቷል። ይኸ ትንታኔያቸው ወደ አዲስ አበባ ብቅ ያሉትን የፖለቲካ ሳይንስ ልሒቅ ለሰላ ትችት ዳርጓቸዋል። 

ጴጥሮስ አሸናፊ ከበደ "ፍራንሲስ ፉኩያማ ኢትዮጵያ መምጣቱንና ከጠቅላያችንም ጋር መወያየቱን ሰማን። ለማንኛውም ፍራንሲስ ድንቅ ፀሃፊ ነው። አብዛኞቹ መፅሃፎቹ ለምርምርና ለክርክር በር የሚከፍቱ ናቸው። በነገራችን ላይ ፉኩያማ አደገኛ የኒዮ ሊበራሊዝም አቀንቃኝ ናቸው። ጠቅላያችንን በዚሁ ፍልስፍና ሳያጠምቋቸው አይቀርም" ሲሉ ሐሳባቸውን አስፍረዋል። ፉኩያማ የአዲስ አበባ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ለኢትዮጵያ አዋጪ አለመሆኑን ጠቁመዋል። 

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአክሱም

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ አክሱም አቅንተው ከነዋሪዎች በተወያዩበት ወቅት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ በዚህ ሳምንት መነጋገሪያ ሆኗል። ጠቅላይ ምኒስትሩ "ምርጫ የማያደርጉ አገራት አሉ። ምርጫ ማድረግ ግዴታ የመጨረሻ ምሽግ አድርገን መውሰድ የለብንም። ምርጫ የማያደርጉ 20 እና 30 አመታት የተቀመጡ አገራት አሉ" ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ በሚቀጥለው አመት ይካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ እጣ-ፈንታ በምርጫ ቦርድ የሚወሰን ቢሆንም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ይራዘም አይራዘም የሚል ክርክር መኖሩን አንስተዋል። ጠቅላይ ምኒትሩ እርሳቸው የሚመሩት ኢሕአዴግ "በሚቀጥለው አመት ምርጫ ቢደረግ ችግር አለው የሚል ዕምነት" እንደሌለው በአክሱም ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ ተናግረዋል። 

Äthiopien Abiy Ahmed Premierminister
ምስል picture-alliance/AP Photo/Saudi Press Agency

ቀድሞም ውዝግብ ያስነሳው የ2012 ምርጫ ጉዳይ ከጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር በኋላም በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ትኩረት አግኝቷል። የተሰጡት አስተያየቶች ግን ከጠቅላይ ምኒስትሩ ሐሳብ ተቆንጽለው በተወሰዱ ዓረፍተ-ነገሮች ላይ የተንተራሱ ጭምር ሆነው ይታያሉ። ሐወኒ ዳቤሳ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ክቡር ዶ/ር ዐቢይ "ምርጫ አያስፈልገንም" ለማለት ራሱ በምርጫ የመጣ መሪ መሆን ግድ ይላል።  እርስዎ እንደ ሽግግር መንግሥት ተቆጥረው በስልጣን ላይ አሉ እንጂ አንድም ድምፅ አግኝተው የተመረጡ ሕጋዊ መሪ (Legitimate Leader) አይደሉም።  በተቻለ ፍጥነት ህዝባችን በመረጠው መንግሥት ብቻ የመተዳደር መብቱ ይጠበቅ።  ምርጫው በተያዘለት ቀን ይደረግ። የምርጫውን ጊዜ ማራዘም ፈፅሞ የምንቀበለው ጉዳይ አይደለም" ሲሉ ፅፈዋል።በዚያው በፌስቡክ መንደር ሙሌ አማን የተባሉ ተጠቃሚ "ነገር አይጣመም! ምርጫ አያስፈልገንም አላለም!! እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ቁርጠኝነት እንዳለው ነው እየተናገረ ያለው" ሲሉ ሐወኒ መሳሳታቸውን ጠቁመው ሊያርሟቸው ሞክረዋል። 

ፖለቲከኛው አቶ አስራት አብርሐም በአክሱም ለጠቅላይ ምኒስትሩ የቀረበውን ጥያቄ እና የሰጠውን መልስ አስታውሰው "ዶ/ር አቢይ አህመድ "ምርጫ ማካሄድ ግዴታ እንዳልሆነ፣ 20 እና 30 ዓመት ምርጫ ሳያካሄዱ የሚኖሩ ብዙ አገሮች አሉ" የሚል መልስ ሰጥቷል። ከተሰጡት መልሶች ሁሉ ይሄኛው ደካማ ነው። እሳቸዉ ያሉት እውነት ሊሆን ይችላል ነገር ግን እዚያ አገሮች ያሉት ዜጎች በውዴታም በግዴታም በህዝብ ያልተመረጠውን ተቀብለው እየኖሩ ስለሆነ ነው። አሁን በአገራችን ባለው ነበራዊ ሁኔታ ዶ/ር አብይ ያለምርጫ መሪ ሆኜ እቀጥላለሁ ቢሉ የሚቀበላቸው ህዝብ ወይም የሚታዘዟቸው ክልሎች ይኖራሉ ወይ? ነው መሠረታዊው ጥያቄ። ሰውዬ እኮ በግልፅ "የስልጣን ዘመንህ ካበቃ በኋላ በድጋሚ እስካልተመረጥክ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አትሆንም፤ መንግስትህም እንደመንግስት አንቀበለውም" ነው እያለ ያለው" ሲሉ ሐሳባቸውን አስፍረዋል። 

#ይኣክል የኤርትራውያኑ ተቃውሞ 

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን አገሪቱ ሉዓላዊነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ የመሯት የኢሳያስ አፈወርቂ መንግሥት ላይ "በቃ" የተባለ ዘመቻ እያካሔዱ ነው። በትግሪኛ፣ በእንግሊዘኛ እና ሌሎች በአገሪቱ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚካሔደው ይኸው ዘመቻ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ትዊተር እና ፌስቡክን ተጠቅሟል። የ16 አመት ታዳጊ ሳሉ አልጋ ተደግፈው የሚታዩበትን ምስል በትዊተር ያጋሩት አቢ የተባሉ የዘመቻው ተካፋይ "ሳዋ እጅግ አስፈሪ ቦታ ነው። ምን እንደሚፈጠር ማንም አያውቅም። በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ኖሪያለሁ" ሲሉ በወታደራዊው የማሰልጠኛ ጣቢያ ያሳለፉትን ጊዜ ፅፈዋል። በሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የተሰጠ የትምህርት የምስክር ወረቀት አያይዘው "እኛ ወደ ኮሌጅ እነሱ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተላክን። ሁላችንም ከዚህ የተሻለ ይገባናል። በውጭ አገራት የምትኖሩ ኤርትራውያን ለሰዎቻችሁ እንድትጮሁ እንፈልጋለን። የእናንተን ጥሪ እየተጠባበቁ ነው። ለእርዳታ እያለቀሱ ነው። ዝም አትበሉ! ንቅናቄውን ተቀላቀሉ" ያሉት ደግሞ በዚያው በትዊተር መንደር ሮራ ሐባብ ናቸው። 

Eritrea Präsident Isayas Afewerki
ምስል picture-alliance/dpa

ደስአለ በበኩላቸው "እኛ ዝም ብለን ስራ እየሰራን ገንዘብ በመላክ ቤተሰቦቻችንን እና ዘመዶቻችንን እንድንረዳ እና ከፖለቲካው ገሸሽ እንድንል ተነገረን። ተከፋፈልን፤ ተዳከምን አሁን ግን በቃ። ተነስተናል" ሲሉ የኤርትራ ገዢ ፓርቲ ሥልጣን መልቀቅ እንዳለበት ፅፈዋል። ሕሩይ ኪዳኔ የተባሉ ሌላው የዘመቻው ተሳታፊ በሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የገጠማቸውን በትዊተር አጋርተዋል። ሕሩይ "ለመጀመሪያ ጊዜ በሳዋ ፌስቲቫል ሲዘጋጅ ከውጭ አገራት የመጡ ተማሪዎችን ለማስደሰት እንደ አስመራ ኤክስፖ ያሳመርንው እኛ ጭቁኖቹ ተማሪዎች ነበርን። በጣም የሚያሳዝነው ነገር በበረዱ የቀዘቀዘ ውሐቸውን እየጠጡ እኛን ቁልቁል ያዩን ነበር"ሲሉ ያለፉበትን በፅፈዋል። 

በትግሪኛ ይኣክል የሚል መጠሪያ የተሰጠው ዘመቻ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያንን ጭምር ከሁለት የከፈለ ሆኖ ይታያል። ፊኒ ፌሊቴ በተሰኘ ስም በትዊተር መልዕክታቸውን ያሰፈሩ አንድ ሰው "በዘመቻው የሚሳተፉ ሰዎች አይረቡም። በሱዳን የተፈጠረውን አሳዛኝ ሁኔታ ዘመቻቸውን ለማጠናከር መጠቀማቸው ያሳዝናል" ሲሉ ወቅሰዋል። ፍሪ ኤርትራ በሚል ስም ሌላ የትዊተር መንደር ተጠቃሚ "በሁለት የተለያየ ዓለሞች ውስጥ መኖራችን እጅግ የሚያሳዝን ነው። ለሶስት ቀናት የወታደራዊ ማሰልጠኛ ሕይወትን መቋቋም የማይችሉ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ሲደግፉ ማየት ያሳዝናል። ከእውነታው እጅግ ተገንጥለዋል" ሲሉ በኢሳያስ አፈወርቂ ደጋፊዎች እና በነቃፊዎቹ መካከል ያለውን ልዩነት ጠቁመዋል። 

በነገራችን ላይ በሳምንቱ መጀመሪያ በስነ-ፅሁፍ የኖቤል ሽልማት አሸናፊው ናይጄሪያዊ ወሌ ሾይንካን ጨምሮ 103 የአፍሪካ ሰዎች ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደብዳቤ ፅፈው ነበር። የዴሞክራሲ አቀንቃኞች፣ የጸረ-ሙስና ዘማቾች፣ ጋዜጠኞች እና ጸሐፊያን ጭምር ለፕሬዝዳንቱ በላኩት ደብዳቤ በኤርትራ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል። ኤርትራ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅን ጨምሮ በተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ወደ ኋላ መቅረቱን የገለጹት ጸሐፊዎቹ ኢሳያስ አፈወርቂ ከፈቀዱ ወደ አስመራ ጎራ ብለው ለመነጋገር ጥያቄ አቅርበዋል።  

ፈተና፣ ኢንተርኔት እና ብልጭ ድርግም 

ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ግልጋሎት አብዝቶ ይቆራረጥ ይዟል። መንግሥትም እና ብቸኛው አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ-ቴሌኮም ለምን? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መስጠት አልፈለጉም። ታምሩ ኪታታ " አንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋም አገልግሎት ለሰጠው ስራ ብቻ ገንዘብ እንደሚቀበል ይታወቃል። ቴሌ ምንም አይነት የኢንተርኔት አገልግሎት ሳይሰጥ በደቂቃ 0.15 MB ይቆርጣል" ሲሉ ትችታቸውን ፅፈዋል። ታምሩ እንደሚሉት የኢንተርኔት አገልግሎት ባልነበረበት ወቅት ኢትዮ-ቴሌኮም ያስከፍላቸው ነበር።

ሙራድ ታደሰ "በኢንተርኔት ሱስ የተለከፈ ሰው ሰሞኑን ሳይወድ በግድ ያለ ኢንተርኔት መኖርን ቢለማመድ መልካም ይመስለኛል" ሲሉ ትዊተር ላይ ጽፈዋል። እጥፍወርቅ መላኩ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የመንግስት ባለሥልጣናት ኢንተርኔት ለፌስቡክ አገልግሎት ብቻ የሚውል አድርገው ነው የሚያምኑት። ኧረ ትምህርት ቤት ላኳቸውና የኢንተርኔት ጥቅም የሚል የስድስት ወር ኮርስ ይሰጣቸው"ሲሉ ተችተዋል። ዳጉ በሚል ስም አስተያየታቸውን ትዊተር ላይ ያሰፈሩ ሌላ ግለሰብ "የፈተና ሰሞን ኢንተርኔት መዝጋት ግን "ሌባ እናት ልጇን አታምንም" ነገር ይሆንብኛል! ብዙ ልጆች ሲያድጉ ወላጆቻቸውን ወይ ዘመዶችቸውን ወይ ጎረቤቶቻቸውን መሆን ነው ሚፈልጉት! አትስረቅ፣ ሲሰርቁ ዝም ብለህ አትለፍ => ልጆችህ አይሰርቁም!" ብለዋል። ዳግም አፈወርቅ "ከቀናት በፊት ውጪ ካለ ሰው ጋር የቃለመጠይቅ ቀጠሮ ያዝኩ (የውጪ ሰው ባተሌ ነው፣ ለኔ ብሎ ስንት ፕሮግራም ቀይሯል መቼም)፡፡ ለ5ሰዓት ቀጠሮ ከ4ሰዓት ጀምሮ online ሆንኩ፤ 4፡30 ላይ ሁሉም የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋረጠ፡፡ ምናለ ቀድመው ቢነግሩን?" ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል። 

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ